2022-07-09 05:46:20
"በንስርም ክንፍ ተሸከምኋችሁ!"
ንስር ንጉሠ አዕዋፍ ነው ፤ በመብረርም ፈጣንና
ጠንካራ የሆነ ነው፡፡ ረዥም ዘመን የሚኖር ፣ ከሩቅ አጥርቶ
የሚያይ ፣ እስከ ተራሮች ከፍታና ከደመናት በላይ
ለመብረር የሚያስችሉ ኃያላን አክናፍ ያሉት ነው፡፡
እንዲሁም ንስር ለጫጩቶቹ ርኅሩኅ ነው፡፡ በጥበብ
ይንከባከባቸዋል ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙም
ያለማምዳቸዋል፡፡
ከእነዚህ ተነጻጻሪ ባሕርያት የተነሣ እግዚአብሔር በትሕትና ራሱን ከንስር ጋር
አመሳስሏል፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፣ ሁሉን ቻይ ፣ ሁሉን ተመልካች (ሁሉን የሚያይና
የሚያውቅ የጥበብ ምንጭ) ፣ ምሕረትን የተሞላ ፣ ለሕዝቡ የሚራራና ወደ ድኅነት
የሚመራቸው ነው፡፡
ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን መርቶ ከግብፅ ባወጣቸውና ከፈርኦን ሠራዊት ጠብቆ
በተአምር ቀይ ባሕርን ባሻገራቸው ጊዜ እንዲህ ብሏቸው ነበር ፡- ‹‹በግብፃውያን ያደረግሁትን በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋቸችሁ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል፡
፡›› (ዘጸ. ፲፱፥፬)
በንስር ሕይወት ውስጥ ካሉት ምሥጢራት አንዱ ሁልጊዜ ጎጆውን በከፍታ ላይ
መሥራቱና በአለታማ ቋጥኞችና ምሽጎች ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኢዮብ
ጥበቡንና ኃይሉን ሲያሳየው ያለውን ልብ በሉ ‹‹በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን?
ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን? በገደል ላይ ይኖራል በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል፡፡
በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጎበኛል ፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች፡፡›› (ኢዮ.፴፱፥፳፯)
ንስር ስለምን ከፍ ብሎ ጎጆውን በተራሮች ጫፍ ላይ ይሠራል ?
እንደ አዳኞችና አራዊት ያሉ ጠላቶቹ ሊደርሱበት ከማይችሉበት ስፍራ ለመገኘት
ብሎ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ጎጆው ደርሶ ጫጩቶቹን ሊበላበት የሚችል ሌላ ጠላት አለ፡፡
ይህም ጠላት እስከዚያ ከፍታ ድረስ እስኪደርስ በልቡ ሊሳብ የሚችለው ዕባብ ነው፡፡
ዕባቡ ዘልቆ እንዳይገባ ጎጆውን በመጠን ብዙ በሆኑ
እሾኆች ከውጪ በኩል ያጥረዋል፡፡ የጎጆው ውስጠኛ ክፍል
ደግሞ በላባዎች የተደራጀ ሞቃታማና ምቹ ነው፡፡ ውጪው
ግን በእሾኽ የታጠረ ነው፡፡ ታላቁ ንስር ለጫጩቶቹ ጥሩ
እንክብካቤ ያደርጋል፡፡ የሚበሉትን ያቀርብላቸዋል ፣ በክንፎቹ
እያንዣበበ ይጋርዳቸዋል ፣ በአፉ (በመንቆሩ) ይመግባቸዋል፡፡
ትንንሾቹ አንስርት (ንስሮች) እንዳሻቸው እንዲኖሩ የተተዉ
ቢሆኑ ኖሮ ለዘላለም ከጎጆአቸው ባልወጡ ነበር፡፡
ስለዚህ ጊዜው ደርሶ ጫጩቶቹ ሲያድጉ ታላቁ ንስር የመብረር ችሎታቸውን
ይፈትናል ፤ ጎጆውንም መትቶ ያነቃንቀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መገፋቱ ጠንከር ሲል ጎጆው
ከተራራው ጫፍ ወደ ዝቅተኛው ጫፍ ሊወድቅ ይችላል፡፡
ጎጆው በተነዋወጸ ጊዜ ከውጪ ያሉት እሾኾች ወደ ውስጥ ይገባሉ ፤ በጫጩቶቹም
ላይ መወጋትንና ሕመምን ያስከትላሉ፡፡ ክንፎቻቸውን ያንቀሳቅሳሉ ለመብረርም ይሞክራሉ፡
፡ ከተሳካላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመብረርና ንጹሑን የሰማይ አየር እየተነፈሱ ለመደሰት
ይችላሉ ፤ ዳግመኛም ወደ ጎጆአቸው በፍጹም አይመለሱም፡፡ በዚህም ተልእኮውን በሚገባ
ያለችግር በማከናወኑ ታላቁ ንስር ደስታ ይሰማዋል፡፡
የጫጩቶቹ የክንፋቸው ላባ በበቂ ሁኔታ ካላደገና መብረር ሳይቻላቸው ከወደቁ ታላቁ
ንስር ፈጥኖ ክንፎቹን ዘርግቶ ይይዛቸዋል ፤ በክንፎቹም ይሸከማቸዋል፡፡ ለተጨማሪ
ቆይታም ወደ ጎጆአቸው ይመልሳቸዋል፡፡ ይህንን ዑደት መብረር እስከሚችሉ ድረስ
ይደጋግመዋል፡፡ አይደንቅም ትላላችሁ?
‹‹ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ ክንፎቹን ዘርግቶ
ወሰዳቸው ፤ በክንፎቹ አዘላቸው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ብቻውን መራው›› ዘዳ.፴፪፥፲፩
ከላይ እንደተገለጠው እግዚአብሔር ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እኛም ከድንቅ
ፍጥረቱ ከንስር ሕይወት አንዳንድ ቁም ነገሮችን እንቀስማለን፡፡
ምእመናን የንስር ጫጩቶችን ይመስላሉ!
የንስር ጫጩቶች ደካሞችና በራሳቸው ለመቆምና በራሳቸው ለመኖር የማይችሉ
ናቸው፡፡ የሰው ልጅም ሲወለድ በራሱ መብላት መጠጣት ፣ መሄድ ፣ መናገር ፣ማሰብ ፣ ፍላጎቶቹን መፈጸም የማይችል ሆኖ ነው የሚወለደው፡፡ በተመሳሳይ
በመንፈሳዊ ሕይወቱም ጠላቶቹን ኃጢአትን ፣ ሰይጣንን ፣ የሥጋ ምኞትንና
የዚህችን ዓለም መስህብነት ለመቃወም ደካማ ነው፡፡
ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ይህንን እውነታ ከአስከፊው ውድቀቱ በኋላ በስድስተኛው
መዝሙሩ ሲገልጥ ‹‹አቤቱ በቊጣህ አትቅሠፈኝ በመዓትህም አትገሥጸኝ፡፡ ድዉይ ነኝና
አቤቱ ማረኝ›› ብሏል፡፡ (መዝ.፮፥፩-፪) የእግዚአብሔር ንቁ ዓይኖች ፣ ኃያላን ክንዶቹና
ሁልጊዜ በላያችን የሚጋርዱን ክንፎቹ ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን ደካማነታችንንና
ኃጢአተኛነታችንን እስካላመንን ድረስ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ወደ እኛ ፈጽሞ
አትመጣም፡፡
በሌላ ያማሩ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል ፡- ‹‹በሰማያት ላይ ለረድኤትህ
በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም፡፡ መኖሪያህ
የዘላለም አምላክ ነው ፤ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፡፡›› (ዘዳ.፴፫፥፳፯)
የንስር ጫጩቶች እንደ እኛ አላዋቂዎች ናቸው፡፡
እኛ ከትምህርታችንና ከዲግሪዎቻችን ያገኘነው ምንም
ይሁን ምን አላዋቂነታችንንና የእግዚአብሔር መሪነት
እንደሚያስፈልገን ማመን ይገባናል፡፡ በመንፈሳዊው ዕይታ
የሰው ልጅ አላዋቂ ነው፡፡ ወደፊት ስለሚመጣው ነገር ፣
ከሞት በኋላም ስላለው ነገር ፣ ሌላው ቀርቶ ስለ ራሱና
በፍጥረታት ውስጥ ስላሉ በሚልዮኖች ስለሚቆጠሩ ነገሮች እንኳን አያውቅም ፡፡
ማየት የማይችል ከመሆኑም የተነሣ የቃለ እግዚአብሔርና የመንፈስ ቅዱስ
ብርሃንነት እንዲሁም ምክረ ካህን ያስፈልገዋል፡፡እግዚአብሔር እኛን የሚንከባከበት መንገድ ከንስር ጋር ይመሳሰላል!
ንስር ከፍ ከፍ እንደሚልና ጎጆውን በከፍታ ላይ እንደሚሠራ እግዚአብሔርም
ልጆቹ ከሌላው ሰው በተለየ መዓርግ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በቅድስና ሕይወት
እንድንኖርና ከእርሱ ጋር ለዘላለም በመንግሥቱ ለመኖር ራሳችንን እንድናዘጋጅ
ይፈልጋል፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት ከተወለድን ጀምሮ የመንግሥተ
ሰማያት ዜጎች ሆነናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ፫፥፲ ፡ ‹‹እኛ ሀገራችን በሰማይ
ነውና›› ብሏል፡፡ ከሰማያዊው አምላክ ተወልደናል ፤ ምግባችን ቃለ
እግዚአብሔርም ፣ ሥጋ ወደሙም ፣ ጸሎትና አንድነታችንም ሁሉም ከላይ ነው፡፡
‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው ፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ
ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡››
(ያዕ.፩፥፲፰)
ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ
በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ
በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር
ተሰውሮአልና ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ
ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ፡፡›› (ቈላ.፫፥፩-፬)
እግዚአብሔር ጎጆአችንን በእሾኾች ያጥረዋል!
18.3K viewsካልባረከኝ አለቅህም, 02:46