2022-11-04 20:11:06
በነ አቶ ምትኩ ካሳ የሙስና የክስ መዝገብ በቁጥጥር ስር ሳይውሉ የቀሩ ተከሳሾች የመኖሪያ አድራሻን ዓቃቢህግ በክሱ ላይ አለመግለጹ ውዝግብ አስነሳ።
በተለያዩ ጊዜያት በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎች እና በሌሎችም አካባቢዎች በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ ማዕከላት የተፈናቃይ ተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እህልና ቁሳቁሶችን ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መጋዘን በማውጣት ለተረጂዎች ሳይደርስ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች በሚሊዮን ብሮች በመሸጥ እንዲሁም ብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በህገወጥ መንገድ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በመቶ ሚሊየን የሚገመት ገንዘብ ለእርዳታ ድርጅቱ ሲሰጥ ነበር በማለት ዓቃቢህግ በነሃሴ 20 ቀን 2014 ዓ/ም አቶ ምትኩ ካሳን ጨምሮ በአጠቃላይ በ13 ተከሳሾች ላይ በየደረጃው የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
አቶ ምትኩና 11ኛ ተከሳሽ አቶ ዩሀንስ በላይ ከማረሚያ ቤት እና ቀደም ሲል በዋስ ወቶ በውጭ ሆኖ ጉዳዩን የሚከታተለው እያሱ ምትኩ እንዲሁም በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አድርጎ መጠቀም ወንጀል የተከሰሱበት አንቀጽ ዋስትና ስለማያስከለክል በጥቅምት 8 ቀን በነበረ ቀጠሮ በ50 ሺህ ብር ዋስ ከስር ተፈተው በውጭ እንዲከታተሉ የተፈቀደላቸው አቶ ምትኩ ካሳ ባለቤት ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል : ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ እና ያልተያዘው የ12 ኛ ተከሳሽ ባለቤት 13ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ህይወት ከበደ በዛሬው ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በባለፈው ቀጠሮ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ላይ የዓቃቢህግ መልስን ለመጠባበቅና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 7 ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርባቸው የሰጠውን ትዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ ተሰይሟል።
ከሳሽ ዓቃቢህግ በሰዓቷ አለመገኘቷን ተከትሎ ችሎቱ ለ 10 ደቂቃ ገደማ ዓቃቢህግን ለመጠበቅ ተገዷል።
ስልክ ከተደወለ በኋላ ዓቃቢህጓ በችሎት የተሰየመች ሲሆን
የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ለሌላ ጊዜ በቀጠሮ ሰዓት ከ3:30 ጀምሮ እንዲገኙ ማሳሰቢያ ሰተዋል።
ይሁንና በዛሬው ቀጠሮ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 7 ተሳሾች ዛሬም ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
ፖሊስ በዛሬው ቀጠሮ ተከሳሾቹን በአድራሻቸው አፈላልጓ ለማቅረብ እንዲያስችለው እረጅም ቀጠሮ እንዲሰጠው በጽሁፍ ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ለፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስ ሁለት ጊዜ ቀጠሮ ተሰቶት ተከሳሾቹን ሳያቀርብ መቅረቱን አስታውሰዋል።
ጠበቆቹ አቶ ምትኩካሳ እና 11 ኛ ተከሳሽ ዩሀንስ በላይ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው የነዚህ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን በጠበቀ መልኩ ፍርድ ቤቱ ሊመለከትላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ጠበቆቹ ለፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።
ከሳሽ ዓቃቢህግ በበኩሏ የሌሉ ተከሳሾች መቅረብ ስላለባቸው ፖሊስ በሚሰሩበት መስሪያ ቤት የመኖሪያ አድራሻቸው ጠይቆ እንዲያቀርባቸው ለማስቻልና ካላቀረበም ማረጋገጪያ እንዲያመጣ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቃለች።
ሆኖም በክሱ የተከሳሾች አድራሻ ባለመጠቀሱና የመኖሪያ አድራሻ ፖሊስ ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት ጠይቆ ማቅረብ እንዲችል ያላቀረበበትን ማረጋገጪያ እንዲያቀርብ የሚለው የዓቃቢህጓ አስተያየት ተከትሎ በችሎቱ ውዝግብ አስተስቷል።
''በቁጥጥር ስር ሳይውሉ ተከሳሾችን መጀመሪያ ክስ ስትመሰርቱ ለምን የመኖሪያ አድራሻን አላካተታችሁም''? የሚል ጥያቄ በችሎቱ ዳኞች ለዓቃቢህ ቀርቧል።
ዓቃቂህጓ ''የመኖሪያ አድራሻቸው በመርማሪ ስላልተገኘ ነው በክሱ ያልተካተተው '' ስትል ምላሽ ሰታለች።
የችሎቱ ዳኞች ሌላ ጥያቄ አስከትለው ማለትም '' የተከሳሾችን መስሪያ ቤት ካወቃችሁ ታድያ ለምን እራሳችሁ ከመስሪያ ቤታቸው የመኖሪያ አድሪሻቸውን ጠይቃችሁ በክሱ ለምንአሟልታችሁ አላቀረባችሁም ''?የሚል ጥያቄ ዓቃቢህጓ ተጠይቃለች።
መዝገቡን ከፖሊስ የተረከብነው ስትል መልስ ሰታለች።
በጠበቆች በኩል የተከሳሶች የመኖሪያ አድራሻ በክሱ ላይ ባልተገለጸበት ሁኔታ በአድራሻቸው ፖሊስ አፈላልጎ ያቅርብ መባሉ አግባብ አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን አድራሻቸው በሌለበት ሁኔታ እንዴት ማረጋገጫ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይጠየቃል የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦች ተነስተዋል።
ክርክሩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ያልተያዙ ተከሳሾች ማለትም 2ኛ ተከሳሽ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽ የፋይናንስ ዳሪክተር አቶ አረጋው ለማ : 3ኛ የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዋና ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያም 4ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ዮናስ ወ/ትንሳኤ : 5ኛ በኤልሻዳይ ድርጅት የፋይናንስ ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ደሞዝ ሀይሉ 9ኛ ተከሳሽ የኤልሻዳይ ድርጅት የመጋዘን ንብረት መዝጋቢ አቶ መብራቱ አሰፋ ወ/ማርያም :10ኛ የኤልሻዳይ ድርጅት ስቶር ኦፊሰርና የመጋዘን ንብረት ክፍል ሰራተኛ የሆነው አቶ ገ/ሚካኤል አብርሐ እና በግል ስራ የሚተዳደሩት 12 ኛ ተከሳሽ ጌቱ አስራትን በሚመለከት ለፖሊስ ትዛዝ መሰጠት አለበት ወይስ ትዛዝ መሰጠት የለበትም የሚለውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለፊታችን ማክሰኞ ለጥቅምት 29 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።
4.5K views17:11