2023-04-09 08:20:34
ጌታችን በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ዕለት በጌትነትና በክብር፣ በውዳሴና በቅዳሴ “ሆሣዕና በአርያም” እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት ሲመሰገን እንዲሁም ሕፃናት “ዝም በሉ” በተባሉ ጊዜ በድንጋዮችም ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ጌታ ለሰጠው ሰላምና ፍቅሩ መታሰቢያ ተደርጎ በዕለቱ ይዘከራል፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ዘካርያስም ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያያቱ ግልገል (ውርንጫይቱ) ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’’ በማለት ትንቢት ተናግሯል፤ (ዘካ.፱፣፱) ጌታ ይህን የሰላምን ብሥራት እንደሚያበሥር የተነገረ የትንቢት ቃል ነው።
በዓሉም ጌታ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ‘ፀበርት’ ወይም ‘ዘንባባ’ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው’’ በማለት በቤተ ክርስቲያን ይዘከራል፡፡ (መዝ.፻፲፯፣፳፯) በዚህ ትውፊት መሠረትም ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች። በመሆኑም ይህን የሆሣዕና በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልናከብረውና ልናዘክረው ይገባል።
የአህያን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን የሚከተሉት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ሰማይ ስሚ፤ ምድርም አድምጪ፤ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም’’ በማለት ነቢዩ እንደተናገረው ጌታ በተወለደ ጊዜ ትንቢቱን ባልተቀበሉ ሰዓት በብርድ ወራት እናቱ የምታለብሰው ልብስ አጥታ ቅጠል አልብሳው በነበረ ጊዜ ለጌታ ሙቀት የገበሩለት ከብቶች፣ ላሞችና አህዮች ናቸው። (ኢሳ.፩፥፫) ‘ወአስተማወቅዎ አድግ ወላህም፤ አህያዎችና ላሞች ሙቀት ገበሩለት’’ እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም።
በሆሣዕና ዕለት ጌታን ለከብር የተሸከመችው አህያ ናት። አህያ በሆሣዕና ጌታ ተቀምጦ በሄደበት ዕለት ልብሳቸውን ሁሉ አንጥፈው በልብሱ ላይ በክብር እንዲትሄድ አደረጉ። ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ ሆኖ ሲመጣ ልብስም ተጎዝጉዞለታል፡፡ ስለዚህም ጌታ በጸጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጢአትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትና ልንለብስ ይገባል።
አህያዋ የኦሪት ምሳሌ ስትሆን ቀንበር መሸከም መቻሏ ሕገ ኦሪትን መጠበቅ የለመዱ የእስራኤል ዘሥጋ፣ ውርንጫይቱ ደግሞ ቀንበር መሸከም የማትችል ስትሆን የአሕዛብ ምሳሌ ናት። አህያይቱ ቀንበር መሸክም የለመደች እንደሆነች ሁሉ ኦሪትም ሕግ ናትና፤ ውርንጫይቱ ቀንበር መሸክም ያልለመደች እንደሆነች ወንጌልም ያልተለመደች ሕግ ናትና፡፡ (ወንጌል አንድምታ)
የልብስ ምሳሌነት ደግሞ ልብስ የውስጥ ገመናን ሸፋኝ ነው። “አንተ ገመናችንን የምትሸፍን ነህ” ሲሉ ልብስ አነጠፉለት። በተጨማሪም ልብስ ክብር ሲሆን “አንትም ክብራችን ነህ” ሲሉ ልብስ አነጠፉለት።
ከበዓለ ሆሣዕና ረድኤት በረከት ሱታፌ እንድናገኝ የእግዚአብሔር ቸርነት ከሁላችን ይሁን።
3.6K views05:20