2023-08-05 01:42:17
+ ጻድቅ ሆኖ ተመለሰ +
አባ ፕሮፎርዮስ እንዲህ ሲሉ ገጠመኛቸውን ያስታውሳሉ ፦
‘በጥምቀት በዓል ሰሞን ውኃው ተጸልዮበት ከተባረከ በኋላ ለካህናት ወደ ሰዉ ቤት መሔድና ጠበል መርጨት የተለመደ ሥርዓት ነው፡፡ የሆነ ዓመት ላይ ይህንን ጠበል እየረጨሁ ምእመናንን ለመባረክ ከቤተ ክርስቲያን ወደ መንደር ወጥቼ ነበር፡፡ በየቤቱ በር አንኳኳና ‘አመ ተጠምቀ እግዚእነ በዮርዳኖስ...!’ /ጌታ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ.../ እያልሁ እያዜምሁ እገባለሁ፡፡
ብዙ መኖሪያ ቤቶች ወዳሉበት መንደር እንደዘለቅሁ አንድ በብረት በር የተዘጋ ትልቅ ጊቢ ጋር ደረስሁ፡፡ ከፍቼ ዘልቄ ገባሁ ፤ ጊቢውን የሞላውን መንደሪን ፣ ሎሚና ብርቱካን የተተከለበት የአትክልት ሥፍራ አልፌ ቀጥ ብዬ ገባሁ፡፡ ሕንጻው ወደ ምድር ቤትና ወደ ላይኛው ፎቅ የሚያስወጡ ሁለት ደረጃዎች አሉት፡፡ ወደ ላይ ወጥቼ አንዱን በር ሳንኳኳ አንዲት ሴት ብቅ ብላ በሩን ከፈተች፡፡ ‘አመ ተጠምቀ እግዚእነ በዮርዳኖስ...!’ ብዬ ማዜም ስጀምር በፍጥነት አስቆመችኝ፡፡ ይሁንና ድምፄ በደንብ ተሰምቶ ስለነበር ከግራ ከቀኝ ካሉት ክፍሎች ውስጥ ወጣት ሴቶች ወደ ኮሪደሩ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ነገሩ ገባኝ ፤ ‘አሃ ዘልዬ የገባሁት ለካ መሸታ ቤት ከሚሠሩ ሴቶች ቤት ኖሯል?’ አልኩኝ በሆዴ፡፡
‘እባክዎን ይሒዱ አባ’’ አለች ቀድማ የወጣችው ሴት ‘እነዚህ ሴቶች መስቀል መሳለም የሚገባቸው አይደሉም ፤ እኔን ያሳልሙኝና ቶሎ ይሒዱ’ አለች በችኮላ፡፡
ኮስተር አልኩና ‘ካህን ነኝ ቤቱን ሳልባርክ አልሔድም’ አልኳት
‘እሱን ይችላሉ እነዚህ ሴቶች ግን መስቀሉን አይሳለሙም’ ብላ ፍርጥም አለች፡፡
‘መስቀሉን መሳም የሚገባው አንቺ ሁኚ እነርሱ በምን እናውቃለን? እግዚአብሔር መስቀሉን መሳለም የሚገባው ማን ነው ብሎ እኔን ቢጠይቀኝ ኖሮ መስቀል መሳለም የሚገባው ለአንቺ ሳይሆን ለሴቶቹ እንደሆነ በነገርሁት ነበር፡፡ ምክንያቱ ከምትመጻደቂው ከአንቺ ይልቅ የእነርሱ ነፍስ ትሻላለች’ ብዬ ገሠጽኋት፡፡ ደንግጣ ዝም አለች ፤ እኔም ሴቶቹን ወደ እኔ እንዲመጡ ጠራኋቸው፡፡
ከዚያም ‘‘አመ ተጠምቀ እግዚእነ በዮርዳኖስ...!’ እያልኩ ከመጀመሪያው በበለጠ ኃይል መዘመር ቀጠልሁ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እነዚህ ምስኪን ነፍሳት እንድመጣ እንዳመቻቸልኝ ስላወቅሁ ውስጤ በደስታ ተሞልቶ ነበር፡፡
ሁሉም መስቀሉን ተሳለሙ፡፡ ሁሉም ያጌጠ ልብስ ለብሰው ሊወጡ ተዘጋጅተው ነበር፡፡ እንዲህ አልኳቸው ፦ ልጆቼ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ፤ እግዚአብሔር የሚወደው ሁላችንንም ነው፡፡ እርሱ መልካም ነውና ለኃጢአተኞችም ለጻድቃንም ዝናምን ያዘንባል፡፡ እርሱ የሁላችን አባት ነውና ለሁላችን ይጨነቃል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ወደ እርሱ መምጣት እርሱን መውደድና መልካም መሆን ብቻ ነው፡፡ እርሱን ውደዱ ምንኛ ደስተኛ እንደምትሆኑ ታያላችሁ’’
በመደነቅ ይመለከቱኝ ነበር ፤ በተጨነቀች ትንሽ ነፍሳቸው ውስጥ የሆነ ነገር እንደቀረ ያስታውቅ ነበር፡፡
‘እናንተን ለመባረክ እግዚአብሔር ዛሬ ወደዚህ ቤት የመምጣትን ክብር ስለሠጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ’ አልኳቸው፡፡ ለመሔድ ስነሣ ‘እግዚአብሔር ለዘላለም ይባርካችሁ’ አልኳቸው ፤ ‘አሜን አባ’ ብለው በአንድነት መለሱ ፤ ጉዞዬን ቀጠልሁ፡፡
ይህንን አጭር ታሪክ በኦርቶዶክሱ ዓለም እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ እጅግ ውብ መጻሕፍት አንዱ ከሆነው ‘Wounded by Love ፤ The Life and the Wisdom of Saint Porophyrios’ ከተሰኘው የአንድ መነኩሴን ሕይወት የሚተርክ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡
ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‘እግዚአብሔር በጽድቁ ከሚመካ ጻድቅ ይልቅ ስለ ኃጢአቱ የሚያለቅስ ዘማዊን ይወድዳል’ ይላል፡፡ በእርግጥም ራስን አጽድቆ የሌላውን ሰው ኃጢአት የማሰብን ያህል ኪሳራ በክርስትና ሕይወት የለም፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበው የሌሎች ሰዎችን ኃጢአት ሲቆጥር ሳይሆን የራሱን በደል ሲቆጥር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‘እኔ መተላለፌን አውቃለሁና ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና’ እንዳለው እግዚአብሔር ኃጢአትህ ተሰረየችልህ የሚለው ሰው የራሱን ኃጢአት ዘወትር የሚያስብ ሰው ነው፡፡
የነነዌው ቅዱስ ማር ይስሐቅ ‘መላእክትን ከሚያይ ሰው ይልቅ የራሱን ኃጢአት የሚያይ ሰው ይሻላል’’ ይላል፡፡ ባለ በገናው ‘እባክህ ጌታዬ ሥጠኝ መስታወት ፤ የሰው ሥራ ትቼ የእኔን አይበት’ እንዳሉ የራሱን በደል ማየት ከሚችል በቀር ይቅርታን የሚያገኝ የለም፡፡ ለብዙዎቻችን ከራሳችን ይልቅ የሰው ጉድፍ ማውጣት ይቀልለናል፡፡ ሰው ሆኖ ሌላ ሰውን ኃጢአተኛ ነህ የማለትን ኃጢአትና ትዕቢት ግን የለም፡፡ የሰዎችን ድክመት ባየን ጊዜ ከመሳደባችን በፊት እኛ ከዚያ ሰው በኃጢአት ብዛት በምንም እንደማንሻል ማሰብ አንደበታችንን ይሰበስብልናል፡፡
አባ ሲድራስ የተባለ አባት አንድ ወጣት መነኩሴ የወይን ፍሬ ሰርቀሃል ተብሎ ከገዳም ሲባረር አይቶት ተከትሎት ወጣ፡፡ አባታችን ወዴት ትሔዳለህ ሲሉት ‘እሱ ወይን ሰረቆ ከተባረረ እኔ የሠራሁት በደል ብዙ ነውና አብሬው ብወጣ ይሻላል ብዬ ነው’ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት መነኩሴውን ከመባረር አዳኖታል፡፡ ወዳጄ እኔና አንተ በወንድማችን የምንፈርደው ከእርሱ የባሰ የተሸሸገ በደል ተሸክመን መሆኑን አንርሳ፡፡ ‘እኔ እንኳን ብዙ ኃጢአት የለብኝም’ የምንል ከሆነ ግን በድሏል ካልነው ሰው የከፋ ለንስሓ መንገድ የሌለው በደል ውስጥ ነን፡፡ እግዚአብሔር ሊያድነን የሚችለው ከምናምነው ኃጢአታችን እንጂ ከመመጻደቃችን አይደለም፡፡
በወንጌል ጌታችን ከተናገራቸው ታሪኮች እጅግ የተዋቡት ምንባባት ኃጢአታቸውን ያልደበቁና ያልተመጻደቁ ኃጢአተኞች ታሪክ ነው፡፡ የዘኬዎስ ፣ የባለ ሽቱዋ ማርያም ፣ ልትወገር የነበረችው ሴት ወዘተ ታሪኮች ኃጢአታቸውን አምነው ይቅርታ ያገኙ ሰዎች ታሪኮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ታሪክ ስለ አንድ ቀራጭ ይናገራል፡፡ በቤተ መቅደስ ፈሪሳዊውና ቀራጩ ጎን ለጎን ቆመው ይጸልያሉ፡፡
ፈሪሳዊው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እንኳን ራሱን ዝቅ አያደርግም፡፡ አፉን ሞልቶ ጽድቁን ያወራል፡፡ ጽድቅን ተናግሮ የሚገኝ ነገር ያለ ይመስል ‘እጾማለሁ ፣ ዐሥራት አወጣለሁ’ እያለ ይመጻደቃል፡፡ አልፎ ተርፎ ‘እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ’ ብሎ የቀራጩን ኃጢአተኝነት ለእግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ወዳጄ ሺህ ጊዜ በጎ ብትሠራ እንዲህ አደረግሁ ያልህ ቀን ዋጋ ታጣለህ ፣ ስለ ሌሎች ሰዎች ኃጢአት ማውራትና ማሰብ እስካልተውህ ለእኔ ፈሪሳዊ ነህ እያለን ነው መሐሪው ጌታ፡፡
ቀራጩ ግን ‘‘በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ’’ ይላል ጌታችን፡፡ በእውነት እንዴት ያለ ቃል ነው፡፡
27.0K views , 22:42