Get Mystery Box with random crypto!

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የሰርጥ አድራሻ: @deaconhenokhaile
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 64.23K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ቻናል በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ፈቃድ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ነው::
@deaconhenokhaile
"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን"
2ኛ ቆሮ. 2:14

Ratings & Reviews

2.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 2

2024-01-11 17:22:48 የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ (ርእስ)

የአእላፋት ዝማሬን ዕውን ለማድረግ ላለፉት ሦስት ወራት እንቅልፍ ያጡ ፣ የታመሙ ፣ ልባቸው በስድብና በሽሙጥ ንግግር የቆሰለ ፣ በረዣዥም ስብሰባዎችና የጉልበት ሥራዎች የዛሉ ፣ ዝግጅቱን በዚህ ደረጃ ከፍ እንዲል ሰዎችን አሳምኖ ገንዘብ በማሰባሰብ የተንከራተቱ ፣ በአንድ ትንፋሽ ሠላሳ መዝሙር ሲያጠኑ የከረሙ ፣ መዝሙር ለማስቀረጽ ሥራ ትተው በስቱድዮ የዋሉ ፣ ሦስት ጊዜ revise የተደረገውን Stage design የሠሩ ፣ በመሐረነ አብ ጸሎት በየአድባራቱ ደጅ የጠኑ ፣ የዘማርያን ልብስና ልብሰ ተክህኖ ዲዛይን ሲያደርጉ ፣ ተነግሮ የማያልቅ ድካም የደከሙ ትሑታንና ታዛዦች የሆኑ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ የቦርድና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ፣ የጃን ያሬድ ኅብረ ዝማሬ መዘምራን ፣ የጃን አጋፋሪ event organizing ቡድንና በሥሩ የተቋቋሙ 15 ቡድኖች ፣ የጃን አግናጥዮስ የሕፃናትና አዳጊዎች project አባላት ፣ የጃን እስጢፋኖስ ዲያቆናት ፣ የጃንደረባው ሚድያ እሳት የላሱ የካሜራና ኤዲቲንግ የግራፊክስ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ ወጣቶች የአእላፋት ዝማሬን እውን ለማድረግ የከፈሉት መሥዋዕትነት እጅግ ብዙ ነው::

ለዚህ አገልግሎት ምስጋና የሚገባው ዕንባና ተማጽኖአችንን ያልናቀ ልዑል እግዚአብሔር ነው::

ዓለም ዘመኑ ጥሩ አይደለም ብላ ስካሩን ጭፈራውን ፈንጠዝያውን ግድያውን አላቆመችም:: እኛም ስብሐተ እግዚአብሔር የወቅቱን ሁኔታ እያየች የማታስታጉል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደመሆናችን ሲከፋን የምንተወው ደስ ሲለን የምንቀጥለው መዝሙር የለም ብለው ለጸሎተ ምሕላና ለአእላፋት ዝማሬ የተሠጡ ወጣቶች ብዙ ናቸው:: "አርምሞ ጽርዓት በሌለበት ምስጋና ሳናቋርጥ ዘወትር እናመሰግንሃለን:: ይኸውም ሊቃነ መላእክት የሚያመሰግኑህ ምስጋና ነው" (ጸሎተ ኪዳን)

ምግብ ቤት ገብተን ጥሩ ስንበላ አስተናጋጁን እናመሰግናለን:: ቲፕ እንሠጠዋለን:: ማዕድ ቤት ውስጥ እሳት የበላቸውን ሼፎችና ተባባሪ ሠራተኞች ግን አናያቸውም:: የአእላፋት ዝማሬንም በተመለከተ ሊመሰገን የሚገባው እንቅልፉን የሠዋ ብዙ ወጣት ከጀርባ አለና አስተናጋጁን ለቀቅ አድርጋችሁ ሼፎቹ ላይ አተኩሩ::
ከዚያ ውጪ ግን ከታመነበት ተአምር መሥራት የሚችለውን ቅን 1/21ኛውን ጃን ያሬድ ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ በጸሎት በገንዘብ በሃሳብ ደግፉ::

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድን ለመደገፍ

https://donate.janderebaw.org/

በቴሌ ብር
Merchant ID 777582
The Ethiopian Jandereba Generation

8261
Commercial Bank of Ethiopia

8261
Abyssina Bank

Janderebaw Media
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ The Ethiopian Jandereba Generation
13.1K views- :, 14:22
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-12-07 09:22:10 ነቢያት ጌታ "ይወርዳል ይወለዳል" ብለው የተናገሩት ትንቢት እንዲፈጸም ተመኝተው ጾሙ ጸለዩ:: እኛ ስለምን እንጾማለን? ክርስቶስ ተወልዶ ፣ ተጠምቆ ፣ አስተምሮ ፣ ተሰቅሎ ፣ ሞቶ ፣ ተነሥቶ ፣ ዐርጎ ፣ በአባቱ ቀኝ አይደለምን? አሁን ለምን እንጾማለን? ብለን እናስባለን::

ጌታ በእኔና አንተ ልብ ውስጥ እውነት ተወልዶአልን? እውነት የእኛ ልብ እንደ ቤተልሔም ግርግም ለክርስቶስ ማደሪያ ሆኖአል? ማደሪያ አሳጥተን ከእናቱ ጋር አልመለስነውም?

የጥምቀቱ ትሕትና በእኛ ልብ መቼ ደረሰ? የስቅለቱ ሕማም መች በእኛ ሕሊና ተጻፈ? የትንሣኤው ተስፋ የዕርገቱ ልዕልና በእኛ ልቡና መቼ ዐረፈ?

ስለዚህ ነቢያት "ውረድ ተወለድ" ብለው የጾሙትን ጾም እንጾማለን:: ጌታ ሆይ በእኔ ሕይወትም ውስጥ ውረድ ተወለድ የእኔን ሰውነት ማደሪያህ አድርገው:: ሕዋሳቶቼ ከኃጢአት አርፈው እንደ ቤተልሔም ግርግም ማደሪያህ ይሁኑ::

የቤተልሔም እንስሳት ትንፋሽ ገበሩልህ ፣ የቢታንያ ድንጋዮች ዘማሪ ቢጠፋ ሊዘምሩ ዝግጁ ነበሩ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለክብርህ ተቀደደ ፣ ጨረቃ ላንተ ደም ለበሰች ፣ ፀሐይ ስላንተ ጨለመች ፣ ከዋክብት ለስምህ ረገፉ ፣ ዓለቶች ለፍቅርህ ተሰነጠቁ::

ከቤተልሔም እንስሳት ፣ ከቢታንያ ድንጋዮች ፣ ከቤተ መቅደስ መጋረጃ እኔ እንዴት አንሼ ልገኝ? የቢታንያ ድንጋይ ያወቀህን ያህል ሳላውቅህ ፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ የተረዳህን ያህል ሳልረዳህ እንዴት ልኑር?

ዓለት ላንተ ሲሰነጠቅ የኔ ልብ ለምን ከዓለት ደነደነ? ጨረቃ ደም ስታለቅስ እኔ መከራህ ለምን አልተሰማኝም?
ሙታን በሞትህ ሲነሡ እኔ ምነው ከኃጢአት ሞት መነሣት ተሳነኝ?

ለዚህ ነው በእኔ ሕይወት ገና አልተወለድክም የምለው::

ስለዚህ ጌታ ሆይ የነቢያትህን ጾም ጸሎት ሰምተህ የወረድህ የተወለድህ ጌታ ሆይ በእኔም ሕይወት ውረድ ተወለድና እኔም ከመላእክት ጋር አብሬ ልዘምር ፣ ከሰብአ ሰገል ጋር ሥጦታህን ልቁጠር ፣ ከእረኞች ጋራ ልደነቅ:: ልደትህ ሳይገባኝ ምጽዓትህ እንዳይደርስብኝ እርዳኝ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጾመ ነቢያት 2015 ዓ.ም. የተጻፈ
12.8K views- :, 06:22
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-22 08:37:39 የትምህርት ዕድል ያመለጠህ መስሎህ ነው? ገና ሺህ የትምህርት ዕድሎች አሉህ:: ዕድሜህ ያመለጠህ መስሎህ ነው? ነገ የሚጠብቁህ ብሩሕ ዘመናት እኮ ቁጭ ብለው አሉ? የሚረዳኝ ሰው የሚያስብልኝ ሰው አጥቼያለሁ? ብለህ ከሆነም ካልሰሙህ ጥቂቶች በላይ ልንሰማህ የምንሻ "ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ"

መከራ ጸናብኝ ኑሮ ጨለመብኝ የሀገሪቱ ሁኔታ ተስፋ አሳጣኝ ብለህ ይሆን? እኛስ አብረንህ አይደልንም? አብረን ከገባንበት ችግር አብረን ብንወጣ አይሻልም? ከአንተ በባሰ ሁኔታ የታሰርንና የተገረፍን ጳውሎሶችና ሲላሶች "ሁላችን በዚህ አለንና በራስህ ክፉ አታድርግ" ስንልህ ስማን::

ይልቅ አንተም እንደ ወኅኒው ጠባቂ "እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብለህ?"ነፍስህን የምታድንበትን መንገድ ወደ መቅደሱ ቀርበህ ጠይቅ::

ወዳጄ ይህንን ጽሑፍ ያነበብኸውም በሕይወት ስላለህ ነው:: የአንተን ዓይን የሚጠብቁ ብዙ ጽሑፎች ፣ የአንተን ጆሮ የሚፈልጉ ብዙ ድምፆች ፣ የአንተን መሐረብ የሚፈልጉ ብዙ ዕንባዎች ፣ የአንተን ሳቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀልዶች ... ገና ብዙ ብዙ አሉ::

ስለዚህ ሰይጣንን አሳፍረው:: እንዲህ በለው :-

"ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ" ሚክ. 7:8

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 2016 ዓ.ም.
ሜልበርን አውስትራሊያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
16.3K views , 05:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-22 08:37:39 + በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ +

ይድረስ ለተከፋኸው ወንድሜ
መኖር ለደከመህ ፣ ሕይወት ለታከተህ ፣ የሚሰማህ ላጣኸው ፣ የሚረዳህ ሰው ላላገኘኸው መከረኛው ወዳጄ!

ከሞት ውጪ ሌላ መፍትሔ አልታይ ካለህ የአንተ ቢጤ መከረኞቹ ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት ውስጥ ሆነው እንዲህ ይሉሃል::

"በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ" ሐዋ. 16:28

አውቃለሁ ዙሪያው ገደል ሆኖብሃል:: ምነው ባልተፈጠርሁ እስክትል ድረስ ተጨንቀሃል::
ግን ይህ ስሜት በአንተ አልተጀመረም:: ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ኑሮ ያልመረረው ማን አለ? መሞት ያልተመኘስ ማን አለ?

ሞት ያማረህ አንተን ብቻ መሰለህ?

" ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ" ያለውን ጻድቅ ኢዮብ አልሰማህም? (ኢዮ. 10:18)

"ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ" ብሎ እንዲሞት የለመነውን ኤልያስን አላየኸውም? 1ነገሥ. 19:4

ዮናስንስ "አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ፡ አለው" ሲል አልሰማኸውም? (ዮናስ 4:3)

ወንድሜ እመነኝ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መኖር ያላስጠላው ሰው በታሪክ ፈልገህ አታገኝም::

ሞት ሞት የሸተተው ልቡ የተሰበረ ብዙ ነው:: አንተ ላይ ብቻ የደረሰ ልዩ ፈተና የለም:: "ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" ይላል መጽሐፍ:: 1ኛ ቆሮ. 10:13

ምናልባት የልብህን መሰበር የኀዘንህን ጥልቀት አይቶ ምቹ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ራስህን እንድትጎዳ ሰይጣን ሊገፋፋህ ይችላል:: እንዴት እንዲህ ዓይነት ሃሳብ በልቤ ሊመጣ ቻለ ብለህ አትረበሽ:: ሰይጣን ይህንን ክፉ ሃሳብ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስም አቅርቦለታል::

"የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር" ብሎ ክርስቶስን እንኳን [ማንነቱን ሳያውቅ] ራሱን እንዲወረውር ሊገፋፋው የሞከረ ደፋር ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ግን ራሱን አይጎዳም:: "ጌታ አምላክህን አትፈታተነው" "ሒድ አንተ ሰይጣን" ብለህ ሰይጣንን ገሠፀው::

ሰይጣን ክርስቶስን "ከሕንፃ ጫፍ በመወርወር የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አሳይ" ሲለው ክርስቶስ ሰይጣንን ሒድልኝ ብሎ በመገሠጹ በክብር ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ::
ወንድሜ ሆይ አንተም ሰይጣንን አትስማው ሃሳቡ ራስህን ጎድተህ ከፈጣሪህ እንድትጣላ ሊያደርግህ ነው:: ሰይጣንን ከገሠጽከው በእግዚአብሔር ቀኝ ከበጎቹ ጋር ትቆማለህ::

አሁን ያለህበት ችግር ያልፋል:: የሚሰማህ ክፉ ስሜት መቼም የማይለወጥ አይምሰልህ:: ኀዘኑም ፣ ብቸኝነቱም ፣ ተስፋ ቢስነቱም ያልፋል:: ጨለማው ይነጋል:: የተዘጋው በር ይከፈታል:: ችግሩ ሲፈታ አንተ ከሌለህ ግን ትርጉም የለውም::

ስለዚህ ለሚፈታ ችግር የማይቀለበስ ውሳኔ አትወስን:: ራስን ማጥፋት ከጊዜያዊ ችግር ለመሸሽ ሲሉ ዘላቂ ችግር ውስጥ መግባት ነው:: ጊዜያዊ ሕመምን ለማስታገስ የዘላለም ሕመምን ለምን ትመርጣለህ? "የሞተ ተገላገለ" ሲሉ ሰምተህ እንዳትታለል ሞት ዕረፍት የሚሆነው ራሱ እግዚአብሔር ሲጠራህ ብቻ ነው::
"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ" ያለው ጌታ ሳይጠራህ ራስን ማጥፋት የዘላለም ስቃይ ያመጣል::

ወዳጄ "በራስህ አንዳች ክፉ አታድርግ"

የሕይወትህን ዋጋ ታውቅ ይሆን? አንተ እኮ የእግዚአብሔር ልጅ ለአንተ ሲል የሞተልህ ነህ:: ሊፈውስህ የቆሰለ ፣ ሊያከብርህ የተዋረደ ፣ ሊያረካህ የተጠማ ፣ ሊያለብስህ የተራቆተ ለአንተ እኮ ነው::
ክርስቶስ ስለ አንተ ሞቶአል:: አንተን ግን የጠየቀህ እንድትሞትለት ሳይሆን እንድትኖርለት ነው::
ለሞተልህ አምላክ እንዴት መኖር ያቅትሃል?

ወዳጄ ሆይ ሰውነትህ በአምላክ ደም የተገዛ ክቡር ሰውነት ነው:: አካልህ "አንተ" እንጂ "ያንተ" አይደለም:: "በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ" ይላል

ስለዚህ በከበረ የእግዚአብሔር ልጅ ደም የተገዛ ሰውነትህን ለሰይጣን በርካሽ አትሽጠው:: አትግደል የሚለው ሕግ ራስህንም ይጨምራል:: ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነትህን ለማፍረስ አታስብ::
"ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ" 1ኛ ቆሮ. 3:17

ሰዎች አስቀይመውህ ይሆን?

"አሳያቸዋለሁ ፤ ስሞት የእኔን ነገር ይገባቸዋል" ብለህ በሰዎች ተቀይመህ ራስህን አትጉዳ:: እመነኝ ብትሞት ሰዎች ከሳምንት በላይ አያስታውሱህም:: ለሕይወትህ ዋጋ ያልሠጡ ሰዎች ለሞትህ ዋጋ አይሠጡም:: ፈጥነውም ይረሱሃል:: ለሚረሱህ ሰዎች ብለህ የማይረሳህን አምላክ አታሳዝን:: ሰው ስለ አንተ ግድ የለውም እግዚአብሔር ግን የራስህን ቁጥር ሳይቀር በቁጥር ያውቀዋል :: እንኳንስ ራስህን ልትጎዳ አንዲት ጸጉር እንኳን ከአንተ እንድትወድቅ አይፈልግም::

እግዚአብሔርን በኃጢአት ብታሳዝነው እንኳን ኖረህ ንስሓ እንድትገባ እንጂ እንድትሞት አይፈልግም:: አባትህ ነውና ከእርሱ ጋር ባትሆንም እንድትኖር ይፈልጋል:: በምሳሌ ልንገርህ :-

ሁለት ሴቶች አንድን ሕፃን "የኔ ልጄ ነው" ብለው እየተከራከሩ ጠቢቡ ሰሎሞን ፊት ቀረቡ:: ጠቢቡ ሰሎሞን ሰይፍ አመጣና "ልጁን ቆርጬ ለሁለት ላካፍላችሁ" አላቸው:: አንደኛዋ ሴት "እሺ እንካፈል" ስትል እውነተኛዋ እናት ግን "ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው" አለች:: እናት መሆንዋም በዚህ ታወቀ::

ወዳጄ ያንተም ኑሮህ ከእግዚአብሔር ጋር ላይሆን ይችላል:: ዓለም የራስዋ አድርጋህም ይሆናል:: በሱስ ውስጥ ትዘፍቀህ ፣ እንደ ሶምሶን በደሊላ እቅፍ ፣ እንደ ዴማስ በተሰሎንቄ ውበት ተማርከህ ይሆናል:: እግዚአብሔር ግን አባትህ ነውና ሞትህን አይፈልግም::

"ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው" እንዳለችው እናት ፈጣሪህ ከነኃጢአትህም ቢሆን እንድትሞት አይፈልግም:: ከእርሱ ጋር ባትኖርም መኖርህን ይፈልጋል:: "የሟቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ" ሕዝ. 18:32

የይሁዳ ኃጢአቱ ጌታውን መሸጡ አልነበረም:: ራሱን መግደሉ ነው:: እግዚአብሔር የሚያዝነው ከበደልህ በላይ በእርሱ ተስፋ ቆርጠህ ራስህን ስትጎዳ ነው::

ወዳጄ የአንተን መኖር የሚፈልጉ ብዙ ናቸው:: ፈጣሪ ወደዚህች ዓለም ያለ ምክንያት አላመጣህም:: በአንተ አለመኖርም የሚጎድል ነገር አለ:: አንተን የሚመስል ሌላ ሰው አልፈጠረምና ለዚህ ዓለም አንተን የሚተካ የለም:: በክብር ወደዚህ ዓለም ያመጣህ አምላክ በክብር ወደራሱ እስኪወስድህ ድረስ "በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ"

"የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።
ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፡ ብሎ ጮኸ" ሐዋ. 16:27-28

ይህ ሰው እስረኛ ያመለጠ መስሎት ራሱን ሊያጠፋ ሲል ጳውሎስ "ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ" አለው::

ወዳጄ አንተስ ተስፋ የቆረጥኸው ምን ያመለጠ መስሎህ ነው?
15.7K views , 05:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-11 11:11:32 https://www.sbs.com.au/language/amharic/am/podcast-episode/interview-with-deacon-henok-haile/1g7smygir
13.4K views , 08:11
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-10 13:19:55 "ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው:: እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች" ምሳ. 31:30

ቅድስት አርሴማን የምናመሰግናት ለዚህ ነው:: ቅድስት አርሴማ (St. Hripsime) በውበትዋ ምክንያት እስከ ሰማዕትነት ድረስ የደረሰች ቅድስት ናት:: በውበትዋ ከተማረከው ከንጉሥ ዲዮቅልጢያኖስ ሸሽታ ወደ አራራት ተራራ ስትሸሽ የአርማንያው ንጉሥ ድርጣድስ (Drtad) ያሳደዳትና እስከ ሰማዕትነት የበቃችው በሚያልፈው ውበት የማያልፈውን አምላክ ላለማጣት ነበር::

ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን

"ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም" ያለው ቃል ቅድስት አርሴማን አይመለከትም:: ዕብ. 12:4 እርስዋ ከኃጢአት ጋር ደም እስከማፍሰስ ተጋድላለች::
ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔር የምትፈራ አርሴማ ግን ትመሰገናለች::
14.2K views , 10:19
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-05 10:09:06 + አባቶቻችን እንዲህ አሉ +

"እሳትና ውኃን ማዋሐድ እንደማይቻል በሌሎች ኃጢአት መፍረድም በራስ ኃጢአት ከመጸጸት ጋር አብሮ አይሔድም" ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

"የማያማትብ እጅ ቀኙም ግራውም አንድ ነው" አባ ፓስዮስ ዘደብረ አቶስ

"እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰው ያለው ፍቅር
ጻድቅ ሰው ለእግዚአብሔር ካለው ፍቅር ይበልጣል"
አባ አርሳኒ

"ሕፃን ልጅ እናቱ ስታጥበው ያለቅሳል:: ሕፃን እምነት (ትንሽ እምነት) ያላቸው ሰዎችም ነፍሳቸውን የሚያጥብ መከራ ሲመጣባቸው እግዚአብሔርን ያማርራሉ" አባ ስምዖን

"ዕለትን የሠጠህ እርሱ ለእለት የሚበቃህንም ይሠጥሃል" ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ

"እጅግ ምርጡ ጸሎት "ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ የፈቀድከውን አድርግልኝ" ማለት ነው"
ባሕታዊ ቴዎፋን

"ሲያመነዝር ያየኸውን ሰው አንተ ንጹሕ ብትሆንም አትናቀው:: ምክንያቱም አታመንዝር ያለው ጌታ አትፍረድም ብሏል" አባ ቴዎዶር

"አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ብታይ እንኳን አትፍረድበት:: አንዳንዴ ዓይንህም ሊሳሳት ይችላል"
ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

"ለኃጢአተኛው ክንፍህን ዘርጋለት:: ኃጢአቱን ልትሸከምለት ባትችል እንኳን ሸፍንለት"
ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ

ከአበው አንዱን ትሕትና ምንድርን ነው? ብለው ጠየቁት:: እርሱም "ትሕትና ማለት ወንድምህ በበደለህ ጊዜ እርሱ ይቅርታ ሳይጠይቅህ በፊት ቀድመህ ይቅር ማለት ነው" አለ::

"ይቅር ካላልክ ገነትም ይቅርብህ" አባ ኤፍሬም አረጋዊ [ If you don’t forgive, forget heaven]

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 22 2013 ዓ ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
23.6K views , 07:09
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-02 16:48:42
"እግዚአብሔር ብፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን"

ባሕርያት (Elements) ለዚህ ዘመን ክርስቲያን ወጣቶች የተበረከተ እጅግ ውብ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነው:: ይህ ውድ መጽሐፍ አምስት ቅጽ ያላቸው እጅግ የተዋቡ መጻሕፍት ውሕድ ሲሆን በዘመናዊው ዓለም እግዚአብሔርን በመምሰል ሕይወትን እንዴት መለማመድ እንደሚቻል የሚያሳይ በዳያስፖራነት የተወለዱ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ሕይወት የለወጠ እና በብዙ ሺህዎች ኮፒ የተሸጠ መጽሐፍ ነው::

የዚህን መጽሐፍ የመጀመሪያ ቅጽ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አማርኛ የተረጎምሁት ሲሆን እስከ ኅዳር ማርያም የአርታኢያንን ዱላ ቀምሶ በኅትመት ቤት አልፎ ከእጃችሁ ይገባል:: የቀሩትም መጻሕፍት በወራት ልዩነት ውስጥ ይከተላሉ::

N.B. የዛሬ ዓመት ገደማ ሊወጣ መንገድ ጀምሮ የነበረው "ሉተርና ሚካኤል" የተሰኘ መጽሐፍ በታላላቅ አባቶቼና ወንድሞቼ በሳል ምክር ምክንያት ከይዘቱ የተነሣ የሚወጣበትን ምቹ ጊዜ እየጠበቀና ተከድኖ እየበሰለ ያለ መሆኑን እገልጻለሁ::

"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን" 2ኛ ቆሮ. 2:14
13.8K views , 13:48
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-02 11:23:01 + ረቢ ወዴት ትኖራለህ? +

ከመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ "የእግዚአብሔር በግ እነሆ" የሚለውን የመምህራቸውን ስብከት ሰምተው ጌታን ተከተሉት::

"ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ" ዮሐ. 1:37-39

ጌታን ተከትለው የሚኖርበትን ካዩት ደቀ መዛሙርት አንደኛው ስም እንድርያስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የራሱን ስም በወንጌሉ ላይ እኔ የማይጽፈውና ቤተ ክርስቲያን ግን የራሱን ነገር ሲገልፅ በሚጠቀመው ቋንቋ የምታውቀው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነበረ::

"ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ" የሚለው ቃል በእርግጥ በጣም አስገራሚ ነው:: የክርስቶስን መኖሪያ ማየት መፈለጋቸው ፈልገው እንዳያጡት አድራሻውን ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ነበረ::
ሆኖም ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ቋሚ አድራሻ አልነበረውም:: ራሱ እንደተናገረ :-ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" (ማቴ. 8:20)

እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የጠየቁት "ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?" የሚለው ጥያቄ አድራሻ ከመጠየቅ ከፍ ያለ ጥልቅ ጥያቄ ነው:: ነቢያቱ "የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው?" ብለው የተጨነቁለት የጥበብ ክርስቶስ ማደሪያ የት እንደሆነ ማወቅ የነፍስ ዕረፍት ነውና ተራ ጥያቄ አይደለም?
ይህ ጥያቄ ዳዊት ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹ ዕረፍት ያልሠጠበት "የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስኪያገኝ ድረስ" የለመነበት ጥያቄ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? የሚለው ጥያቄ እንድርያስና ዮሐንስ በአንድ ቀን ብቻ የሚመለስ ጥያቄ መስሎአቸው አብረውት ሔደው አብረውት ዋሉ እንጂ የጌታ መኖሪያ ግን ያን ቀን የዋለበት ብቻ አይደለም::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ" መዝ. 43:3

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? "ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች" መዝ. 139:8 ለአድራሻ የሚያስቸግረው የረቢ መኖሪያው ብዙ ስለሆነ የት ትኖራለህ ለሚለው ጥያቄ መልሱ "መጥታችሁ እዩ" ብቻ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ብለው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ቦታውን ከመናገር ይልቅ "መጥታችሁ እዩ" ያለው ጌታ እርሱን ጸንተው እስከተከተሉ ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አልፎም ከሞቱ በኋላ የሚያዩት ብዙ መኖሪያ ስላለው ነበር::

የረቢ መኖሪያው ብዙ ነው:: "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡ ወደ እርሱም እንመጣለን፡ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" እንዳለ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ሰውነትም የእርሱ ማደሪያ ነው:: (ዮሐ. 14:23)

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? " በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና" ስትል ሰምተንህ ነበር:: (ዮሐ. 14:2) የአንተ መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ሲል እንደሰማነው እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ እንደመዋል ዐሥሩ መዓርጋት ላይ የደረሱ በጽድቅ መንገድ የሔዱ የሚያዩት ማደሪያህ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? መጥተን ለማየት "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" እስክትለን በተስፋ እየጠበቅን አይደለምን?

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ካሉት ጠያቂዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ዮሐንስ ያያቸው የረቢ መኖሪያዎች ከገሊላ እስከ ታቦር ተራራ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ፣ ከወንጌል እስከ ራእይ እጅግ ብዙ እንደነበሩ ታየኝ::

"ወዴት ትኖራለህ?" ብሎ ጠይቆ ጌታን የተከተለው ዮሐንስ "መጥተህ እይ" በተባለው መሠረት የጌታን መኖሪያ የእርሱን ያህል ያየም ሰው የለም::

ዮሐንስ "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" ለሚል ጥያቄው ግን አንጀት የሚያርስ ልብ የሚያሳርፍ መልስ ያገኘው አርብ ዕለት መስቀሉ ሥር ነበር:: ወዴት ትኖራለህ? ላለው ዮሐንስ የዘጠኝ ወር ከተማውን የዘላለም ማረፊያውን "እነኋት እናትህ" ብሎ ሲሠጠው መጥቶ ካያቸው የረቢ መኖሪያዎች ሁሉ የምትበልጠውን መኖሪያ አየ:: "እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ" ብሎ የመረጣትን ማደሪያ ከማየት በላይ ምን ክብር አለ? (መዝ. 132:13)

ዮሐንስ ይህችን የረቢ መኖሪያ ወዲያው ወደ ቤቱ ወሰዳት:: ዮሴፍ ሊወስዳት ስላልፈራ ምን እንዳገኘ ያውቃልና እርሱም ይህችን የዕንቁ ሳጥን ወደ ቤቱ ወስዶ ቢዝቁት የማያልቅ ጸጋን ተጎናጸፈ::

ጌታ እናቱን ለዮሐንስ መሥጠቱ የሁለት ድንግልናዎች ማስረጃ ሆነ:: የድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናም የዮሐንስ ድንግልናም በጌታ ንግግር ታወቀ::

አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ድንግል ማርያም ከጌታ ሌላ ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ "እናቴን ከልጆችዋ ነጥለህ ወደ ቤትህ ውሰዳት" "አንቺም ልጆችሽን ይዘሽ ወደ ሰው ቤት ሒጂ" ብሎ ለዮሐንስ አይሠጣትም ነበር:: ድንግል ማርያም የአብን አንድያ ልጅ አንድያ ልጅዋ አድርጋለችና አምላክ ባደረበት ዙፋን ሌላ ፍጡር ያላስቀመጠች የአምላክ ብቸኛ ዙፋን ፣ እግዚአብሔርን አስገብታ በርዋን የዘጋች ዘላለማዊት ድንግል መሆንዋ ለዮሐንስ በመሠጠትዋ ታወቀ:: ዮሐንስም ቤት ንብረት የሌለው መናኝ ባይሆንና ሚስት ድስት ያለው ሰው ቢሆን ድንገት ወደ ቤቱ ይዞአት እንዲሔድ እናቱን ባልሠጠው ነበር::

የሰው ልጅ ድኅነት ታሪክ በሁለት "እነሆ"ዎች መሃል መከናወኑ እጅግ ይደንቃል:: የሰው መዳን የተጀመረው "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ብላ ራስዋን ለፈጣሪ በሠጠችው ድንግል ቃል ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ "እነኋት እናትህ" ብሎ በደም በታጠበ አንደበቱ በነገረን የኑዛዜ ቃል ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ለእኛም አታሳየን ይሆን? እስከ ዐሥር ሰዓት መዋል ፣ ዐሠርቱን ትእዛዛትህን ፣ ዐሥሩን የቅድስና ደረጃዎችን መውጣት ላቃተን ለእኛስ መኖሪያህን ታሳየን ይሆን? መጥታችሁ እዩ የሚለውን ጥሪ ሰምተን ለማምጣት አቅም ላነሰን መጻጉዕዎች ፣ ዓይን ላጣን በርጤሜዎሶች ተነሡ እዩ ብለህ መኖሪያህን አታሳየን ይሆን? መቅደስህን እንመለከት ዘንድ ፣ መኖሪያህን መንግሥትህን እናያት ዘንድ ፣ ዮሐንስ ያያትን መኖሪያህ እናትህን እናይ ዘንድ እንመኛለን::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 21 2016 ዓ.ም.
ለእመብዙኃን ዝክር የተጻፈ

"ንዒ ማርያም ለዕውር ብርሃኑ
ወንዒ ድንግል ለጽሙዕ አንቅዕተ ወይኑ
ኦ ኦ ተኃድግኒኑ ኦ ኦ ትመንንኒኑ
ኀዘነ ልብየ እነግር ለመኑ"
ወተዘከርኒ ለኃጥእ ገብርኪ ተክለ ማርያም
14.7K views , 08:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-10-02 08:39:08 + መርጦ መወለድ +

ከእገሌ ልወለድ ብሎ መርጦ የተወለደ የለም:: ምረጡ ብንባል ምን ዓይነት ወላጅ እንመርጣለን? ቀድመን የመገምገም ዕድል ቢኖረን ምን ዓይነት ወላጆች እንመርጣለን። መቼም በወላጆቼ ደስተኛ ነኝ የሚል ሰው "እኔ ደግሜም ብወለድ ከአባዬ ከእማዬ ነው መወለድ የምፈልገው" ማለቱ አይቀርም። ግን ደግሞ ዕድሉን ቢያገኝ መቼም ትንሽም ቢሆን የሚያስተካክለው ነገር አይጠፋም። መርጦ መወለድ አይቻልም እንጂ ቢቻል የምንመርጠው ልዩ ምርጫ ይሆናል።

መርጦ የተወለደ ክርስቶስ ብቻ ነው። በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ተመልክቶ መዓዛዋን መርጦ ፣ በቅድስናዋ ውበት ተማርኮ ከእርስዋ ሊወለድ የመረጣት የተመረጠች እናት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። የፈጣሪ ምርጫ እንደ ሰው አይደለም። ሰው ፊትን ያያል እርሱ ግን እስከ ልብ ድረስ ዘልቆ ይመለከታል። እንዴት ብትነጻ ፣ እንዴት ብትቀደስ ነው? እስከ ውስጥዋ ዘልቆ አይቶ ከእርስዋ ሊወለድ የመረጣት? ንጉሥ ውበትዋን የወደደላት ፣ ለእናትነት የመረጣት ቅድስት እንዴት የከበረች ናት?
አዎ መርጦ የተወለደ የለም ፣ ክርስቶስ ግን መርጦ ብቻ ሳይሆን ፈጥሮ የተወለደ ነው። መቅደሱን አንጾ የገባባት እርሱ ነው። መርጦ ለተወለደብሽ ለአንቺ በጸጒራችን ቁጥር ምስጋና እናቀርባለን።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 21 2012 ዓ ም
የግሸንዋን ንግሥት በረከት በመናፈቅ
ሜልበርን አውስትራሊያ
13.8K views , 05:39
ክፈት / አስተያየት ይስጡ