2022-05-20 20:42:45
መንግሥት የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ መፍትሔው የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው አለ!!
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ውስጥ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ ህገወጥነትና የሰላም መደፍረስ እንዲሁም ስርዓት አልበኝነትን ለመቆጣጠር መሆኑን አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያና በአጎራባች ክልሎች የሸኔ የሽብር ቡድን ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር በመተባበር ህዝባችን ላይ እያደረሰ የነበረውን ጥቃት ለመቀልበስ መንግስት የተሳካ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በአልሸባብ የሽብር ኃይል ላይ እየተወሰደ የሚገኘውም እርምጃ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በአማራ ክልል በህገወጥ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ዝውውር፤ በቡድን ተደራጅቶ ግለሰቦች ያፈሩትን ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ላይ የተሰማሩ፤ በነፍስ ግድያ የሚጠረጠሩ፣ አንዱን ህዝብ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክልሉ እንዳይረጋጋ በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባና በዙሪያው ኦሮሚያ ከተሞች በቡድን ተደራጅተው በልዩ ልዩ የዝርፊያ ወንጀሎች ላይ የተሰማሩ፣ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር አቀባባይ በሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች፤ እንዲሁም በወያኔ ሰርጎ ገቦች ላይም መንግስት ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብሏል፡፡
በሁሉም ክልሎች እየተካሄደ በሚገኘው ኦፕሬሽን በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ከነ ትጥቆቻቸዉ፤ ከዘረፉት ንብረትና ቀጣይ ሊፈፅሙ ያቀዷቸዉ ጥፋቶችን ካሰፈሩባቸው ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ እየተደረገ ነው። ጉዳያቸውም ተገቢውን ሂደት ጠብቆ እየተጣራ ለፍርድ እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በተለይም በፋኖ ስም የሚነግዱ የዝርፊያ ቡድኖች በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ክህደት የፈፀሙ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች እና የተላላኪዎቻቸው ዓላማ ማስፈፀሚያ መሆናቸው ነው ብሏል፡፡
መላው ህዝባችን ይህንን እኩይ ሴራ በመገንዘብ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት ይጠይቃል፡፡
መንግስት በበኩሉ በህገወጥ ተግባር ላይ በመሳተፍ፤ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሆነ ብለው፤ አቅደዉ በሚሰሩ አካላትና ግለሰቦች እንዲሁም የሚዲያና የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
T.me/ethio_mereja
ኢትዮመረጃ
10.2K viewsedited 17:42