2023-09-28 19:20:09
+ የመስቀሉ ደም +
መስቀል ደም አለው ወይ? ከእንጨት የተሠራ ነገር ቢወጉት ይፋፋቅ ይሆናል እንጂ አይደማም::
ስለ ክርስቶስ መስቀል ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር ግን "በመስቀሉ ደም ሰላምን አደረገ" አለ:: (ቆላ. 1:20)
"ወገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ"
የመስቀሉ ደም የሚለው ቃል መስቀሉ ደምቶአል ለማለት አይደለም:: ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ጠዋት ሦስት ሰዓት ሊቶስጥራ ላይ ጌታን ሲያሸክሙት የመስቀሉ ቀለም የእንጨት ብቻ ነበረ:: ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ ለሦስት ሰዓታት ከወጣና ለሦስት ሰዓት ተሰቅሎ ነፍሱን ከሠጠ በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋውን ከመስቀሉ ሲያወርዱት የመስቀሉ መልክ የእንጨት አልነበረም:: በጥሩ ባለሙያ ቀይ ቀለም የተቀባ እስኪመስል ድረስ መስቀሉ በክርስቶስ ደም ታጥቦ ነበር:: እሾህ ከደፋው ራሱ ፣ ከተቸነከሩት እጆቹ ፣ ከተገረፈው ጀርባው ፣ ሚስማር ከያዛቸው እግሮቹ እንደ ውኃ የፈሰሰው ደም በመስቀሉ ላይ ፈስሶ ነበር::
መፍሰስን ለመግለፅ በግእዝ ሁለት ቃላት አሉ "ክዒው" እና "ውኂዝ" የሚሉ:: ወደ አማርኛ ሲመለሱ ሁለቱም መፍሰስ ቢሆኑም ግን ልዩነት አላቸው:: አንድ ሰው በብርጭቆ ውኃ ቢያፈስስ ውኃው ፈሰሰ ይባላል:: የወንዝ ውኃ ሲፈስስም ፈሰሰ ይባላል:: ግእዙ ግን ከአንድ ብርጭቆ ለሚፈስሰው ውኃ "ተክዕወ" ሲል እንደ ወንዝ ላለው ብዙ ፈሳሽ ደግሞ "ውኅዘ" ብሎ ይለየዋል::
ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕታት ስለ ክርስቶስ ብለው አንገታቸው ተሰይፎ እንደሞቱ ሲናገር "ወከዓዉ ደሞሙ በእንተ መንግሥተ ሰማያት" "ስለ መንግሥተ ሰማያት ደማቸውን አፈሰሱ" ይላል::
ይኸው አባት ቅዱስ ኤፍሬም ስለ ክርስቶስ ደም መፍሰስ ሲናገር ግን "በውኂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሖሙ ለመሃይምናን" "በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ያመኑትን አነጻቸው" ብሎአል:: የጌታችንን ደም መፍሰስ ለወንዝ ፈሳሽ በሚነገርበት ቃል ውኂዝ የተባለው ከጌታችን የፈሰሰው ደም ከመላው ሰውነቱ ስለነበረ ነው::
መስቀሉን ለዓመታት መፈለግ ፣ ማክበር ግድ የሆነውም መስቀሉ ዓለም በተገዛበት በከበረ ደም ስለተቀደሰ ነው:: (እስመ ተቀደሰ በደመ ክርስቶስ መድኅን)
ወዳጄ ሆይ በደም የታጠበ መስቀል ስታይ ምን ይሰማሃል? በደም የተቀደሰው የመስቀሉ ክብር አይታይህም? አዎ መስቀል ክቡር ነው::
የመስቀሉ ደም ሌላ የሚያሳየው ክብርም አለ:: እርሱም የእኔና የአንተን ክብር ነው:: ምክንያቱም ያ ሁሉ ደም የፈሰሰው ለእኔና ለአንተ ነው:: በሰዎች የመጠሪያ ስምህ ማን ነው? ማን ብለው ሲጠሩህ አቤት ትላለህ?
ቅዱስ ጳውሎስ ግን ለእኔም ለአንተም ስም አውጥቶልናል:: ጳውሎስ አንተን ለሰዎች ሲያስተውቅህ እንዲህ ብሎ ነው :-
"ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው" 1ቆሮ.8:11
ወዳጄ የአንተ ክብር እዚህ ድረስ ነው:: አንተ ክርስቶስ የሞተልህ ወንድም ነህ:: አንቺ ክርስቶስ የሞተልሽ እኅት ነሽ::
ቅዱስ ጴጥሮስ ጨምሮበታል :-
"በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ" 1ኛ ጴጥ. 1:18-19 ቅዱስ ያሬድም "አኮ በወርቅ ኃላፊ ዘተሳየጠነ አላ በደሙ ክቡር ቤዘወነ" ብሎ ዘምሮታል::
የእኔና አንተ ዋጋ በወርቅ በብር የሚመዘን አይደለም:: ዋጋችን በመስቀል ላይ የፈሰሰው ክቡር ደም ነው::
ጌታ "መላእክቶቻቸው የአባቴን ፊት ያያሉና ማንንም እንዳትንቁ" ብሎ ነበር:: (ማቴ.18:10) ሰውን ስለ መልአኩ ብለን እንዳንንቅ ከተነገረን ስለፈሰሰለት ደምማ ምንኛ ልናከብረው ይገባን ይሆን?
ውድ ክፍያ ተከፍሎ ልብስ የተገዛለት ልጅ ልብሱን ስለተከፈለበት ዋጋ ሲል ተጠንቅቆ ይለብሰዋል:: በውድ የተገዛ ዕቃ የተሠጠው ሰው በጥንቃቄ ይጠቀምበታል:: የእኛ ሰውነት ግን የተገዛው በአምላካዊ ደም ነው:: እንደተከፈለልን እየኖርን ይሆን?
ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ብሔራዊ ቴአትር ጋር ያለውን ሐውልት እጅግ በውድ ዋጋ አሠርተው ነበር ይባላል:: ንጉሡ የአንበሳ ሐውልት ሊመርቁ ሲከፍቱ ግን ሐውልቱ አንበሳ አይመስልም:: የአንበሳና ቀጭኔ ዲቃላ መስሎ ጉብ ብሎአል:: ንጉሡ አንጀታቸው እያረረ ከመረቁ በኋላ ንግግር ሲያደርጉ "ይህ አንበሳ አንበሳ ባይመስልም የወጣበት ገንዘብ ግን አንበሳ ያደርገዋል" አሉ ይባላል::
የእኛም ሕይወት እንደዚያ ነው:: ስንታይ ምናችንም ክርስቶስን አይመስልም:: አንዳንዴም በክፋት ከሰውነት ተራ እንወርዳለን:: ሆኖም እንዲህ ብንበድልም "ክርስቶስ የሞተልን ነን"
ምንም እንኳን ክርስቲያን ባንመስል የተከፈለልን ደም የክርስቶስ ያደርገናል:: ምንም እንኳን የከበረ ሕይወት ባይኖረንም የፈሰሰልን ክቡር ደም ክቡራን ያደርገናል::
"በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ"
1ኛ ቆሮ.6:19
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 17 2016 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
18.7K views , 16:20