2023-02-17 12:37:11
በትግራይ ክልል በሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት ዙሪያ በፌደራል መንግስትና ሕወሓትና መካከል ድርድር ሊካሄድ ነው
ሕወሓት ግዜያዊ መንግስቱን ለማቋቋም የሚረዳ ሰነድ በማጽደቅ፤ ከፌደራል መንግስት ጋር ይደራደራል ተብሏል
በፌደራል መንግስትና በሕወሓት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት በትግራይ ክልል የሚቋቋመውን ጊዜያዊ መንግስት አስመልክቶ ከፌደራል መንግስት ጋር እንደሚደራደር ሕወሓት አስታውቋል፡፡
ለዚህም በሕወሓት በኩል ከወታደራዊ መስክ፣ ከምሁራን፣ ከሕወሓት አባላት የተውጣጣ የጊዜያዊ መንግስት አደራጅ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ውስጥ አደራጅ ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በውይይቱም ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ተወካዮች ይሳተፋሉ ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ከውይይቱ በኋላ ግዜያዊ መንግስቱን ለማቋቋም የሚረዳ ሰነድ ይጸድቃል ብለዋል፡፡
ይህ ሰነድም በቀጣይ ሳምንት በሚዘጋጅ መድረክ ላይ ይፋ ይደረጋል ያሉት ጄነራሉ፣ ሕወሓት ይህን ሰነድ ይዞ ከፌደራል መንግስት ጋር ይደራደራል ብለዋል፡፡
ጄነራል ታደሰ የጊዜያዊ መንግስት ምስረታው የትግራይ ክልልን ሉአላዊ ግዛት የሚያስከብር፣ የክልሉን ጸጥታና የነዋሪዎችን ደኅንነት የሚያስጠብቅ እርምጃ ነው ያሉ ሲሆን፣ እርምጃው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ላይ ለውጥ የማምጣት ወርቃማ እድል አለው ብለዋል፡፡
በዚህም የጊዜያዊ መንግስት ምስረታው የውስጥ የፖለቲካ ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ እንደሆነ የገለጹት ጄነራሉ፣ የትግራይ ክልል ሕዝብን ችግር ከመፍታት ባለፈ እንደ አገር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል፡፡
ይሁንና አስተያየት ሰጪዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሕወሓት ጊዜያዊ መንግስት ከመቋቋሙ በፊት የሸብርተኝነት አዋጁ ሊነሳለት ይገባል ያሉ ሲሆን፣ “አሸባሪ” ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት ሕጋዊ መንግስት የማቋቋም ሚና ሊኖረው አይችልም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ሕወሓት ያቋቋመው ኮሚቴም ገለልተኛነቱ ላይ ጥያቄ የተነሳም ሲሆን፣ ጄነራል ታደሰ በመግለጫቻ ኮሚቴው ኹሉንም አካላት ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከፌደራል መንግስት በኩል እስከአሁን የተሰማ ነገር የለም፡፡
@leyumerga
1.2K viewsedited 09:37