Get Mystery Box with random crypto!

ሰሙነ ሕማማት ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ሳምንት በዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ት | ማኅበረ ቅዱሳን ( Mahibere Kidusan)

ሰሙነ ሕማማት

ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ሳምንት በዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ነው። ሰሙነ ሕማማት የተባለበት ምክንያት ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የጌታችንን ምሥጢረ ሕማማቱን ነገር በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት “ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማምነ” እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ ሲል እንደተናገረው የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ድኅነት በፍቃዱ ሕማማተ መስቀልን በትዕግሥት በመሸከም ማህያዊ ሞቱ በመስቀሉ የተፈፀመበት በመሆኑ እኛም መከራ መስቀሉን የምናስብበት ስለሆነ ሰሙነ ሕማማት ተብሏል። (ኢሳ.፶፫፥፬፣ማቴ.፰፡፲፣፯፣ዮሐ ፩፥፳፱)

ዕለተ ሰኑይ መርገመ በለስ ወአንጽሖተ ቤተ መቅደስ

በዚህ ዕለት ሰኑይ (ሰኞ) አዳምና ሔዋን ከገነት እንደተባረሩ፣ የበለስ ቅጠል እንዳገለደሙ ይታሰባል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እንደጻፈው (ማር.፲፩፥፲፪-፲፬) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበዓለ ሆሣዕና በመሸ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ። የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። በዚያን ጊዜ “ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” ብሎ ረገማት። ስለዚህም በሰሙነ ሕማማት የሚገኘው ሰኞ “መርገመ በለስ” የተፈጸመበት ዕለት መታሰቢያ ነው። የዚህም ትርጉም ወይም ምሥጢሩ ከበለስ ፍሬ መሻቱ ከሰው ፍቅር ተርቦ ለማጣቱን ለመግለጽ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእኛ መልካም የሃይማኖትና የምግባር ፍሬ ሽቶ ይመጣልና ፍሬ አልባ ሆነን እንዳያገኘን፣ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ እንደሚቆረጥና ቅጠሎቹም እንዲቃጠሉ ለእሳት እንደሚሰጡ የተነገረውን አስታውሰን መልካም ፍሬን ልናፈራ ይገባል።