Get Mystery Box with random crypto!

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የሰርጥ አድራሻ: @deaconhenokhaile
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 64.23K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ቻናል በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ፈቃድ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ነው::
@deaconhenokhaile
"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን"
2ኛ ቆሮ. 2:14

Ratings & Reviews

2.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 9

2023-05-27 18:24:59 ለነገሩ ለወላዋዩ ናቡከደነፆር ምን መልስ ይሠጣል፡፡ ታሪኩን ስናነብ እንደ ናቡከደነፆር ተገለባባጭ ሰው የለም፡፡ ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት ላይ ለፈጣሪ መሰከረ ፣ ምዕራፍ ሦስት ላይ ካደ ፣ ምዕራፍ ሦስት መጨረሻ ላይ አምኖ መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጀመሪያ ላይ ለፈጣሪ እንደ መዘመር ቃጣው በሕልሙ መልአክ እስከማየት ደርሶ ስለ ፈጣሪ ኃያልነት መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጨረሻ ላይ ግን ‹‹ይህች በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?›› ብሎ ተኮፍሶ እንደ እንስሳ ሣር እስኪግጥ ድረስ ተቀጥቷል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹አምላካችሁ ማን ነው?› ሲላቸው መልስ ልንሠጥህ አያስፈልገንም ፤ አንተው ማን እንደሆነ ሣር ስትግጥ ታየዋለህ አሉት፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው ያሉ እነፈርኦን የደረሰባቸው ባይገባህ አንተ ላይ ደርሶ ታየዋለህ ሲሉ ‹እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም› አሉት፡፡

ሦስቱ ወጣቶች አምላካችሁ ማን ነው የሚለውን ባይመልሱም ይህንን ግን አሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ አምላካችን ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል› ንጉሥ ሆይ አምላካችን ኃይሉ ከእሳት በላይ ነው፡፡ ያለ እሳት ማንደድ ያለ ውኃ ማብረድ ይችላል፡፡ ከእሳቱ ያድነናል ፤ ‹ከእሳቱ ቢያድናችሁ ምን ዋጋ አለው ፤ ከእሳት ብታመልጡ ከእኔ አታመልጡም› ብለህ ታስብ እንደሆን ‹‹ከእጅህም ያድነናል›› አሉት፡፡

‹‹ነገር ግን ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነንም አማልክትህን እንደማናመልክ እወቅ›› አሉት፡፡ ወጣቶቹ ‹ባያድነንም› ያሉት ተጠራጥረው አይደለም፡፡ ለጣዖት ከመስገድ ሞት ይሻለናል ፣ ለጣዖት በመስገድ የምንጎዳው ጉዳት በእሳት ተቃጥለን ከምንጎዳው አይብስም ፣ የዘላለም እሳት ከሚፈጀን የአንተ እሳት ቢፈጀን እንመርጣለን ለማለት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሦስቱ ወጣቶች ‹ያድነን ዘንድ ይችላል› አሉ እንጂ ‹እንድናለን› አላሉም፡፡ የፈጣሪያቸውን የማዳን ኃይል በእርግጠኝነት ተናገሩ እንጂ ከዚህ እሳት እንደሚድኑ በእርግጠኝነት አልተናገሩም፡፡ ይህም ከትሕትናቸው የተነሣ ነበር፡፡ እግዚአብሔር መላእክቱን ስለ እኔ ያዝዝልኛል ያድነኛል ብሎ ወደ ሞት ራስን መሥጠት ጌታችን ለዲያቢሎስ እንዳለው ጌታ አምላክን መፈታተን ነው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹ባያድነን እንኳን› ሲሉ ምግባራችን ከልክሎት ባያድነን እንኳን ያልዳነው በኃጢአታችን ነው እንጂ አምላካችን ማዳን ተስኖት እንዳይመስልህ አሉት፡፡

እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ያስደንቃሉ ፤ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባልተሰበከበት በዚያ ዘመን ፣ ምንም እንኳን ሥቃይ የማይነካቸው ቢሆንም እንኳን ጻድቃንም ቢሆኑ ወደ ሲኦል በሚወርዱበት በዚያ ዘመን ተስፋ ሳይኖር ተስፋ አድርገው እንደ ሐዲስ ኪዳን ሰው ወደ ሞት የሔዱት እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ክቡራን ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰማዕቱ ዮስጦስ (Justine the martyr) ‹‹ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች›› (Christians before Christ) የሚላቸው፡፡

★ መርጦ የሚያነድ እሳት ★

ናቡከደነፆር በወጣቶቹ መልስ እጅግ ተበሳጨ ፤ የሚነድደውን እሳት ሰባት እጥፍ እንዲያደርጉት አዘዘ፡፡ ልፋ ሲለው ነው እንጂ እሳቱ ሰባት እጅም ቢሆን ፣ አንድ እጅም ቢሆን ለሦስቱ ወጣቶች መቃጠል ያው መቃጠል ነው፡፡ የባቢሎንን ማገዶ ከማባከን በቀር ሦስቱ ወጣቶች የሚሞቱት ሞትም ያው አንድ ሞት ነው፡፡ የተፈለገው ግን እንዲፈሩ ነበር፡፡ ሰይጣን አሠራሩ እንዲህ ነው ፤ እምነታችን ሲጨምር እሳቱ ሰባት እጥፍ ይጨምራል፡፡ ‹ያድነናል› የሚለው ምስክርነታችን ናቡከደነፆሮችን ያስቆጣል፡፡ በሥልጣናቸው የሚነድደውን እሳት መጨመር እንጂ የእኛን እምነት መቀነስ አይችሉም፡፡ ሦስቱን ወጣቶች ከሰናፊላቸው ፣ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸው ከቀረው ልብሳቸውም ጋር እንዲታሠሩ ተደረገ፡፡ ያ ሁሉ ልብስ አብሮአቸው እንዲታሰር የተፈለገው ሥቃያቸውን የበለጠ ለማብዛት ፣ እግራቸው መታሰሩም ሳይንፈራገጡ እንዲቃጠሉ ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱን ወጣቶች ወደ እሳት ጨመሯቸው፡፡ ከእሳቱ ኃይል የተነሣ ‹የጣሏቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው›

ሦስቱን ወጣቶች እሳት ውስጥ ሲገቡ ከእስራቸው ተፈትተው ሲመላለሱ ታዩ ፤ ናቡከደነፆር ባላዋቂ አነጋገር ‹የአማልክት ልጅ› ያለውን ‹የእግዚአብሔር ልጆች› ተብለው ከሚጠሩት መላእክት አንዱ የሆነውን መልአኩን ልኮ የእሳቱን ኃይል አጠፋ፡፡ ‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሠፍራል ያድናቸውማል› የተባለውም ተፈጸመ፡፡ ‹የአማልክት ልጅ› የተባለው የመልአኩ መውረድ የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ፣ የመምጣቱና የሰውን ልጅ ከሲኦል እሳት የማዳኑ ሥራ ምሳሌ ሆኖ ይኖራል፡፡

ሦስቱ ወጣቶች ልብስ አልብሰው የጨመሯቸው እንዲሰቃዩ ነበር ፤ ሆኖም ለሥቃይ የለበሱት ልብስ ለዝማሬ ሆናቸው፡፡ መቼም ዕርቃን ሆኖ ዝማሬ የለም፡፡ አልብሰው ባይከቷቸው ኖሮ ሲወጡ ዕርቃናቸውን በወጡ ነበር፡፡ የሚያስደንቀው እነዚህ ሦስት ዕፀ ጳጦሶች እንኳን ሊቃጠሉ ጭስ ጭስ እንኳን አይሉም ነበር፡፡
የባቢሎን እሳት አስደናቂ እሳት ነው፡፡ ከእሳቱ ውስጥ እያሉ እሳቱ ያቃጠለው የታሰሩበትን ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ የጣሏቸውን ሰዎች ወላፈኑ ገደላቸው፡፡ ሰዎችን ወደ እሳት መገፍተር ቀላል ነው፤ እሳቱ ግን ገፍታሪዎቹን ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ‹‹እሳት በላዒ ለአማፅያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ፤ ወእሳት ማኅየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ›› (ስሙን ለሚክዱ ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው ፤ፈቃዱን ለሚሠሩ ልባቸው ለቀና የሚያድን እሳት ነው) የሚለው የአባ ሕርያቆስ ቅዳሴ በብሉይ ኪዳን ቢሆን ለባቢሎን እሳት ይሠራ ነበር፡፡

ሦስቱ ወጣቶች እሳት ውስጥ ገብተው የመውጣታቸው ታሪክ በጥላቻና በዘረኝነት እሳት እየነደድን ባለንበት በዚህ ዘመን ሆነን ስንመለከተው መልእክቱ ብዙ ነው፡፡ በሚነድደው እሳት ላይ የእያንዳንዳችን ድርሻ ምንድር ነው? አንዳንድ ሰው ‹ይለይለት ካልደፈረሰ አይጠራም› ይላል፡፡ በስድብ በጥላቻ በነቀፋ ከሩቅም ከቅርብም ሆኖ የሚያባብስ ሰው እንግዲህ እሳቱን ሰባት እጥፍ ከሚጨምሩት የናቡከደነፆር አሽከሮች አይለይም፡፡ በዚያ ላይ ይለይለት ብለህ የምትጨምረው እሳት ወላፈኑ አንተኑ ማቃጠሉ አይቀርም፡፡ ያለነውም የምንኖረውም እሳቱ ውስጥ ሆነው ‹‹የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል›› ብለው በሚጸልዩ ሰዎች ነው፡፡ ጸሎት መፍትሔ ነው ሲባል በሚያስቀን በናቡከደነፆሮች ሳይሆን ዳዊቱን በማያስታጉሉ አናንያ አዛርያና ሚሳኤሎች ነው፡፡

እሳት ውስጥ ገብተው የወጡት እነዚህ አርበኞች ከጸሎቱ ባሻገር አንድ ልብ ነበሩ፡፡ በሙሉ ትንቢተ ዳንኤል ላይ ‹አናንያ እንዲህ አለ ፤ አዛርያም እንዲህ አለ› የሚል አልተጻፈም፡፡ ሦስት ሲሆኑ እንደ አንድ ሰው ሲናገሩ ሲሰሙ ፣ አብረው ሲጾሙ ፣ አብረው ሲሾሙ ፣ አብረው ሲታሰሩ ፣ አብረው ከእሳት ሲገቡ አብረው ሲወጡ ፣ አብረው ሲዘምሩ ነው ያየናቸው፡፡ አንድ ልብ ሳይሆኑ ከእሳት መውጣት አይቻልም፡፡ አናንያና አዛርያ ተፋቅረው ሚሳኤልን ቢጠሉት ኖሮ በሃሳብ ባይስማሙ ኖሮ ተቃጥለው ይቀሩ ነበር፡፡ ‹‹መልአኩን የላከ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የአናንያ የአዛርያ የሚሳኤል አምላክ ይባረክ›› (ዳን. 3፡28)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 19/2011 ዓ.ም.
ኦስሎ ኖርዌይ
22.6K views , 15:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-27 18:24:58 + ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች +
++++++++++++++++++++++++++++

. የቆሎ ተማሪዎች

ንጉሥ ናቡከደነፆር እስራኤልን ድል ነሥቶ በግዞት ወደ ባቢሎን በወሰዳቸው ጊዜ ሕዝቡን ለአመጽ እንዳያነሣሡበት ከነገሥታትና መሳፍንት ወገን የሆኑትን ፣ መልከ መልካሞቹን ፣ ወጣቶቹንና ብሩሕ አእምሮ ያላቸውን መርጦ ከሕዝቡ ለይቶ በቤተ መንግሥቱ ሰበሰበ፡፡ ዓላማው ወጣቶቹ የሀገሩን ቋንቋ ከተማሩና በቤተ መንግሥት በምቾት ከኖሩ የወገኖቻቸው መከራ እንደማይሰማቸው በማሰብ ነበር፡፡ ከሰው ልጅ የሚበዛው እርሱ እስከተመቸውና ጥቅሙ እስካልተነካበት ድረስ የሌላው ወገኑ ጩኸት ስለማይሰማው ናቡከደነፆር እስራኤልን ለማፈን የተጠቀመው አደገኛ ስልት ነበረ፡፡ ይህ ስልት ግን በሦስቱ ወጣቶች በአናንያ በአዛርያና ሚሳኤል ላይ አልሠራም፡፡ ገና ከጅምሩ በቤተ መንግሥት የቀረበላቸውን ‹ጮማና ጠጅ አንበላም ጥሬ ይሠጠን› ብለው በድብቅ ‹የቆሎ ተማሪዎች› ሆኑ፡፡

መቼም የቤተ መንግሥትን እንጀራ አንዴ አትልመደው እንጂ የለመድከው እንደሆነ ንጉሡ ምንም አድርግ ቢልህ ታደርጋለህ፡፡ የቤተ መንግሥት ምግብ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ እንጀራ ተከትሎት ሄደ›› ተብሎ እንደተጻፈ እንኳን የናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ምግብ ይቅርና የንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥት ምግብም እንደ ኦርዮ ሞትን ሊያስከትልም ይችላል፡፡ ከቤተ መንግሥት የሚሠጥህን ምግብ አገኘሁ ብለህ ደስ ቢልህም ያ ምግብ የመጨረሻ ራትህ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ነገ ክፉ ነገር አድርግ ቢሉህ እምቢ ለማለት ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ጥሬ ቆርጥመው ሊማሩ ወሰኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሦስቱን ወጣቶች ከንጉሡ ጋር የሚያጋፍጥ ነገር የመጣው፡፡

ከዚህ በኋላ ናቡከደነፆር ሕልም አለመ ፤ ሆኖም ሕልሙ ጠፋበት፡፡ አስማተኞቹን ሰብስቦ ‹ሕልሜን ከነፍቺው ንገሩኝ› ብሎ አፋጠጣቸው፡፡ ግራ ገባቸው ፤ ሕልሙን ተናግሮ ቢሆን ‹ሲሳይ ነው ፣ ዕድሜ ነው ፣ ጸጋ ነው› ብሎ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን ‹ሕልሜን ውለዱ› አለ፡፡ አልነግር ሲሉት ሊገድላቸው ወሰነ፡፡ በዚህ መካከል ሦስቱ ወጣቶች ከአጎታቸው ዳንኤል ጋር ሆነው መፍትሔ አመጡ፡፡ እነርሱ በጸሎት ሲተጉ እግዚአብሔር ሕልሙን ከነትርጓሜው ለዳንኤል ገለጠለት፡፡
ንጉሡ በዘነጋው ሕልሙ ያየው ‹ራሱ የወርቅ ፣ የቀረው አካሉ የብር ፣ የናስ ፣ የብረትና ሸክላ የሆነ ትልቅ ምስል ነበር› ዳንኤል ሕልሙን ለንጉሡ ከነገረው በኋላ እንዲህ ብሎ ፈታለት፡፡ ‹ንጉሥ ሆይ ባየኸው ሕልም ላይ በሥልጣን ከሁሉ በላይ አድርጎሃልና የወርቁ ራስ አንተ ነህ ፤ ከዚያ በታች ያየኻቸው ደግሞ ከአንተ በኃይል የሚያንሡ ከአንተ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት ናቸው›› ብሎ እርሱና ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት እንዴት መንግሥታቸው እንደሚያልፍ ሕልሙን ከነዝርዝር ፍቺው ነገረው፡፡ በዚህም ንጉሡ ደስ አለውና ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው ፤ ሦስቱን ወጣቶችም በአውራጃ ሥራ ላይ አዛዦች አድርጎ ሾማቸው፡፡

★ እንደ ንጉሡ አጎንብሱ ★

ናቡከደነፆር ዳንኤል ከፈታለት ረዥም ሕልም ውስጥ ግን ከአእምሮው ያልጠፋችው ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለው ዓረፍተ ነገር ነበረች፡፡ መቼም እኛ ወርቅ የሆንንበት ቅኔ ከልባችን አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ራስ ወዳዱ ናቡከደነፆር ከረዥሙ ሕልም ውስጥ ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለዋ ብቻ ልቡን ነካችው፡፡ ባልንጀራህን ‹እንደ ራስህ ውደድ› ስለሚል ራስን መውደድ ጥፋት አይደለም፡፡ ራስን መውደድ በጣም ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ‹ፀሐይ የምትወጣው እኔን ለማየት ነው› እስከማለት ያስደርሳል፡፡ ናቡከደነፆር በራሱ ፍቅር ወደቀ ፣ ራሱን አቅፎ ለመሳም ቃጣው ፤ በመጨረሻም ‹እኔ ወርቅ ነኝ› የምትለው አሳቡ አድጋ በዱራ ሜዳ ላይ ትልቅ የወርቅ ሐውልት ሆነች፡፡ ‹ለዚህ ጣዖት የማይሰግድ ሰው ወደ እሳት ይጣላል› የሚል አዋጅ አወጀ፡፡ የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሀገሩ ተሰማ፡፡ ሕዝቡ ወደ ዕቶን እሳት ትጣላለህ ከሚል ማስፈራሪያ ጋር ስሜቱን የሚነካ ሙዚቃም ሲሰማ ያለማመንታት ታዘዘ፡፡ በዚህ አዋጅ ምክንያት በድፍን ባቢሎን የሚኖሩ እስራኤላዊያንም ጭምር ሁሉም ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡

የአውራጃ ሹመኞች የሆኑት የቤተ መንግሥት ጾመኞች ሦስቱ ወጣቶች ግን አልሰገዱም፡፡ ሁሉም ሲሰግድ አለመስገድ ፣ ሁሉም ሲያጨበጭብ እጅን መሰብሰብ ፣ ሁሉ ሲስቅ መኮሳተር ጽናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹ከሀገሩ የወጣ ሰው እስኪመለስ ድረስ ፤ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ› ብለው መተረት አልፈለጉም፡፡ ሀገሩ ሁሉ ከሰገደ በእነዚህ ወጣቶች ለይቶ የሚፈርድባቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከእስራኤል ወገን ብዙ ሽማግሌዎች ብዙ መጽሐፍ አዋቂዎች አገጎንብሰው ቢሰግዱም እነዚህ ወጣቶች አልሰገዱም፡፡ ‹‹ከእኛ ብዙ የሚያውቁት እነ እገሌ እነእገሌ ከሰገዱ እኛ ለምን እንጠቆራለን? ከሰው ተለይተን ምን እንፈጥራለን? የአውራጃ ገዢ አድርጎ ሾሞን የለ አሁን እንቢ ብንል ውለታ ቢስ መሆን አይሆንብንም? ስገዱ ያለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው እንጂ ጣዖት አምልኩ አላለንም ፤ እሳት ውስጥ ከምንገባ ይህችን ቀን አጎንብሰን ብናልፋትስ ፣ ዋናው ልብ ነው›› ብለው ራሳቸውን ሊያሞኙ አልፈለጉም፡፡ ሁሉ ባጎነበሰበት ቀን አንሰግድም ብለው ቆሙ፡፡

★ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ★

ናቡከደነፆር ሦስቱ ወጣቶች እንዳልሰገዱ ሲነገረው ቁጣው ነደደና አስጠራቸው፡፡ ‹‹የምሰማው እውነት ነውን?›› አለ ፤ እንዲያስተባብሉ ዕድል ሲሠጥ፡፡ ‹አሁንም የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ብትሰግዱ መልካም ነው›› አለ፡፡ መቼም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ናቡከደነፆር የሙዚቃን ስሜት ቀስቃሽነት የተረዳ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ ‹‹በሉ ሙዚቃው ድጋሚ ይከፈትልሃል ትጨፍራላችሁ›› የሚል ይመስላል፡፡ ስገዱ ከማለቱ ሙዚቃውን ስትሰሙ ማለቱ ይገርማል፡፡ ከዚያ ማስፈራሪያ ጨመረበት ‹‹ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።

ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ለሚለው ለንጉሡ ጥያቄ ሦስቱ ወጣቶች ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም›› አሉት፡፡ ምን ማለታቸው ነው? ለምን አይመልሱለትም? ይህንን ያሉበት ምክንያት ናቡከደነፆር ከጥቂት ጊዜ በፊት ሕልም አልሞ በተፈታለት ጊዜ ደስ ብሎት ‹‹አምላካችሁ የአማልክት አምላክ የነገሥታትም ጌታ ምሥጢርም ገላጭ ነው›› ብሎ መስክሮ ስለነበር ነው፡፡ (ዳን 2፡47) አሁን ደግሞ ተገልብጦ ‹ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?› አላቸው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ትናንት ያመሰገነውን አምላክ እንደማያውቀው ሲሆን ላንተ መልስ አያስፈልግህም አሉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትናንት ያመለኩትን አምላክ ዛሬ እንደማያውቁ ሆነው ሲጠይቁ ፣ ትናንት ያመኑበትን ዛሬ ክደው ሲያናንቁ ‹‹በዚህ ነገር እንመልስላቸው ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም››
14.5K views , 15:24
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-27 18:21:12 የእግዚአብሔር መላዕክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል !(በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
12.5K views , 15:21
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-26 22:29:07 የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች pinned «ሐይቅ እጢፋኖስ የመጀመሪያው መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ የነበረ እጅግ ጥንታዊ ና ታሪካዊ ሥፍራ ነው:: በቅዱስ አባ ኢየሱስ ሞዓ አባትነት አእላፋትን የወለደው ይህ የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን ኩራት የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫንና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የመሳሰሉ ቅድስናን ከሊቅነት ያስተባበሩ መምህራንን ያፈራ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሥነ ጽሑፍ ከፍታ ላይ ለመድረሱ መነሻ…»
19:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-26 22:29:00 ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
14.2K views , 19:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-26 22:29:00 + ከታቦር ተራራ አትቅር +

"አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። "
ማር 9: 3
/ሽራፊ ሃሳቦች ከደብረ ታቦር ንባብ/

የወንጌላውያን ትሕትና ይደንቃል ፣ ማቴዎስ ማርቆስ ሉቃስ ስለ ደብረ ታቦር ሲጽፉ ዮሐንስ አልጻፈም። ዮሐንስ ተመርጦ የተገኘበትን ታሪክ "ተመርጬ" ብሎ አልጻፈም። የቀሩት ወንጌላውያን ደግሞ "እኛ የሌለንበትን ነገር አንጽፍም" አላሉም። አንድ ወንጌል እየሰበኩ የሚፎካከሩ ፣ የአንድ ቤት ጣሪያ እየሠሩ ቆርቆሮ የሚሻሙ የእኛ ዘመን አገልጋዮች አልነበሩምና እነርሱ ያልተመረጡበትን ታሪክ ለመናገር ተሯሯጡ። እኛን የማያካትት ክብር ፣ እኛን የማይጨምር ድግስ ጉዳይ ሲነሣ ለማይጥመን ፣ እኛ የሌለንበትን ፎቶ እንኳን ለማየት የማንፈልግ ፣ በእኛ በኩል ያለፈን ነገር ብቻ የምናራግብ ፣ የሌለንበትን ነገር ጥሩም ቢሆን እንኳን ለምናጣጥል "በእኔ በቀር ባዮች" ትምህርቱ ድንቅ ነው።

ሌላ ማሳያም አለ ማቴዎስ ወንጌላዊው ስለ ራሱ ታሪክ ሲጽፍ "ማቴዎስ የተባለ ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ" ብሎ በኃጢአት ከተዘፈቀበት ሥራ ላይ ወደ ክርስትና እንደተጠራ በግልጽ ሲጽፍ ሌሎቹ ወንጌላውያን ግን በሐዋርያት ዝርዝር ላይ ማቴዎስ ያሉትን ሰው ስለ ቀድሞ የቀራጭነት ሥራው ሲጽፉ ግን ሌዊ የሚል ተለዋጭ ስሙን ተጠቅመዋል። ትሑቱ ማቴዎስ ግን በሌሎች ወንጌላውያን የተሸሸገ የቀድሞ የኃጢአት አኗኗሩን ለእግዚአብሔር ይቅር ባይነት ማሳያ እንዲሆን ስለፈለገ ጭራሽ በሐዋርያት የስም ዝርዝር ላይ "ቀራጩ ማቴዎስ" ብሎ ራሱን ጠርቷል።

የሚገርመው ከቀራጭነት ከተጠራ በኋላ በቤቱ ታላቅ ድግስ ደግሶ ጌታችንን ከኃጢአተኞች ጓደኞቹ ጋር የተቀበለ መሆኑን በሌሎች ወንጌላውያን ሲጽፉ ማቴዎስ ግን ቀራጭነቱን አጉልቶ እንዳልጻፈ ሁሉ የግብዣው ነገር ደጋሹ እርሱ መሆኑን አድበስብሶ በመጻፍ አልፎታል።

★ ★ ★

ቅዱስ ጴጥሮስ "ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" አለ። "ለእኛ" መልካም ነው የሚለው ቃል ድንቅ ነው። በእግዚአብሔር ቤት መኖራችን መልካምነቱና ጥቅሙ ለእኛ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። የማንጠቅም ባሪያዎቹ ስሙን በአሕዛብ ዘንድ ከማሰደብ በቀር ለእርሱ ምን እንጠቅመዋለን። ለዚህም ነው ቅዱስ ባስልዮስ "ጌታ ሆይ የአንተ አምላክነት ለእኔ ያስፈልገኛል እንጂ የእኔ ፍጡርነት ለአንተ አያስፈልግህም" ያለው።
ስለዚህ ጴጥሮስ "ለእኛ መልካም ነው" አለ።

"ብትወድስ ሦስት ዳስ እንሥራ" አለ ፣ ጌታ ካልወደደ እንኳን ሦስት አንድ ዳስ መሥራት አይቻልም ፣ እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ" ስለዚህ "ብትወድስ" አለ።

የዋሁ ጴጥሮስ ለእኔ ልሥራ አላለም ፣ የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያ ነኝ ብሎ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ከማክበር ወደ ኋላ አላለም። "አንተ ዓለት ነህ በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ" በተባለ ማግስት ለነቢያቱ ድንኳን ሊቀልስ የጠየቀ ከጴጥሮስ በቀር ማን አለ?

ከእግዚአብሔር አብ ግን "አትሙት" እስከማለት ለደረሰው ለነጴጥሮስ ንግግር "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" የሚል ትእዛዝ መጣ። ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ቃሉን ሳይሰሙ ዳስ መሥራት መጀመር አይቻልም።

በዚያ ላይ ጌታ የመጣው በደብረ ታቦር ድንኳን አስጥሎ ሊኖር ሳይሆን በቀራንዮ በተሰቀለበት በመስቀሉ ካስማ በደሙ ድንኳን ተክሎ ሊያስጠልለን ነው። ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ "ጴጥሮስ ሆይ ለአንተ የፊቱን ብርሃን እያየህ በዚህ መኖር መልካም ነው ፣ እኛ ግን የምንድነው በተራራው ሲኖር ሳይሆን ወርዶ ፊቱን በጥፊ ሲመታ ነው" ብሎታል።

ጴጥሮስ የዋሁ "በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ" ላለው ለክርስቶስ ድንኳን ሊቀልስ ጠየቀ። በሰማይ "በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ድንኳን" ላለችው ሊቀ ካህናት ድንኳን ሊሠራ ለመነ። እዚህ አለ ሲሉት እዚያ ለሚገኘው ፣ በመንፈስ እየተነጠቀ አድራሻውን ለመወሰን ያስቸግር ለነበረው ኤልያስ እንዲቀመጥ ተስፋ አድርጎ ድንኳን ልሥራ አለ። እጅግ የተዋበችና በወርቅ በሐር ያጌጠችን የኦሪት ድንኳን ለሠራው ሙሴ ዓሣ አጥማጁ ጴጥሮስ ድንኳን ልሥራለት አለ። ሐዋርያት ነቢያቱን ሊያስተናግዱ የለመኑባት ደብረ ታቦር ፣ ሐዋርያት ነቢያቱን ለጌታ ቀኝ አዝማች ግራዝማች አድርገው በድንኳን አስቀምጠው እነርሱ እንደ ሎሌ ከደጅ ሊኖሩ የጠየቁ እነ ጴጥሮስ እንደምን ይደንቃሉ? ጴጥሮስ ሆይ አሁን በሰማይ ድንኳኖች ውስጥ እያገለገልህ ይሆንን? ደብረ ታቦርን አይተህ በደስታ "እንኑር" ያልከው ጴጥሮስ ሆይ የገነት ደስታ ስታይ ምን ተሰምቶህ ይሆን?

በእሳት ድንኳን ለመኖር ተስፋ የምናደርግ "በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል" የተባልን እኛስ ምንኛ የታደልን ነን?

★ ★ ★

በታቦር ተራራ ላይ የጌታችን ልብስ እንደ ፀሐይ አበራ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ከፀሐይም በላይ ነው ፣ ፀሐይ አይቶ የወደቀ የለም የጌታችንን ልብስ ሲያዩ ግን የወደቁት ያበራው ከዚያ በላይ ስለሆነ ነው" ይላል።

ከጌታችን በዚያ ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ነበረ። ሙሴ እንደምናውቀው ጽላቱን ተቀብሎ ሲወርድ ሕዝቡ "እባክህን ተሸፈንልን" ብለውት ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፍኖ ነበር። የሙሴ አምላክ ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲወድቁ አይቶ በልብሱ እንዳይሸፈን ያበራው ፊቱ ብቻ ሳይሆን ልብሱም ነበር።

" አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ" ማር 9: 3
የሚለው ቃል ምንኛ የሚደንቅ ነው። በምድር ላይ ያለ አጣቢ ቢፈትግ ቢታገል የዚያን ያህል ሊያነጻው የማይችለው ነጭ እንዴት ያለ ነው? መቼም ሁላችን የምናውቀው ነጭ ነገር ሁሉ በምድር ላይ ባለ አጣቢ የታጠበ ስለሆነ እንዲህ ነው ማለት አንችልም። ብቻ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በምድር ያሉ አጣቢዎች ከሚያነጡት በላይ ልብስን ማንጣት ይችላል።

ይህ ቃል በኃጢአት እድፍ ልብሳችን ላደፈ ሁሉ መጽናኛችን ነው።

መቼም የምድር አጣቢዎች አቅማቸው ውስን ነው።
ቆሽሸን ያዩን ሰዎች ብንታጠብም አያምኑንም ፣ ቢያጥቡልንም በኅሊናቸው የሚያስቀሩብን ቆሻሻ አለ።
በሰው ዓይን አንዴ ቆሽሸህ አትገኝ እንጂ ከተገኘህ መቼም ነጭ አትሆንም። አንተ ግን የደብረ ታቦሩ ብርሃን መድኃኔ ዓለምን ብቻ "እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ" በለው "ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። " ብሎ በገባው ቃል መሠረት ነጭ ያደርግሃል።

እርሱ ወዳለባት የቅድስት ቤተክርስቲያን ተራራ በንስሓ ከደረስክና በታቦር ያበራውን ብርሃኑን ካበራልህ ነጭ ትሆናለህ። ከዚያ "አጣቢ የማያነጻውን ያህል ትነጻለህ" ከአብ የባሕርይ ልጅ ከብርሃኑ ፀዳል ስትቀርብ አንተም በጥምቀት ያገኘኸው የጸጋ ልጅነትህ ያንጸባርቃል። ነጭ በሆንህ ጊዜ የሚያዩህ ሁሉ "በበጉ ደም ልብስህ መታጠቡን"ና ነጭ መሆኑን አይተው ይደነግጣሉ ፣ ሊሰሙህ ያልወደዱ ሁሉ ለባሕርይ ልጁ "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" ብሎ እንዳዘዘለት ለአንተም ጆሮ እንዲሠጡህ ያደርግልሃል።

አንተ ብቻ ከደብረ ታቦር አትቅር ፣ ካልሞትህ እንደ ኤልያስ ፈጥነህ ና ፣ በበደል ከሞትክም እንደሙሴ ተነሥተህ ና። ብቻ ወደ ደብረ ታቦር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት ተስፋ አትቁረጥ ፣ እንደ ሙሴ ትሞታለህ እንጂ ምድረ ርስትን አታይም ብትባል ፣ እንደ ኤልያስ ትኖራለህ እንጂ ሞትን አታይም ብትባል ብቻ አንተ ከደብረ ታቦር አትቅር።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ደብረ ታቦር 2010
ለንደን ፣ ብሪታንያ
14.7K views , 19:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-26 16:40:54 ሐይቅ እጢፋኖስ የመጀመሪያው መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ የነበረ እጅግ ጥንታዊ ና ታሪካዊ ሥፍራ ነው:: በቅዱስ አባ ኢየሱስ ሞዓ አባትነት አእላፋትን የወለደው ይህ የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን ኩራት የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫንና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የመሳሰሉ ቅድስናን ከሊቅነት ያስተባበሩ መምህራንን ያፈራ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሥነ ጽሑፍ ከፍታ ላይ ለመድረሱ መነሻ የሆነ ቦታ ነው::

ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በዕድሜ ዘጠና ዓመት ያለፋቸው በጵጵስና ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ዕብራይስጥና ዐረቢኛን ጠንቅቀው የሚያውቁ በረከታቸው የሚያሳሳ ለቤተ ክርስቲያን የዋሉት ውለታ እጅግ ብዙ የሆነ አባት ናቸው::

"ልሔድ ክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" የሚሉት እኚህ ሐዋርያዊ አባት ከማለፌ በፊት ይህንን ትምህርት ቤት ፈጽሜ እንድሔድ አግዙኝ ብለው ትልቅ የበረከት ጥሪን ለሁላችን አስተላልፈዋል:: እንኳን ሐይቅን ያህል ታሪካዊ ሥፍራ ላይ ቀርቶ በበረሃ ላይም ሕንፃ እንጀምር ቢሉን የብፁዕ አባታችንን ቡራኬ ለመቀበል የማይሻማ የለም:: የኤልያስን በረከት ለመቀበል ኤልሳዕ የሮጠውን ሩጫ ሁላችንም ይህንን ትምህርት ቤት በመፈጸም እንሮጣለን::

ነገው ዕለት "ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት" የተሰኘውን ድንቅ መጽሐፋቸውን ከቀኑ 7:00 ጀምሮ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አዳራሽ መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ዶ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ የመጽሐፋቸውን ሽያጭ የሚገኘውን ትርፍና በዕለቱ የሚገኘውን ገቢ ለሐይቅ እስጢፋኖስ የትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታ እንዲውል አድርገዋል:: ነገ በቅድስት ሥላሴ ተገኝተን በረከቱን እንካፈል::

ከሩቅ ያለንም በዚህ አካውንት የተቻለንን እናስገባ:: 1000520883097
https://fb.watch/kMs74TMFIK/?mibextid=CDWPTG
22.9K views , 13:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-25 17:28:26 ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ ዮሐ 21 ፥ 3 1


17.2K views , 14:28
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-25 15:50:44 + የተቀደሰው የሩጫ ውድድር +

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሩጫ ብሔራዊ ኩራት በሆነበት ሀገር መቼም የሩጫ ነገር ብናወራ ሰሚ አናጣም:: ሮጦ ሀገር ማስጠራት : ሮጦ ብዙ ሀብት ማፍራትና ለሀገር መትረፍ የቻሉ ውድ አትሌቶቻችንን በፍቅር እናያቸዋለን:: "በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ" የሚለው ቅዱስ ቃል ለነፍስ ቢነገርም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን "ታገኙ ዘንድ ሩጡ" የሚለው መርሕ "ሮጬ ባለፈልኝ" በሚሉ ተስፈኞች ይተገበራል:: (1ቆሮ 9:24)

ዛሬ ግን በሁለት ሰዎች መካከል የተደረገ ቅዱስ ሩጫ ትዝ አለኝ:: በትንሣኤ ዕለት የተደረገ ቅዱስ እሽቅድምድም በዓይነ ሕሊናዬ መጣ::
ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ሁለቱ የተሳተፉበት ዳኛም ተመልካችም የሌለበት የትንሣኤ ዕለት ሩጫ!!!

ሴቶች ወደ ጌታ መቃብር ደርሰው ሲመለሱ ጌታ በመቃብር እንደሌለ ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩአቸው::
ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቃብሩ ሔዱ::

"ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ" ዮሐ 20:4

በዚህ ቀን በተደረገው ቅዱስ ሩጫ የ58 ዓመቱ ጎልማሳ ጴጥሮስ ከ28 ዓመቱ ወጣት ዮሐንስ ጋር ወደ ጌታ መቃብር ሮጡ:: ሐሙስ ማታ ጌታውን የካደው ጴጥሮስ እስከ መስቀል ድረስ ጌታውን ከተከተለው ዮሐንስ ጋር አብሮ ወደ መቃብሩ ሮጠ::

ጴጥሮስ ሆይ ወደ ጌታህ መቃብር በሩጫ ስትገሰግስ ምን እያሰብህ ይሆን? ሐሙስ በካድከው ጊዜ ቀና ብለው ያዩህ ዓይኖቹ በሕሊናህ መጥተው ይሆን?
ወደ መቃብሩ ስትሮጥ "ጌታ ሆይ በአፌ ክጄሃለሁ በእግሮቼ ግን አልክድህም" ብለህ አስበህ ይሆን? "በባሕር ላይ ያራመድኸው እግሬ : አጎንብሰህ ያጠብከው እግሬ ወደ አንተ ለመሮጥ አይደክመውም" ብለህ ይሆን? መቃብሩ ሥር ተደፍተህ ለማልቀስ የሐሙሱን ዕንባህን በመግነዙ ለማበስ አስበህ ይሆን?

ብቻ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር ወደ መቃብሩ ሮጠ:: ዮሐንስ በጉልበቱ ገና ወጣት ቢሆንም : እንደ ጴጥሮስ ጸጸት የማይቆጠቁጠው ድል አድራጊ ቢሆንም ጴጥሮስ አብሮ ከመሮጥ ወደኁዋላ አላለም::

ብቻ መቃብሩ ልድረስ እንጂ ቢቀድመኝም እከተለዋለሁ:: እንደርሱ እስከ መስቀል ባልጸናም ለመቃብሩ ግን ዳግም እታገላለሁ ብሎ ጴጥሮስ ሮጠ::

በዚህ ቅዱስ ሩጫ አርብ የወንድ ለቅሶን ያፈሰሰው ዮሐንስ በዕንባ በደከሙ ዓይኖቹ በኀዘን በጠቆረ ፊቱ እያማተረ ወደ ጌታ መቃብር ገሠገሠ:: በዚያች ዕለት ጌታን እንዴት እንደ ገረፉት አይቶአል:: እንዴት እንደ ቸነከሩት ተመልክቶአል:: አሁን ደግሞ መስቀል ሥር ቆመው በዋሉ እግሮቹ ወደ መቃብሩ እየሮጠ ነው::

ወንድሜ ሆይ ጴጥሮስና ዮሐንስን ወደ ጌታ መቃብር ሲሮጡ እያቸው:: አንተና ጉዋደኞችህስ ወዴት ትሮጣላችሁ? የእናንተ እሽቅድምድም ወደ ጌታ መቃብር ነው? የት ለመሔድ ትፎካከራላችሁ? የት እንገስግስ ትባባላላችሁ?

ወጣቱ ዮሐንስ ጎልማሳውን ጴጥሮስን ቀድሞ ከጌታ መቃብር ደረሰ:: የጌታን መግነዝም አየ:: ወደ ውስጥ ግን ሳይገባ ቆሞ ጴጥሮስን ጠበቀው:: ጴጥሮስ ዘግይቶ ቢደርስም ከዮሐንስ ቀድሞ ወደ መቃብሩ ገባ::

ከእኔ የበረታ መንፈሳዊ ጉልበት ያለህ ወንድሜ ሆይ ብትቀድመኝ እንኩዋን አትፍረድብኝ:: ጨክነህ ጥለኸኝ ወደ ጌታ ማረፊያ እንዳትገባ:: የዘገየሁት ኃጢአት እግሬን አስሮት ነውና ብርቱው ወንድሜ ሆይ እባክህን ጠብቀኝ:: ድክመቴን አይተህ አትናቀኝ መጎተቴን አይተህ አትፍረድብኝ:: አደራህን ብቻህን ወደ ጌታ ደስታ እንዳትገባ:: አደራህን በንስሓ እስክበረታ ጠብቀኝ:: እንኩዋን አንተ አብረኸኝ ሩጫ የጀመርክ ወንድሜ ቀርቶ ከእኔ ቀድመው ሩጫቸውን የጨረሱት እንኩዋን ብቻቸውን ወደ ዘላለማዊ ደስታ እንዳይገቡ በገነት ሆነው እኔን ይጠብቁኝ የለ?

ነቢዩ እንደተናገረ :-
አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ፤
ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤
ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ፡
ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ። (መዝ 142:7)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት 16 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://t.me/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
18.8K views , 12:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-22 15:17:05 +++ "እየጠላን የምናደርገው" +++

ብዙ ሰው ‹‹እኔ ሐሜት አልወድም፡፡ ግን ማማት የሚወዱ ጓደኞች አሉኝ›› ይላል፡፡ አሁን እርሱ ምን እያደረገ ነው? ‹‹ወዳጆቼ ሐሜተኞች ናቸው›› ሲል እያማቸው አይደለምን? ወይስ ለእርሱ ሲሆን ሐሜቱ ተለውጦ የመረጃ ቅብብል ይሆናል?! በነገራችን ላይ ይህ የዚህ ጽሑፍ መግቢያ ራሱ ሐሜት ነው።

የማንወደው ነገር ግን እየጠላንም ቢሆን የምናደርገው ኃጢአት ሐሜት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሜተኛ ሆኖ የተጠቀሰው በእባብ ያደረው ሰይጣን ነው፡፡ በመጀመሪያ የታማው ደግሞ እግዚአብሔር ሲሆን፣ ሐሜቱን ሰምታ ሳትመረምር የተቀበለችውና ለስሕተት የቸኮለችው ሴት ሔዋን ነበረች፡፡(ዘፍ 3፥1-5)

የሰይጣን ሐሜት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንደኛ "አትሞቱም፤ እንደ እርሱ እንዳትሆኑ ነው የከለከላችሁ" በሚለው ንግግሩ "እግዚአብሔር ዋሽቷችኋል" እያለ ፍቅሩን እንድትጠራጠር እያደረገ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ከዛፉ ብትበሉ እንደ እርሱ ትሆናላችሁ በማለት የእግዚአብሔር አምላክነት "የዛፍ ፍሬ" በመብላት የተገኘ መሆኑንና እርሱም እንደ እነርሱ የነበረበት ጊዜ እንዳለ እንድታስብ እየገፋፋት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ስም ማጥፋት (Character assassination) ከየት ሊገኝ ይችላል? ሰይጣን በነገር ሁሉ ፍጹም የሆነን አምላክ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ሐሰት ፈጥሮ ለማማት ወደ ኋላ ካላለ፣ አንዳች ጉድለት የማያጣብን እኛማ ከሐሜቱ ጅራፍ ልናመልጥ እንደማንችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

በተለይ በአሁን ጊዜ ሐሜት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ሥሩን ሰድዷል። እንደውም ባልንጀራን ማማት እንደ ምግብ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቻችን በዚህች ደሃ አገር ከመጠን በላይ ወፍረን እንቸገር ነበር። ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን የሐሜት አውድማዎች ሆነዋል። በየገጾቻችን ከሽነን የምናቀርባቸው ጽሑፎች ጠረናቸው የሰው ሥጋ የሰው ሥጋ ይላሉ። ፊታችን በሐሜት ወይቦ ሁለት መልክ ካወጣን ቆየን። ይኸው ሳንባችን በማማት አየር ተመርዞ ሳሉ ከበረታብን ሰነባብተናል። ወዳጃችንን የማናማበት ብቸኛው ጊዜ ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ሰዓት ነው። ያውም ደግሞ ያንኑ ጊዜ ሌላኛውን ሰው ለማማት ካልተጠቀምንበት ማለቴ ነው።

ሊቁ ዮሐንስ ካዝያን እንደሚናገረው ሰው ከሚጠቅመው ቃለ እግዚአብሔር ይልቅ የማይጠቅመው ሐሜት ያጓጓዋል። የአምላክ ቃል ሲነገር እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለው ሁሉ፣ የሐሜት ነገር ሲሆን ግን እንደ እርሱ ንቁ የሚሆን የለም። በጥፍሩ ቆሞ ይሰማል። ሌሊቱን ሁሉ ሳይተኛ ቢያድር ደስ ይለዋል።

ለመሆኑ ባልንጀራችንን ስለ ምን በቀስታ እናማዋለን? የወዳጃችንንስ ውድቀት በማውራት በእኛ ላይ የምንጨምረው ምን በጎ ነገር አለ? በሰው ፊት መልካም እየመሰልን ከኋላው ግን ስለ እርሱ ውድቀት በማውራት የራሳችንን ደረጃ ከፍ ማድረግ አይቻልም። ስለ ሌሎች በማውራት የምናጠፋውን ሰዓት ራሳችንን ለማሳደግ ብንጠቀምበት ኖሮ "መኖራችንን ትርጉም እንዲኖረው" ማድረግ ይቻለን ነበር።

"ንጹሕ ወዳጅነት" ሐሜትና ማሾክሾክ የሌለባት የታማኞች ጌጥ ናት። የሐሜት ስለታቸውን ያልጣሉ ሰዎች "እውነተኛ ባልንጀርነት"ን አያውቋትም። አንተ በፍቅር ወዳጅ አድርገህ ከፊትህ ስታቀርባቸው እነርሱ ከኋላህ ሆነው የሚያሙህን አትጥላቸው፤ አትጣላቸው። ነገር ግን የሐሜቱ እርሾ እንዳያገኝህ ቶሎ ተለያቸው። ከፊትህም አድርገህ አታሰቃያቸው። የእነርሱ ቦታ ከኋላህ መሆን ነው።

ሐሜት የሰይጣን ነው። ሰውን የሚያማ በገዛ ፈቃዱ አንደበቱን ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠ ነው። ማማት በቤተ ክርስቲያን መለያየትን ያመጣል፣ ቤተሰብ ይበትናል፣ ወንድሞችን ያጣላል። ብንችል ስለ ሰው የምናውቀውን ጥሩውን እናውራ። የምናወራው ጥሩነት ከሌለው ደግሞ ቢያንስ ምንም አንበል።

ሔዋን ልክ እንደ አዳም እባብን "ሂጅልኝ" ብላ ብታባራት ኖሮ እነርሱም ከፈጣሪ ባልተጣሉ ሐሜትም ወደ ዓለም ባልገባ ነበር። ሐሜትን ማጥፋት ከፈለግን ሐሜተኛን እሺ አንበል። ማር ይስሐቅም "ወዳጁን በፊትህ የሚያንኳስሰውን ሰው አፉን መዝጋት ባትችል እንኳን ቢያንስ ሐሜቱን ከመስማት ተቆጠብ" ይላል። ሐሜትን ደስ ብሎህ ካልሰማኸው ደስ ብሎት የሚያማን ሰው ልትፈጥር አትችልም።

"ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" ገላ 5፥15
Dn Abel Kassahun Mekuria
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://t.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
27.9K views , 12:17
ክፈት / አስተያየት ይስጡ