Get Mystery Box with random crypto!

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የሰርጥ አድራሻ: @deaconhenokhaile
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 64.23K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ቻናል በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ፈቃድ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ነው::
@deaconhenokhaile
"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን"
2ኛ ቆሮ. 2:14

Ratings & Reviews

2.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 10

2023-05-19 21:17:36 "አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። "
<ማር 9: 3>

የወንጌላውያን ትሕትና ይደንቃል ፣ ማቴዎስ ማርቆስ ሉቃስ ስለ ደብረ ታቦር ሲጽፉ ዮሐንስ አልጻፈም። ዮሐንስ ተመርጦ የተገኘበትን ታሪክ "ተመርጬ" ብሎ አልጻፈም። የቀሩት ወንጌላውያን ደግሞ "እኛ የሌለንበትን ነገር አንጽፍም" አላሉም። አንድ ወንጌል እየሰበኩ የሚፎካከሩ ፣ የአንድ ቤት ጣሪያ እየሠሩ ቆርቆሮ የሚሻሙ የእኛ ዘመን አገልጋዮች አልነበሩምና እነርሱ ያልተመረጡበትን ታሪክ ለመናገር ተሯሯጡ። እኛን የማያካትት ክብር ፣ እኛን የማይጨምር ድግስ ጉዳይ ሲነሣ ለማይጥመን ፣ እኛ የሌለንበትን ፎቶ እንኳን ለማየት የማንፈልግ ፣ በእኛ በኩል ያለፈን ነገር ብቻ የምናራግብ ፣ የሌለንበትን ነገር ጥሩም ቢሆን እንኳን ለምናጣጥል "በእኔ በቀር ባዮች" ትምህርቱ ድንቅ ነው።

ሌላ ማሳያም አለ ማቴዎስ ወንጌላዊው ስለ ራሱ ታሪክ ሲጽፍ "ማቴዎስ የተባለ ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ" ብሎ በኃጢአት ከተዘፈቀበት ሥራ ላይ ወደ ክርስትና እንደተጠራ በግልጽ ሲጽፍ ሌሎቹ ወንጌላውያን ግን በሐዋርያት ዝርዝር ላይ ማቴዎስ ያሉትን ሰው ስለ ቀድሞ የቀራጭነት ሥራው ሲጽፉ ግን ሌዊ የሚል ተለዋጭ ስሙን ተጠቅመዋል። ትሑቱ ማቴዎስ ግን በሌሎች ወንጌላውያን የተሸሸገ የቀድሞ የኃጢአት አኗኗሩን ለእግዚአብሔር ይቅር ባይነት ማሳያ እንዲሆን ስለፈለገ ጭራሽ በሐዋርያት የስም ዝርዝር ላይ "ቀራጩ ማቴዎስ" ብሎ ራሱን ጠርቷል።

የሚገርመው ከቀራጭነት ከተጠራ በኋላ በቤቱ ታላቅ ድግስ ደግሶ ጌታችንን ከኃጢአተኞች ጓደኞቹ ጋር የተቀበለ መሆኑን በሌሎች ወንጌላውያን ሲጽፉ ማቴዎስ ግን ቀራጭነቱን አጉልቶ እንዳልጻፈ ሁሉ የግብዣው ነገር ደጋሹ እርሱ መሆኑን አድበስብሶ በመጻፍ አልፎታል።
★ ★ ★

ቅዱስ ጴጥሮስ "ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" አለ። "ለእኛ" መልካም ነው የሚለው ቃል ድንቅ ነው። በእግዚአብሔር ቤት መኖራችን መልካምነቱና ጥቅሙ ለእኛ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። የማንጠቅም ባሪያዎቹ ስሙን በአሕዛብ ዘንድ ከማሰደብ በቀር ለእርሱ ምን እንጠቅመዋለን። ለዚህም ነው ቅዱስ ባስልዮስ "ጌታ ሆይ የአንተ አምላክነት ለእኔ ያስፈልገኛል እንጂ የእኔ ፍጡርነት ለአንተ አያስፈልግህም" ያለው።
ስለዚህ ጴጥሮስ "ለእኛ መልካም ነው" አለ።

"ብትወድስ ሦስት ዳስ እንሥራ" አለ ፣ ጌታ ካልወደደ እንኳን ሦስት አንድ ዳስ መሥራት አይቻልም ፣ እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ" ስለዚህ "ብትወድስ" አለ።

የዋሁ ጴጥሮስ ለእኔ ልሥራ አላለም ፣ የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያ ነኝ ብሎ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ከማክበር ወደ ኋላ አላለም። "አንተ ዓለት ነህ በዚህች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ" በተባለ ማግስት ለነቢያቱ ድንኳን ሊቀልስ የጠየቀ ከጴጥሮስ በቀር ማን አለ?

ከእግዚአብሔር አብ ግን "አትሙት" እስከማለት ለደረሰው ለነጴጥሮስ ንግግር "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" የሚል ትእዛዝ መጣ። ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ቃሉን ሳይሰሙ ዳስ መሥራት መጀመር አይቻልም።

በዚያ ላይ ጌታ የመጣው በደብረ ታቦር ድንኳን አስጥሎ ሊኖር ሳይሆን በቀራንዮ በተሰቀለበት በመስቀሉ ካስማ በደሙ ድንኳን ተክሎ ሊያስጠልለን ነው። ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ "ጴጥሮስ ሆይ ለአንተ የፊቱን ብርሃን እያየህ በዚህ መኖር መልካም ነው ፣ እኛ ግን የምንድነው በተራራው ሲኖር ሳይሆን ወርዶ ፊቱን በጥፊ ሲመታ ነው" ብሎታል።

ጴጥሮስ የዋሁ "በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ" ላለው ለክርስቶስ ድንኳን ሊቀልስ ጠየቀ። በሰማይ "በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ድንኳን" ላለችው ሊቀ ካህናት ድንኳን ሊሠራ ለመነ። እዚህ አለ ሲሉት እዚያ ለሚገኘው ፣ በመንፈስ እየተነጠቀ አድራሻውን ለመወሰን ያስቸግር ለነበረው ኤልያስ እንዲቀመጥ ተስፋ አድርጎ ድንኳን ልሥራ አለ። እጅግ የተዋበችና በወርቅ በሐር ያጌጠችን የኦሪት ድንኳን ለሠራው ሙሴ ዓሣ አጥማጁ ጴጥሮስ ድንኳን ልሥራለት አለ። ሐዋርያት ነቢያቱን ሊያስተናግዱ የለመኑባት ደብረ ታቦር ፣ ሐዋርያት ነቢያቱን ለጌታ ቀኝ አዝማች ግራዝማች አድርገው በድንኳን አስቀምጠው እነርሱ እንደ ሎሌ ከደጅ ሊኖሩ የጠየቁ እነ ጴጥሮስ እንደምን ይደንቃሉ? ጴጥሮስ ሆይ አሁን በሰማይ ድንኳኖች ውስጥ እያገለገልህ ይሆንን? ደብረ ታቦርን አይተህ በደስታ "እንኑር" ያልከው ጴጥሮስ ሆይ የገነት ደስታ ስታይ ምን ተሰምቶህ ይሆን?

በእሳት ድንኳን ለመኖር ተስፋ የምናደርግ "በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል" የተባልን እኛስ ምንኛ የታደልን ነን?

★ ★ ★

በታቦር ተራራ ላይ የጌታችን ልብስ እንደ ፀሐይ አበራ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ከፀሐይም በላይ ነው ፣ ፀሐይ አይቶ የወደቀ የለም የጌታችንን ልብስ ሲያዩ ግን የወደቁት ያበራው ከዚያ በላይ ስለሆነ ነው" ይላል።

ከጌታችን በዚያ ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ነበረ። ሙሴ እንደምናውቀው ጽላቱን ተቀብሎ ሲወርድ ሕዝቡ "እባክህን ተሸፈንልን" ብለውት ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፍኖ ነበር። የሙሴ አምላክ ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲወድቁ አይቶ በልብሱ እንዳይሸፈን ያበራው ፊቱ ብቻ ሳይሆን ልብሱም ነበር።

" አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ" ማር 9: 3
የሚለው ቃል ምንኛ የሚደንቅ ነው። በምድር ላይ ያለ አጣቢ ቢፈትግ ቢታገል የዚያን ያህል ሊያነጻው የማይችለው ነጭ እንዴት ያለ ነው? መቼም ሁላችን የምናውቀው ነጭ ነገር ሁሉ በምድር ላይ ባለ አጣቢ የታጠበ ስለሆነ እንዲህ ነው ማለት አንችልም። ብቻ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በምድር ያሉ አጣቢዎች ከሚያነጡት በላይ ልብስን ማንጣት ይችላል።

ይህ ቃል በኃጢአት እድፍ ልብሳችን ላደፈ ሁሉ መጽናኛችን ነው።

መቼም የምድር አጣቢዎች አቅማቸው ውስን ነው።
ቆሽሸን ያዩን ሰዎች ብንታጠብም አያምኑንም ፣ ቢያጥቡልንም በኅሊናቸው የሚያስቀሩብን ቆሻሻ አለ።
በሰው ዓይን አንዴ ቆሽሸህ አትገኝ እንጂ ከተገኘህ መቼም ነጭ አትሆንም። አንተ ግን የደብረ ታቦሩ ብርሃን መድኃኔ ዓለምን ብቻ "እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ" በለው "ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። " ብሎ በገባው ቃል መሠረት ነጭ ያደርግሃል።

እርሱ ወዳለባት የቅድስት ቤተክርስቲያን ተራራ በንስሓ ከደረስክና በታቦር ያበራውን ብርሃኑን ካበራልህ ነጭ ትሆናለህ። ከዚያ "አጣቢ የማያነጻውን ያህል ትነጻለህ" ከአብ የባሕርይ ልጅ ከብርሃኑ ፀዳል ስትቀርብ አንተም በጥምቀት ያገኘኸው የጸጋ ልጅነትህ ያንጸባርቃል። ነጭ በሆንህ ጊዜ የሚያዩህ ሁሉ "በበጉ ደም ልብስህ መታጠቡን"ና ነጭ መሆኑን አይተው ይደነግጣሉ ፣ ሊሰሙህ ያልወደዱ ሁሉ ለባሕርይ ልጁ "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" ብሎ እንዳዘዘለት ለአንተም ጆሮ እንዲሠጡህ ያደርግልሃል።

አንተ ብቻ ከደብረ ታቦር አትቅር ፣ ካልሞትህ እንደ ኤልያስ ፈጥነህ ና ፣ በበደል ከሞትክም እንደሙሴ ተነሥተህ ና። ብቻ ወደ ደብረ ታቦር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት ተስፋ አትቁረጥ ፣ እንደ ሙሴ ትሞታለህ እንጂ ምድረ ርስትን አታይም ብትባል ፣ እንደ ኤልያስ ትኖራለህ እንጂ ሞትን አታይም ብትባል ብቻ አንተ ከደብረ ታቦር አትቅር።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
11.9K views , 18:17
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-13 18:13:00 +ሕይወት ከሰርግ ማግስት+
መምህር ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ተከታታይ ትምህርት ከርስቲያናዊ ቤተሰብ
ክፍል ሰባት (7)
6.0K views , 15:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-13 18:12:24 {{ማርያም ግን መልካምን እድል መርጣለች ከሷም አይወሰድባትም ሉቃ {10÷42}}}
《 በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ 》


@deaconhenokhaile
@deaconhenokhaile
@deaconhenokhaile
6.1K views , 15:12
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-09 17:18:40 https://www.facebook.com/100044640840128/posts/767778098053545/?mibextid=HQY48bSgtFjSxY5f
9.7K views , 14:18
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-09 13:16:54 "ወንጌላዊው ዮሐንስ እመቤታችንን የጠራበት መንገድ"

ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን …………“የኢየሱስ
እናት” ብሎ ጠርቷታል፡፡ ይኼ ሐዋርያ በጻፈው
ወንጌል ላይ የራሱንም ስም እንኳን አንድ ጊዜ
ያልጠራ ትሑት ሰው ቢሆንም የእመቤታችንን
ስም የጠራበት መንገድ እንዲሁ የምናልፈው
አይደለም፡፡ በወንጌሉ/በዮሐንስ ወንጌል/
እመቤታችንን ስምንት ጊዜ አንስቷታል፡፡ /ዮሐ
፪፥፩‚ ፪፥፫‚ ፪፥፭‚ ፪፥፲፪‚ ፮፥፵፪‚ ፲፱፥፳፭
‚ ፲፱፥፳፮‚ ፲፱፥፳፯/ ስምንት ጊዜ ሲጠራት ግን
አንድም ቦታ “ማርያም” ብሎ በስሟ
አልጠራትም፡፡ የጠራት “የኢየሱስ እናት” “እናቱ”
ብቻ ብሎ ነው፡፡ ቅርበት ባይኖረው ነው እንዳንል
ወንጌሉ ድንግል ማርያም በመስቀሉ ሥር
ለዮሐንስ ተሰጥታው “ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ወደ
ቤቱ ወሰዳት” ይላል፡፡ /ዮሐ ፲፱፥፳፯/ ሥጋዋን
መላእክት ነጥቀው ወደ ሰማይ ሲወስዱትም
አብሯት ተነጥቋል፡፡ ይህ ሐዋርያ በወንጌሉ ዐሥራ
አራት ጊዜ ማርያም የሚባሉ ሴቶችን ስም
ቢጽፍም አንድም ጊዜ እመቤታችንን በስሟ
አልጠራትም፡፡
ነገሩን አልን እንጂ እሱማ መጽሐፍ ቅዱስን
ስንመረምር አምላክን ከወለደች ጀምሮ
ከመላእክትም ወገን ሆነ ከሰዎች ወገን እሷን
የጠሩበት መንገድ ሲቀይሩ አይተናል፡፡አምላክን
ከመጸነሷ በፊት “ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር
ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ” ሲሉ የነበሩት
መላእክት ከወለደች በኋላ ግን “ሕጻኑና እናቱን
ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ” ሲሉ እናገኛለን፡፡ ሉቃ
፩፥፴ ማቴ ፪፥፵፫ አክስቷ ኤልሳቤጥ ልትጠይቅ
በሔደች ጊዜ ኤልሳቤጥ “የጌታ እናት አለች
እንጂ” እንደ ዝምድናዋ “ማርያም” ብላ
አልጠራቻትም፡፡ ሉቃ ፩፥፵፫
ይህ የሆነበት ምክንያት ድንግል ማርያም እጅግ
ታላቅ የክብር ስሟ “እናቱ” “የኢየሱስ እናት”
“የጌታ እናት” “የአምላክ እናት” የሚለው ስለሆነ
ነው፡፡ አንዲት እናት የታወቀ የከበረ ዝነኛ ልጅ
ካላት ለከሟ ይልቅ የእገሌ እናት ተብላ መጠራቷ
የተለመደና ተገቢ ነው፡፡ እመቤታችን ሰማይና
ምድር በእጁ የሠራው የገናናው አምላክ
ለእግዚአብሔር እናቱ ሆናለች፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው
በስሟ ከመጥራት ይልቅ በክብር ስሟ “የኢየሱስ
እናት” ብሎ ሊጠራት ወደደ፡፡ ይህን የቅዱስ
ዮሐንስ የመላእክት የቅዱሳኑ ትውፊትና የጉባኤ
ኤፌሶን ውሳኔ ይዘን እኛም ማርያም ከማለት
ይልቅ ወላዲተ አምላክ እመ አምላ እመቤታችን
እመ ብርሃን እንላታለን፡፡

የወላዲተ አምላክ ምልጃዋ ረድኤቷ አይለየን!!

ከቃና ዘገሊላ መጽሐፍ
በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
ከገጽ ፴፬-፴፭
Deacon Henok Haile
13.0K views , 10:16
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-05-05 20:15:31 + የኤማሁስ መንገደኞች እና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ +

ፊልጶስ ለጃንደረባው ከትንቢቱ ትርጓሜ ተነሥቶ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ ውጤቱ እንጂ ይዘቱ ያልተጻፈልን ይህ በፍጥነት በሚሔድ ሰረገላ ላይ የተሰበከ ስብከት እንዴት ያማረ ይሆን? የጦርነት ስንቅ ተሸከመው በመጋለብ ፈንታ ወንጌላዊውን ከአዲስ ተማሪው ጋር ይዘው የጋለቡ እነዚያ ፈረሶች ምንኛ የታደሉ ናቸው? በክፋቱ ከነፈረሶቹ በባሕር የሚሠጥም ፈርዖንን የያዙት ፈረሶች ያልታደሉ ከሆኑ ወንጌል ተሸክመው የጋለቡና እንደ ግብፅ ፈረሶች በውኃ በመስጠም ፈንታ ከውኃ ዳር ባለቤታቸውን ሊያስጠምቁ ተለጉመው የቆሙት እነዚህ ፈረሶች እንዴት የከበሩ ናቸው? ያንን ‹የፈረስ ወዳጅ› የፊልጶስን ስብከቱን ሰምተውት ይሆን? ምነው እንደ በለዓም አህያ አንደበታቸው በተከፈተና ስለዚያ ፍቱን ስብከት በነገሩን?

ጃንደረባውን በዚያ ቅጽበት የለወጠ ፣ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች የሰሚውን ልብ ያቀለጠ ይህ ስብከት እንዴት ያለ ይሆን?

የኤማሁስ መንገደኞች ከኢየሩሳሌም ሲወጡ ክርስቶስ ከመካከላቸው ሆኖ እንዳናገራቸው ጃንደረባውም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ሲጓዝ ፊልጶስ ከመንገድ አነጋገረው፡፡ የኤማሁስ መንገደኞች ጌታን ‹ከእኛ ጋር እደር› ብለው እንደለመኑት ጃንደረባውም ፊልጶስን ከእኔ ጋር ተቀመጥ ብሎ ለመነው፡፡ (ሉቃ. ፳፬፥፲፫-፴፩)

የኤማሁስ መንገደኞች የነቢያት መጻሕፍት ሲተረጎሙላቸው ልባቸው እንደተቃጠለ ጃንደረባውም ፊልጶስ በተረጎመለት የትንቢተ ኢሳይያስ ትርጓሜ ልቡ ተቃጠለ፡፡ የኤማሁስ መንገደኞች ከጌታ እጅ ቁራሽ ተቀብለው ዓይናቸው ሲከፈት ጌታ ተሰወራቸው ፤ ጃንደረባው ደግሞ ጥምቀትን ተቀብሎ ፊልጶስ ከእርሱ ተነጠቀ፡፡ እነርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሊናገሩ ሲገሰግሱ ጃንደረባውም ወደ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሰ፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ : ገጽ 105
22.1K views , 17:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-29 02:11:28 ከዓመት እስከ ዓመት ግርግር በማያጣትና ሁሌም በሰውና በገበያተኛ በተጨናነቀችው ኢየሩሳሌም ውስጥ እየተጓዝን ነው:: ጥንታዊትዋ የኢየሩሳሌም ከተማ በአሁኑ ሰዓት በአራት ሩቦች ተካፍላ ትተዳደራለች:: የክርስቲያን እርቦ ፣ የሙስሊሞች እርቦ ፣ የአርመኖች እርቦ እና የአይሁድ እርቦ ይባላሉ::

ለሦስቱ አብርሃማውያን እምነቶች (Abrahamic religions) ለአይሁዳዊነት ለክርስትናና ለእስልምና ትልቅ ፋይዳ ባላት ኢየሩሳሌም "አርብ አርብ" ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሽብርና ግርግር አለ:: በሁሉም ሩቦች ተሳላሚዎች ፣ ጎብኚዎች ፣ ሻጮች ፣ ገዢዎሽ እስከ እኩለ ሌሊት ይርመሰመሳሉ::

ዘንድሮ እግር ጥሎኝ ከአንድ ወዳጄ ጋር በአይሁድ እርቦ (Jewish quarter) በኩል ሳልፍ አንድ ልብ የሚነካ ሥዕል ዓይኔ ውስጥ ገባ:: ሥዕሉን ሳይ ዕንባ በዓይኔ ሞላ:: የኢሳይያስ 53ቱን የሕማም ሰው ፣ የማይናገረውን በግ በአንገቱ የእሾህ አክሊል ጌጥ አድርገውለት እንዲህ ሆኖ ሳየው ችዬ የማላነበውን ኢሳይያስ 53 በሥዕል ሲያመጣብኝ ከማልቀስ ውጪ ምንም አቅም አልነበረኝም::

ነቢዩ ኢሳይያስ ሳይናገር በፊት የሚቀበለው እንደሌለ አውቆ "የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?" ብሎ የተጨነቀበትን ይህን አስጨናቂ ራእይ እንዴት እንረሳዋለን? ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባስ በቀር ኢሳይያስ 53 ን አንብቦ "ማን አምኖአል?" (ሐዋ. 8:26) የእግዚአብሔር ክንዱ የተባለ ክርስቶስስ ለማን ተገልጦአል?

በግርፋቱ ብዛት ፊቱ በደም ተለውሶ "ባየነው ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም" የተባለበትን ውበቱ ስለ እኛ የጠፋው የሕማም ሰው እንዴት ከሕሊናችን ተሰወረ?

"እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።ተጨነቀ ተሠቃየም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" የሚለው ቃል ምንኛ ያስጨንቃል? ቆስሎ የሚፈውስ ታምሞ የሚያድን ታስሮ ነፃ የሚያወጣውን የእግዚአብሔር በግ ለመግለፅ ቃላት አቅም ቢያጥራቸው እንዲህ በብሩሽ ኃይል ተሥለው ሳያቸው ሁሉን ነገር ዘነጋሁት::

አንድ ልብሱ በቀለም ያደፈ ሰው በሥዕል ጋለሪው ደጃፍ ቁጭ ብሎ ይፈርማል:: እንደ መታደል ሆኖ ሰውዬው የሥዕሉ ባለቤት UDI MERIOZ ነበረ:: ቀርቤ ስለ ሥዕሉ የተሰማኝን ስነግረው እሱም ስሜቱ ተነካ:: "ይሄንን ሥዕል እኔ ብሥለውም የእኔ ፈጠራ አይደለም:: ሸራውን ወጥሬ በቀለም ላይ የሠራሁት እኔ ነኝ:: ነገር ግን ከመሣሌ በፊት በተደጋጋሚ በሕልሜ አየው ነበር:: የሣልሁትም ያየሁትን ነው" አለኝ:: ሥዕሉንም ፈርሞ ለእኔና ለወዳጄ ሠጠን::

ቅዱስ ኤፍሬም "ጌታ ሆይ ረዥሙን ሥቃይህን ማን ሊገልጸው ይችላል?" እንዳለው የጌታን መከራ የሚገልፅ አንደበት የሚሥለው ብሩሽ ባይኖርም ለአፍታ ግን እንዲህ በየሰዉ ላይ ባሳረፈው ጸጋ ሕማሙን ያስታውሰናል::

ይህ የበገና መዝሙር ግጥም ግን ከሕሊናዬ መጣ

"ያ ሁሉ መከራ እንዴት ይግባ ልቤ
አልበጠስ አለኝ የኃጢአት መረቤ

ተው ልቤን ስበረው ልመንህ አጥብቄ
መቼ ሕይወት ሆነኝ ቃልህን ማወቄ
ቃሉን ተናጋሪ ምግባር የሌለኝ
ተገርፎአል ተሰቅሎአል የምል ብቻ ሆንኩኝ" (ዘማሪት አዳነች አስፋው)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
5.4K views , 23:11
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-28 05:15:14

9.9K views , 02:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-25 04:48:30 ++ እንዴት ወድቀን እንዴት ተነሣን? ++

ኦሪት ዘፍጥረት ስለሰው ልጅ ውድቀት ሲናገር ዕባብና ሔዋን ያደረጉትን ቃለ ምልልስና በዕባብ ምክር ሠጪነት የሰው ልጅ እንዴት ከገነት እንደተባረረና ጸጋውን እንደተገፈፈ ያስረዳል፡፡

ይህንን የዕባብና የሔዋን ቃለ ምልልስን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብናወጣው ወይም ኦሪት ዘፍጥረት የአዳምና ሔዋንን ከገነት መባረር ብቻ የሚናገር ቢሆን ኖሮ ‹ምን አጥፍተው ነው የተባረሩት?› ወደሚል ግራ መጋባት ውስጥ እንገባ ነበር፡፡

ወዳጄ የዕባብና ሔዋንን ቃለ ምልልስ መስማት ሳይችል የአዳምና ሔዋንን ከገነት የመባረር ታሪክ ለመረዳት የሚችል እንደሌለ ሁሉ የእመቤታችንንና የቅዱስ ገብርኤልን ቃለ ምልልስ ሳያነብ የሰው ልጅን ወደ ገነት የመግባትና የመዳን ታሪክ ለመረዳት የሚችል ሰው ማንም የለም፡፡


ቅዱስ ጳውሎስ በአዳምና በክርስቶስ ተምሳሌት (Christ-Adam analogy) አድርጎ ጻፈ:: ክርስቶስን ‹ኋለኛው አዳም› ብሎ ጠርቶታል፡፡ (1ቆሮ. 15፡45) አዳምንም ‹አዳም ይመጣ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነው› በማለት የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ (ሮሜ. 5፡14) የሰው ልጅ ተፈጥሮ ታሪክ የተጀመረው ከአዳም ታሪክ እንደነበር የሰው ልጅ አዲሱ ተፈጥሮ ታሪክም የተጀመረው በዳግም ፍጥረት (Recaptulation) በተፈጠርንባት በቀራንዮ ነው፡፡

ይህም ንጽጽርም በኁዋላ ዘመን ለተነሡ እንደሰማዕቱ ዮስጦስና እንደ ያዕቆብ ዘሥሩግ ያሉ ሊቃውንት የማርያምና ሔዋን ተምሳሌትን (Mary eve analogy) እንዲያመሠጥሩ መነሻ ሆናቸው:: ያነጻጸሩት ሔዋንን ከማርያም ብቻ ሳይሆን እንዴት ወደቅን እንዴት ተነሣን የሚለውን ነው::

ሔዋን ለውድቀታችን መነሻ ነበረች ማርያም ግን ለመነሳታችን ምክንያት ሆነች:: ሔዋንን ሰይጣን በዕባብ ተመስሎ አነጋገራት:: ማርያምን ግን እግዚአብሔር በገብርኤል ሆኖ አነጋገራት:: ሔዋን የዕባቡን ቃል በመስማትዋ ከገነት ወጣን : ማርያም የገብርኤልን ቃል በመስማትዋ ወደ ገነት መለሰችን::

የዕባብና የሔዋንን ቃለ ምልልስ በቁጭት እናነበዋለን:: የድንግልና የገብርኤልን ምልልስ ግን በደስታ እንጸልየዋለን:: ያ ቃለ ምልልስ እኛን ወደ ሕይወት የመለሰ ቃለ ምልልስ ነው:: የ15 ዓመትዋ ብላቴና ማርያም ምድራዊያንን ሁሉ ወክላ ከሰማያዊው መልእክተኛ ጋር ተነጋግራ ዕርቃናችንን አለበሰችን:: የድሆች ልጅ የሆነችው ብላቴና የመላእክትን አለቃ በጥያቄ አስጨንቃ መርምራ ከጭንቃችን ገላገለችን::

ሔዋን የዕባብን ምክር ሳትመረምር ተቀበለች:: ድንግል ማርያም ግን የገብርኤልን ብሥራት መረመረች:: ለሔዋን ዲያቢሎስ "እግዚእብሔር እንደርሱ እንዳትሆኑ ብሎ ከለለላችሁ" ብሎ ከፈጣሪ አጣላቸው:: ሔዋን ሁሉን አዋቂ ለመሆን ቸኩላ ከባልዋ ጋር ፈጠነች:: ድንግል ማርያም ግን ሁሉን አዋቂ ልሁን አላለችም :: "ወንድ ስለማላውቅ እንዴት ይሆንልኛል? ብላ ጠየቀች : ሔዋን አምላክ ለመሆን ተታለለች:: ትሕትና የሞላባት ድንግል ግን "እነሆኝ የጌታ ባሪያው ነኝ" ብላ ተቀበለች::

ይህች ድንግል ገብርኤልን ሰምታ የሕይወትን ዛፍ አበላችን:: ይህች ድንግል ይሁንልኝ በማለትዋ የተጠመቅን ሁላችን ክርስቶስን ለበስን:: በእርስዋ ይሁንልኝ ማለት ኪሩብ ሰይፉን ጣለ : ከጥበቃም ተገላገለ:: እኛም ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ ታደልን::

ብዙ ሰው " ሔዋን ለመውደቃችን ምክንያት ናት " ሲባል ይስማማል:: ድንግል ማርያም ግን ለመዳናችን ምክንያት ሆነች የሚለውን ግን አንዳንዶች ለመቀበል ይቸገራሉ:: ሔዋን ለመውደቃችን ካደረገችው ይልቅ ድንግል ማርያም ለመነሣታችን ያደረገችው ይበልጣል!

የድኅነታችን መጀመሪያ የሆነችውን ይህችን ድንግል ክብርዋን በሕሊናችን እንሳለው:: እሳታዊ መልአክ ቆሞ የዘመረላት ድንግል : አባትዋ ዳዊት ከሩቅ ሆኖ እያያት "ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ጆሮሽን እዘንብዪ" እያለ የገብርኤልን ቃል እንድትሰማና ከሲኦል እንድታወጣው የሚማጸናትን ድንግል : ወንድምዋ ሰሎሞን "እኅቴ ሙሽራ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም" እያለ የቀረበላትን 'የተባረክሽ ነሽ' የሚል ምስጋና እንድትቀበል የሚዘምርላትን : በእጆችዋ ሐርና ወርቅን : በማኅጸንዋ ሰውና አምላክን : በመውለድዋ ሰውና መላእክትን አስማምታ የፈተለችና ያዋሐደችዋን ይህች ድንግል እስቲ ለአፍታ እናስባት:: የባቢሎንን ሰባት እጥፍ የነደደ እሳት ያቀዘቀዘው ገብርኤል በፊትዋ በትሕትና አደግድጎ የቆመላትና ዘካርያስን ዲዳ ትሆናለህ ባለበት አንደበቱ "አንቺ የተባረክሽ ነሽ " እያለ የሚማጸናትን የዐሥራ አምስት ዓመት ብላቴና እስቲ እናስባት! ዓላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ይህች ማናት?

ሽማግሌ አባትዋን ቅጠል ከለበሰበት ዛፍ አውጥታ ልጅዋን ሸማ አድርጋ ያለበሰች : እናትዋን ሔዋንንም የሚጎዳ ማሠሪያዋን ፈትታ ቁስልዋን ያከመች የሔዋን መድኃኒት ይህች ድንግል ማን ናት? የእርስዋን ክብር በኃጢአተኛ ብዕር እንደምን እጽፈዋለሁ?
ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ያለውን ብዬ ብዘጋው ይሻለኛል
"የድንግል ማርያምን ክብር ከመግለጽ ፀሐይን ከነብርሃንዋና ከነሙቀትዋ መሣል ይቀልላል"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ወተዘከርኒ ለኃጥእ ገብርኪ ተክለ ማርያም
ታኅሣሥ 21 2012
አዲስ አበባ
Deacon Henok Haile
Deacon Henok Haile - ብትግርኛ
Dn Heenook Hayilee - Afaan Oromoo
Deacon Henok Haile - English Sermons
10.5K views , 01:48
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-04-19 19:08:05
7.3K views , 16:08
ክፈት / አስተያየት ይስጡ