2023-01-28 19:45:17
የኮልፌ መካነ መቃብር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተገለጸ ።
...
ሀሩን ሚዲያ፥ ጥር 20/2015
...
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመካነ መቃብር ይዞታዎችን በተገቢው ለማስተዳደር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል። በከተማው የሚገኙት የዘላቂ ማረፊያዎች ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሻሻል ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባለፉት ሶስት ወራት ይህንን ጉዳይ ብቻ የሚከውኑ አምስት አባላት ያቀፈ ኮሚቴ በማዋቀር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
...
በዛሬውም እለት የአ/አ/ከ/እ/ጉ/ጠ/ም/ቤት የምክር ቤት አባልና የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ካሊድ መሀመድ ፣ የም/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማልን ጨምሮ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እ/ጉ/ከ/ም/ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኡስታዝ ባህሩ ተማም እና ዋና ፀሀፊ ኡስታዝ አንዋር ሱልጣን ተገኝተው ኮሚቴው በአጭር ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልክተዋል።
...
ለተቋቋመው ኮሚቴ ምክር ቤቱ ስራ አስኪያጅ በመመደብ የተጠናከረ ስራ እንዲከናወን አድርጎል። ኮሚቴው ከተዋቀረ ጀምሮ በከተማው የሚገኙ የመካነ መቃብር ስፍራዎችን በመመልከት ያሉበትን ተጨባጭ በመገምገም ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ ሀሳቦች የማፈላለግ ተግባራትን አከናውኗል። ኮሚቴው በእቅስቃሴውም ከፍተኛ አገልግሎት ለአዲስ አበባ ህዝበ ሙስሊም እየሰጠ የሚገኝውን ኮልፌ መካነ መቃብር ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
...
የኮልፌ መካነ መቃብር ከዚህ ቀደም ያለወን ቦታ ጥበትን ፣ የአጠቃቀም ችግር ፣የቀብር ጉድጎድ ቁፋሮ ወጥነት አለመኖር፣በበቂ መልኩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በእኩል ያለ ማስተናገድ ተግባራት ሲከናወኑ እንደነበር እና በአሁኑ ጊዜ መሰል ችግሮች እየተቀረፉ እንደሆነ በመስክ ጉብኝቱ ወቅት የኮሚቴው አመራሮች ይፋ አድርገዋል።
...
ከዚህ በተጨማሪ በኮልፌ መካነ መቃብር የህዝብ መገልገያ የሆኑ መፀዳጃ ቤቶች፣ መታጠቢያ ቤቶች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችና ሌሎች መሰረታዊ የሚባሉ ግንባታዎች መሰራታቸውንም ኮሚቴው አብራርቷል።
...
የኮልፌ መካነ መቃብር አስተዳደርና የፋይናስ ክፍል ሃላፊው አቶ ዳውድ መሀመድ በመካነ መቃብሩ ዙሪያ ለቀብር አፈፃፀም ሥራው የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጥን በሚመለከት ችግር መኖሩን አንስተዋል።
...
የመቃብር ይዞታ የሆኑ ቦታዎችም እየተሸራረፉ መሆናቸውን ሌላኛው የዘላቂ ማረፊያ አስተዳደር የሆኑት አቶ አብዱረህማን ጁሃር ገልፀዋል። ይህንን የተገነዘበው የከተማው እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሠል ችግሮችን ለመቅረፍና የተሻለ የመካነ መቃብር አስተዳደር እንዲኖር በዋናነት ኮልፌን መነሻ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
...
ኮልፌ ለዚህ ስራ ሲመረጥ ስፍራው ከታሪካዊነቱ ባለፈ ሌሎች ተመሳሳይ መካነ መቃብሮች በዚህ መልኩ ማደራጀት እንዲቻል ታስቦ መሆኑን የመካነ መቃብሩ አስተዳደር አቶ መሀመድ ዘይን ተናግረዋል። በውይይትና ጉብኝቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማል ቦታው ላይ ተገኝተን ያለውን ዕውነታ መመልከታችን ችግሮችን በጥልቀት እንድንረዳ አድርጎናል ብለዋል።
...
ምክር ቤቱ በመካነ መቃብር አስተዳደሩ የተነሱትንና በጉብኝቱ ወቅት የተገነዘቡትን ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል። በተጨማሪም ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተለያየ መልኩ ግንኙነት በማድረግ ያለውን ችግር ለመፍታት ይሰራል ያሉት አቶ ሪያድ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጥበቃ የሚደረግበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።
...
መረጃው የአ/እስ/ጉ/ከ/ም/ቤት ነው።
ሀሩን ሚዲያ
___
በቴሌግራ
ም፥ https://t.me/harunmedia
በዩቲዩብ ፥ http://bit.ly/3MXs17j
3.1K views16:45