Get Mystery Box with random crypto!

በኢትዮጵያ በተቋረጡ እና በቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የ35 ቢሊዮን ብር ካሳ በተቋራጮች ተጠየቀ | ETHIO-MEREJA®

በኢትዮጵያ በተቋረጡ እና በቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የ35 ቢሊዮን ብር ካሳ በተቋራጮች ተጠየቀ

የ #ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር “በፀጥታ ችግር” ምክንያት በተቋረጡ እና በቆሙ የመንገዶች ፕሮጀክቶች ላይ 34.95 ቢሊዮን ብር ካሳ በተቋራጮች መጠየቁን አስታወቀ።

አስተዳደሩ እስከ 2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ድረስ “በፀጥታ ችግር” ምክንያት “ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ውላቸው የተቋረጠ” 31 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 19ኙ የሚገኙት የፋኖ ታጣቂዎች እና የፌደራል መንግሥቱ ግጭት ውስጥ በገቡበት የአማራ ክልል ነው።

ለሁለት ዓመታት ያህል ጦርነት በተካሄደበት የትግራይ ክልል ደግሞ 11 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውላቸው ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚንቀሳቀስበት የኦሮሚያ ክልል ደግሞ 19 የመንገድ ፕሮጀክቶች በጊዜያዊነት ቆመዋል ብሏል።

በፀጥታ ችግር በተቋረጡ እና በቆሙ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር ውስጥ፣ የውጭ አገር የሥራ ተቋራጮች በድምሩ 34.95 ቢሊዮን ብር ካሳ ጠይቀዋል።ከዚህ ውስጥ 87 በመቶ ወይም 30.5 ቢሊዮን ብር ካሳ የጠየቁት የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ናቸው።