2022-08-01 21:45:30
ለጥያቄዎች መልስ ምንሠጥበት ሰዓት ላይ ነን። በቅድሚያ ለአስተያየቶቻችሁ አመሠግናለሁ ። ጽሑፎቼን ምትከታተሉ፣ምትወዱ እና አስተያየት ሳትሠስቱ በመሥጠት ብርታት የምትኾኑልኝን ሁሉ አከብራችኋለሁ፣እወዳችኋለሁ ። ከምሥጋና ጋር።
.
ተመሳሳይ ዐውድ ያላቸውን ጥያቄዎች አንድ ላይ በማድረግ ልመልስ።
.
1. ለምንድነው እንደበፊቱ ቶሎ ቶሎ የማትለቀው?
.
የመጀመሪያው ምክንያት የበፊት ሁኔታ ላይ አይደለሁም ።በጣም የተጣበበ ጊዜ እና ተደራራቢ ሥራ ስለምወጠር እንደበፊቱ ቶሎ መጻፍ አዳጋች ኾኖብኛል ። ይኼ ቻናል ከተከፈተ ወደ አምስት ዓመታት ገደማ ተጠግቷል። ለነፍስ ሀሴት ግጥሞችን ወጎችን በመጻፍ በተወሰኑ ሰዎች ከመመሥገን ያለፈ ኑሮን የሚያቀና ነገር አይገኝም። ለእንጀራ ሌላ ሥራ ሲኖር የሥነ-ጽሑፍን ሥራ በመቀነስ ወደ ኑሮ ትግል ማምራት ግድ ነው።
.
ሁለተኛው ምክንያት ሥነ-ጽሑፍ የተለየ ባሕሪ ስላለው ነው። እስቲ ልጻፍ ተብሎ አይጻፍም። ነገሮችን በማስተዋል፣ስሜቶችን በመተርጎም ቃላትን ፈልፍሎ አውጥቶ የሚሠራ ነው። እንዲህ ያለው ሥራ አብዛኛው የአዕምሮ መረጋጋትን፣ ልብን የማድመጥ ፋታን ይጠይቃል። ለምሳሌ የማለዳ ማስታወሻ የሚለውን አምድ ከወሰዳችሁ ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሣሁ ውስጤ የሚመላለስን የመጀመሪያ ሐሳብ የምጽፍበት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእንቅልፌ የምነሣው የ ሥራ ሰዓት ላለማርፈድ በሚፈጠር ድንጋጤ ነው። የሚጻፉና ኑሮን የሚደጉሙ ተጨማሪ ሥራዎችን ማታ እየጻፍኩ አምሽቼ ስለምተኛ ጠዋት ለማሰብ ሳይኾን ለመሮጥ ነው ጊዜ ሚኖረኝ።ኾኖም የማለዳ ማ ስታወሻ ይቀጥላል።
.
2. ግጥም እና እኔ...?
.
"መቼ ጀመርክ?" "እንዴት አዳበርክ?" የሚሉ ተመሣሣይ ምላሽ ያላቸውን ጥያቄዎች ልመልስ።
ግጥም መቼ መጻፍ እንደጀመርኩ አላስታውስም። ሦስተኛ ክፍል እያለሁ እንደ ሰውነቴ ደካማ የኾኑ ግጥሞችን መድረክ ላይ ወጥቼ አነብ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ መማሬ የጠቀመኝ ይመስለኛል። ደጃዝማች በቀለ ወያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል። ልደታ ለልማት ተብሎ ሳይፈርስ(ሳይሰዋ) በፊት በዚህ ትምህርት ቤት የሚያበረቱኝ መምህራን፣ የሚያደምጡ ኝ ተማሪዎች ግጥምን እንድከተል ያደረጉኝ ይመስለኛል።
.
እኔ ሁለት ዓይነት ገጣሚዎች እንዳሉ አምናለሁ። ተፈጥሯዊ እና ኢ-ተፈጥሯዊ። ተፈጥሯዊ ገጣሚዎች ችሎታቸውን ለማዳበር ብዙ አይለፉም። ትንሽ ንባብ፣ ትንሽ አፈንጋጭነትና ትንሽ ኑሮ በቂያቸው ነው። የነዚህ ገጣሚዎች ስንኞች ቀጥታ ከአንባቢዎች ልብ ጋር ይጣበቃል ። የኛን ሕይወት የሚያወሩ እስኪመስለን። ኢ-ተፈጥሯዊ ገጣሚዎች ከብዕር ጋር ሲገናኙ ብዙ ያምጣሉ። ከሐሳባቸው ይልቅ ቃላቸው ጠጣር ነው ። መልዕክታቸው እንደ ቄጠማ ሁለት ቀን አይሻገርም። ይኼ ጊዜ ይወስዳል እንጂ ምናልባት ይስተካከላል። ግጥም ወዳጅ መኾን በራሱ ጊዜ የሚስተካከል መንገድ ያበጃል። ማዳበር፣ ማሻሻል፣መልመድ ለምትፈልጉ የምመክረው አንብቡ...ኑሩ... መሠረታዊ ዕውቀቱን ያዙ።
.
3. የምትጽፋቸው ነገሮች ከሕይወትህ ጋር ይገናኛሉ?
.
ሁሉም አይገናኝም። ሁሉም አይራራቅም። ግጥም እንደ ሥዕል ነው ይባላል። ለመሳል ማየት ግድ ነው። ግጥምም ላይ ለመግጠም ስሜቱን መጋራት ያስፈልጋል ። በእርጅና ምክንያት መንገድ ላይ የተጣለ፣የተረሳ የተገፋ ፈረስ ዐይቼ ግጥም ጽ ፌያለሁ። የፈረሱ ሕይወት የእኔ ሕይወት ኾኖ አይደለም። ገጣሚ ስለኾንኩ እና ስስ ነፍስ ስላለኝ ነው።(መልሼያለሁ ብዬ አስባለሁ)
.
4. ኢስላማዊ ግጥም. . .
.
እኔ ጥበብ ሐይማኖት የለውም ብዬ አምናለሁ። ሐይማኖት ግን ጥበብን ይጠቀማል። ለሰው ልጅ ነው ምጽፈው። ማንኛውም እምነት ይከተል ከየትም ይምጣ...ስሜት ያለው ሰው ሁሉ ግጥም ልቡን ቢያናግርለት ብዬ እመኛለሁ። "ከኢስላማዊ ወጣ ያለ ነው" ለምትሉ "መቼ ገባ አለ?" የሚል ጥያቄያዊ መልስ አለኝ። የጥበብ ቻናል እንጂ የሐይማኖት ቻናል አልከፈትኩም። አንዳንዴ እምነቴ ግጥሞቼ ላይ ሊታዩ ይችላሉ....መቼም ሰው አይደለሁ...
.
5. መድረክ ላይ ወግ እያቀረብክ ሰዎች ባይሥቁ፣ባይሰሙህ ምን ይሰማሃል..
.
ያለ ቦታዬ እንደተገኘሁ ይሰማኛል። አሁን ላይ መድረክ እየመረጥኩ መሔድ የጀመርኩት እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሞኝ ነው። እንደ ስሕተት ወስጄ ተምሬበት አልፋለሁ እንጂ የተለየ የማደርገው ነገር የለም።
.
6. Bot ብትከፍትልን...
.
ከዚህ ቀደም Bot ከፍቼ አስተያየቶች እቀበል ነበር። ነገር ግን አንዳንዶች የሚሰነዝሩት አስተያየት መርዛማነት፣ እንደ ሐይማኖት አባት ተመልክተውኝ ከመንፈሳዊ ዓለም የራቀ ሥራ ነው በሚል አሰልቺ ስድብ፣ "ግጥም አስለምደኝ" እና "ገምግምልኝ" የሚል የማልወደው ጥያቄ፣ አዳዲስ ሰዎችን ማወቅ አለመውደዴን እና ሌሎችንም ብዙ ምክንያቶች ጨምሮ Botን ለማጥፋትና ሁሉ እንዲያይ የሚያስችል ግሩፕ ለመክፈት ተገድጄያለሁ። So...No more Bot! ግን አንደንዴ ከአስተያየታቸው አንገብጋቢነት በመነሣት ራሴ የማናግራቸው ሰዎች አሉ..ኩራት እንዳልኾነ ይሰመርልኝ!
.
7.ግጥሞችህ ላይ ሐዘን ይበዛሉ...
.
አዎ...ሐዘን ለግጥም ትልቁ ምንጭ ነው። ሐዘን በቀላሉ ወደ ግጥም የመቀየር ባሕሪ አለው። ገጣሚ በልቡ ያየውን ይጽፋል...ሕይወት ደሞ አሳዛኝ ገጿ ይበዛል። ሰውን ለማነሣሣት የማለዳ ማስታወሻን እመርጣለሁ። ሐዘን ብቻ አልጽፍም። ግን ሐዘንም፣ ዙሪያችን ያንዣበበው ጽልመት በጥበባዊ መንገድ መገለጽ አለባቸው ። ሁላችንም ጋር ህመም እንዳለ ሁላችንም ማወቅ አለብን።
.
8. ከግጥም እና ከወግ?
.
ያለ ማንገራገር ግጥም!!
.
9. አርዓያ..ማበርከት ምትፈልገው፣ አምላክህ ፊት አንድ ግጥም አቅርብ ብትባል...?
.
ማንም አርዓያ አድርጌ አላውቅም። የማደንቃቸው ገጣሚዎች አሉ... አርዓያዎቼ ግን አይደሉም። ገጣሚ አርዓያ ይፈልጋል እንዴ? እናንተ እዚህ ምድር ላይ ለመኖር ማነው አርዓያችሁ? ማንን ዐይታችሁ ትኖራላችሁ? ልክ እንደዚህ ጥያቄ ነው ግራ ሚገባኝ "አርዓያህ ማነው?" ስባል..ግጥም መንገድ ነው..ኑሮ ነው። በመንገድ ለመሔድ የማንንም አረማመድ ማየት አይጠበቅብኝም። እንደ እግሬ ብርታት፣ እንደ ጫማዬ ስፋት እራመድበታለሁ። ለመኖር መተንፈስ መቻል እንጂ የሰው ኑሮና አኗኗርን አላይም።ግጥምም እንደ መንገድና ኑሮ ነው።
.
በሥነ-ጽሑፍ ማበርከት ምፈልገው...የሰዎችን ህመም እንደተካፈልኩ ቢያውቁ፣ አንድ ቀሽም ቀናቸው ላይ አንዲት ቃል ጽፌ ፊታቸው ላይ ፈገግታ መጫር ከቻልኩ፣ ክፋትን ተቃውሜ ክፉን ካሸማቀቅኩ፣ ደጎችን አድንቄ ደግነታቸው እንዳይከስም ከሞከርኩ...ብዙ አበርክቻለሁ ብዬ ማሰብ እጀምራለሁ። ጥበብ ጥቃቅን ነገሮችን መግራት ላይ ነውና ኃይሏ!
.
አምላክ ፊት አልቆምም። መቆም እንደምችል ሳምን ፊቱ ቆሜ የቱን ግጥም እንደማነብ አስብበታለሁ።
.
10. ስለ ሐገር...
.
አስተውላችሁ ከኾነ ብዙ ጊዜ በሴት ውስጥ ሐገርን እና እናትን እስላለሁ። እናት ያለችበት ሁሉ ሐገር ነው። ሐገርህ ላይ ካለህ እናት ባይኖርህም ለነፍሷ ቅርብ ነህ ብዬ አምናለሁ። ለዚያም ነው ራሴን ከሐገሬ አርቄ ማሰብ የሚያዳግተኝ። ግጥሞቼ መሐል ስለ ሴት ፍቅር የሚመስሉ ግን ስለ ሐገር እና እናት የሚያወሩ ግጥሞች አሉ።
4.4K viewsFa, edited 18:45