Get Mystery Box with random crypto!

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የሰርጥ አድራሻ: @deaconhenokhaile
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 64.23K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ቻናል በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ፈቃድ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ነው::
@deaconhenokhaile
"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን"
2ኛ ቆሮ. 2:14

Ratings & Reviews

2.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 4

2023-09-17 05:34:30

19.5K views , 02:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-17 02:37:04 ትሁት ልቦና [NEW VIDEO] || ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ


15.9K views , 23:37
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-16 11:50:30 + አባቶቻችን እንዲህ አሉ +

"በኃጢአት በወደቅህ ጊዜ ተስፋ ቆርጠህ ጸሎትህን እንዳታቆም። ንስሓ እስከምገባ ድረስ ብለህ ጸሎት ካቆምክ መቼም ንስሓ አትገባም። ምክንያቱም ጸሎት ራሱ የእውነተኛ ንስሓ መግቢያ በር ነው" ቅዱስ ቄርሎስ ሳድሳዊ

"ሰዎች አንድ ሰው ተነሥቶ ሌላውን ሲገድል ወንጀለኛ ነህ ይሉታል። አንድ ላይ ተሰባስበው ብዙ ሰዎችን ሲገድሉ ግን ውጊያ ይሉትና መግደላቸውን ጀግንነት ይሉታል" ቅዱስ ቆጵሮሳዊ

"ሰዎች የሚያብዱበትና እንደነሱ ያላበደ ሰው ሲያዩ "እንደኛ ስላልሆንክ አብደሃል" የሚሉበት ዘመን ይመጣል"
ቅዱስ እንጦንዮስ

"መካሪ አያስፈልገኝም የማለትን ያህል ታላቅ ትዕቢት የለም"
ቅዱስ ባስልዮስ

"ይህንን ካስታወስክ በሰው መፍረድ ታቆማለህ:: ይሁዳ ሐዋርያ ነበር:: ከጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ነፍሰ ገዳይ ነበር" ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

"የክርስቲያኖች መሣሪያ በእጃቸው ሰይፍን መታጠቅ ሳይሆን እጃቸውን ወደላይ ለጸሎት መዘርጋት ነው"
ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ

"እግዚአብሔር ለአብርሃም "ከሀገርህ ውጣ ከወገኖችህ"ተለይ ብሎት ነበር። በዚህ ጥሪ እግዚአብሔር ሁላችንንም የተወለድንበት ዘር እንድንተው ይጠራናል። ሰማዕቱ ዮስጦስ (100 AD-165 AD)

"ክርስቶስ ጴጥሮስን "ሰይፍህን ወደ ሰገባው አስገባ" ሲለው ትጥቅ ያስፈታው ጴጥሮስን ብቻ ሳይሆን እንደ ጴጥሮስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ነበር" ሊቁ ጠርጡለስ

‹‹ይጸልያል ነገር ግን የሌሎችን ጸሎትም ይሰማል፡፡ ያለቅሳል የሌሎችን ዕንባ ግን ያብሳል፡፡ ሰው ነውና አልዓዛር ወዴት እንደተቀበረ ጠየቀ፡፡ አምላክ ነውና አልዓዛርን ከሞት አስነሣ፡፡ እርሱ በርካሽ ዋጋ ያውም በሠላሳ ብር ብቻ ተሸጠ፡፡ ነገር ግን ዓለምን በውድ ዋጋ በከበረ ደሙ ገዛ፡፡ እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ እርሱ ግን የእስራኤል እረኛ የዓለምም ሁሉ ጠባቂ ነበረ፡፡ እንደ በግ ዝም አለ ነገር ግን እርሱ በምድረ በዳ በሚጮኽ ሰው ድምፅ የተሰበከ ቃል ነበር፡፡ እርሱ የተሰቃየና የቆሰለ ነበር ፤ ሁሉንም በሽታና ቁስል ግን ይፈውስ ነበር›› ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ

"ለቤተ መቅደስህ ተክል ያደረግኸኝ፡፡ አቤቱ ሆይ የውጭ ተክል አታድርገኝ፡፡ የጽድቅ ተክል አድርገኝ፡፡ የኃጢአት አይደለም፡፡ የዕውነት ተክል አድርገኝ የሐሰት አይደለም የፍቅር ተክል አድርገኝ የጽል አይደለም፡፡

የመጻሕፍት መጀመሪያ የምትሆን ኦሪት ደመና የምትጋርደኝ፡፡ ከቅዱስ ወንጌል ፈሳሽ የምጠጣ ከጎንህ ከፈሰሰው ደም የምረካ ልሁን፡፡ በናትህ በድንግል ጸሎት የሃይማኖት አበባ ላብብ፡፡ የጽድቅ ፍሬን ላፍራ ከቅዱሳንህ ሐዋርያትም ከቃላቸው ፍሬ የተነሣ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የተባረከ የወይን ቦታ ልባል የጽድቅን ፍሬ የሚያስቀረውንም የኃጢአት እሾህ ጠምዝዘው ከደጁም አሜከላውን አረሙንም ሙጃውንም ንቀለው፡፡ አቤቱ ከኔም አርቀው ሥርዓትህን የሚሠሩትን ያበባቸውን ፍጻሜ እንዳፈራ አድርገኝ" ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት 26 2011
ጅማ ፣ ኢትዮጵያ

https://t.me/deaconhenokhaile
18.3K views , 08:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-14 18:29:03 + ከአንተ ባላውቅም ...+

በገነተ አበው (The Paradise of Fathers) መጽሐፍ ላይ ይህ ታሪክ ተጽፎአል::

አንድ መነኩሴ በበአቱ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ አንድ ቃል ሊገባው አልቻለም:: ለመረዳት በጣም ሲያስቸግረው "ይኼን ቃልስ እንዲገልጽልኝ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ አለብኝ" ብሎ ወሰነ:: ነቢያቱ ያደርጉት እንደነበረውም እግዚአብሔር የቃሉን ፍቺ እስኪገልጽለት ድረስ መጾምና መጸለይ ጀመረ:: ነገር ግን ለሰባ ሳምንታት ያህል እየጾመ ቢጠባበቅም ምንም ነገር ሊገለጽለት አልቻለም:: በየሳምንቱ መጨረሻ ቃሉን ደግሞ ሲያነበውም የበለጠ እየተወሳሰበበት ሔደ እንጂ ጨርሶ ሊገባው አልቻለም::

በመጨረሻም ተስፋ ቆረጠ:: ስለዚህ ሌላ መነኩሴ ጋር ሔዶ ስለዚህ ቃል ትርጉም ሊጠይቀው ወሰነ:: በአቱን ዘግቶ መንገድ ሊጀምር ሲዞር ግን የእግዚአብሔር መልአክ በፊቱ ቆሞ ታየው::

"አይዞህ አትፍራ የፈለግኸውን የቃሉን ትርጉም ልገልጽልህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬያለሁ" አለው::

መነኩሴው ግራ ገባው
"የጌታ መልአክ ሆይ ሰባ ሳምንት ሙሉ እየጾምሁ እንዲገልጥልኝ ስለምን ቆይቼ ምንም መልስ አላገኘሁም:: አሁን ተስፋ ስቆርጥ እግዚአብሔር ስለምን መለሰልኝ?" አለ በፍርሃት ውስጥ ሆኖ

"እግዚአብሔር ሰባ ሳምንታት ከጾምኸው ጾም ይልቅ ወንድምህን ለመጠየቅ በመሔድ ያሳየኸውን ትሕትና ተቀብሎታል" አለው::

አላዋቂ መስሎ መታየትን ያህል የምንፈራው ነገር የለም:: "አላውቀውም አንተ ንገረኝ" ከማለት ይልቅ ብዙ ሰው ሞት ይመርጣል:: ትንሽ ተምሬያለሁ የሚል ሰውማ ጥያቄ መጠየቅ ዲግሪውን ማቃጠል ይሆንበታል:: የብዙዎቻችን ትሕትና የሚፈቅድልን ሰዓት ለመጠየቅ ብቻ ነው:: "ከአንተ አላውቅም ..." ብለው የሚጀምሩ ዐረፍተ ነገሮች ራሱ ልብ ብለን ከሰማናቸው ይዘታቸው "ከእኔ አታውቅም" ነው::

የእውቀታችንን ውስንነት ለማመን የሚከብደን በሥጋችን ውስጥ ያለችው ለባዊት ነፍሳችን በሥጋዊ እውቀት ራስዋን መገደብ ስለምትቸገርም ነው:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "አሁን ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ" ብሎ የእውቀትን ውስንነት ማመን ግን ዕረፍት ይሠጣል:: 1ቆሮ. 13:12

በመንፈሳዊው ዓለም እንዲህ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ አሳዛኝ እውነታ ነው:: "የቀለም ቀንድ" ፣ "የእውቀት ምንጭ" ፣ "መልስ በጉንጩ"፣ "ተጠያቂው" የሚለውን የክብር ሥፍራ ስንፈልግ በማናውቀው ጉዳይ ሌሎችን ከመጠየቅ ይከለክለናል:: አላውቀውም አላነበብኩትም አልሰማሁትም ከማለት ይልቅ ሁሉን አዋቂ ሆኖ ለመገኘት ስንል የምንበላቸው ዕፀ በለሶች ብዙ ናቸው::

"ብዙ የማውቀው ነበረ ሰዓት ገደበኝ እንጂ" ብሎ ውስን እውቀቱን ባሕር ለማድረግ የሚደክምና ሰዎች ከተናገረው ከጻፈው በላይ አድርገው እንዲያስቡት የሚገፋፋ ሰው የሚወለደው ካላዋቂነት ፍርሃት ውስጥ ነው:: በጥቂት ንባብ ውስጥ ራስን በጥልቅ ምሁር ዓይን ማየትና "እኔ የማውቀው ማወቄን ነው" ማለት የአላዋቂነት ፍርሃት የሚወልዳቸው ኢሶቅራጥሶች መርሕ ነው::

ከሌላው በታች አላዋቂ መስሎ መታየትን እንፈራለን:: ስለዚህ ሌላውን ከመጠየቅና እንደ ጃንደረባው "የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?" "ነቢዩ ይኼን ስለማን ተናግሮታል?" ብሎ ከመማር ይልቅ በራሳችን ለመረዳት ብንሟሟት እንመርጣለን:: ብዙ "የእምነት" denominations የተፈጠሩትም ሌላውን ከመጠየቅ ሞት በሚመርጡ ትዕቢተኞችና "እንደገባኝና እንደተረዳሁት" በሚል አስተሳሰባቸው እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል::

"ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር" ፊልጵ. 2:3

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 2016 ዓ.ም.

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
17.8K views , 15:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-10 07:08:40 የፌስ ቡክ ገጼ በሌሎች ሰዎች hack ተደርጎአል የምታዩትን ቪድዮ ጨምሮ ማስመለስ እስከምችል ድረስ ፖስቱ የእኔ አይደለም::

Henok Haile
13.8K views , 04:08
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-08 22:58:18 + አምናለሁ እና አላምንም +

ልጁ የታመመበት አባት ነው:: ጌታን "ቢቻልህስ ልጄን ፈውስልኝ" አለው:: ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡ አለው።

ይህን ጊዜ ሰውዬው "ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው፡ አለ" ማር. 9:24

የዚህ ሰውዬ ንግግር ፍቺ የሚፈልግ ቅኔ ይሆንብኛል "አምናለሁ አለማመኔን እርዳው"

ይኼ ሰውዬ ያምናል ወይንስ አያምንም?

ያምናል እንዳንል "አለማመኔን" ይላል ፤ አያምንም እንዳንል "አምናለሁ" ይላል:: የቸገረ ነገር ነው? ሁሉን አዋቂው መድኃኔዓለም ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶት ልጁን ፈወሰለት:: እኔ አላዋቂው ግን "አምናለሁ አለማመኔን እርዳው" የሚለውን ቃል እየደጋገምኩት ቀረሁ::

እያመኑ አለማመን እንዴት ያለ ነው? ብዬ መላልሼ ሳጤነው ግን ሰውዬው የእኔኑ ድክመት እየተናገረ እንደሆነ ገባኝ::

አምናለሁ እላለሁ:: በእርግጥም በፈጣሪ መኖር አምናለሁ:: ሁሉን እንደሚችልም አምናለሁ::
ግን ደግሞ በእርሱ ታምኜ አላውቅምና በሥራዬ እክደዋለሁ:: ኑሮዬ "በሥራቸው ይክዱታል" ከተባሉት የሚመደብ ነው:: (ቲቶ 1:16) አቅዋሜ የማመን ኑሮዬ ያለማመን ነውና አምናለሁ አለማመኔን እርዳው ብል ለእኔ የሚገባ ጸሎት ነው::

ወረደ ተወለደ ተጠመቀ ተሰቀለ ሞተ ተነሣ ዐረገ ብዬ አምናለሁ:: በትሕትና መውረድን ፣ በንስሓ መወለድን ፣ በታናሽ እጅ ዝቅ ብሎ ጽድቅን መፈጸምን ፣ መከራን በትዕግሥት መቀበልን ፣ ከመከራ ሞት ወዲያ ተነሥቶ በክብር ከፍ ማለትን ግን እኔ ሕይወት ላይ አላውቀውም:: የምተርከው ክርስቶስ እንጂ የሚተረክ ክርስትና የለኝም:: ስለዚህ አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በልኬ የተሰፋ ጸሎት ነው::

መች በዚህ ያበቃል::

እጾማለሁ አለመጾሜን እርዳው::
ከምግብ እጾማለሁ ከኃጢአት ግን አልጾምም:: ሥጋ መብላት ትቼ የሰው ሥጋ በሐሜት የምበላ ነኝና እጾማለሁ አለመጾሜን እርዳሁ እላለሁ::

እጸልያለሁ አለመጸለዬን እርዳው::
ቆሜ የማደርሰው ጸሎትስ አለኝ:: ግን ልቤ ሠላሳ ቦታ ደርሶ ይመለሳል:: የምጸልየው ማናገር የማልፈልገውን ሰው በግድ የማናግር ያህል የግብር ይውጣ እንጂ ነፍሴ እርሱን ሽታ አይደለምና እጸልያለሁ አለመጸለዬን እርዳው እላለሁ::

እሰግዳለሁ አለመስገዴን እርዳውስ?
ላቤ እስኪወርድ ሰግጄ አውቃለሁ:: ልቤ ግን አንዴ አልሰገደም::

ጌታ ሆይ እመጸውታለሁ አለመመጽወቴን እርዳው:: እዘምራለሁ አለመዘመሬን እርዳው:: አስቀድሳለሁ አለማስቀደሴን እርዳው:: እማራለሁ አለመማሬን እርዳው:: ሆኜ ያልሆንሁትን አድርጌ ያላደርግሁትን ሁሉ አንተ ታውቀዋለህና እርዳኝ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጳጉሜን 3 2015 ዓ.ም.

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://t.me/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
18.0K views , 19:58
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-07 16:30:47 + አልቆም ያለ ደም+

"በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ" ሉቃ. 8:44

ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።

ደምዋ ፈስሶ አያልቅም ወይ? ዓሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ? እንዴት ያለ ሕመም ነው?! ሰው በክፉ ሽታዋ እስኪርቃት ድረስ የማይቆም ደም::

ባለ መድኃኒቶች ሊያቆሙት ያልቻሉትን የደም ጎርፍ የናዝሬቱ ባለ መድኃኒት በቀሚሱ ብቻ አቆመው:: በልብሱ ጫፍ ብቻ::

ሳያያት ሳይነካት እጁን ሳይጭንባት በልብሱ ጫፍ ብቻ የደምዋን ዝናብ እንዲያባራ አደረገው:: የሕመምዋን ማዕበል ገሠጸው::

በልብሱ ጫፍ ብቻ የሚፈውስ ሐኪም እንዴት ያለ ነው? ቀጠሮ ሳይሠጥህ ሳያናግርህ ቀና ብሎ ሳያይህ ስትነካው ብቻ የምትድንበት ከሆነ እርሱ መድኃኒት የሚያዝ ሐኪም ሳይሆን ራሱ መድኃኒት ነው:: የልብሱን ጫፍ የነካ ከዳነ ሥጋውን የበሉ ደሙን የጠጡማ ምንኛ ይድኑ ይሆን?

ሊፈውሳት አስቦ አልነበረም የዐሥራ ሁለት ዓመት ሴት ልጅ ከሞት ሊያስነሣ መንገድ ሲሔድ ግን እግረ መንገዱን የዓሥራ ሁለት ዓመት የቁም ሙትዋን ፈወሳት::

መድኃኔዓለም እንዲህ ነው:: ወደ በሽተኛው ሳይሔድ በቃሉ ብቻ ተናግሮ ይፈውሳል ፤ በሽተኛው ቤት ገብቶ በአልጋው ላይ ይፈውሳል:: ሊፈውስ ሲሔድም ይፈውሳል:: እናም የሴቲቱ አልቆም ያለ ደም በልብሱ ጫፍ ብቻ ቀጥ አለ::

ጌታዬ ሆይ የእኔንስ ደም የምታቆመው መቼ ነው?

ምን ደም ፈስሶህ ያውቃል ካልከኝ ኃጢአት የሚባል ደም ሲፈሰኝ አይታይህም? አንተስ በቃልህ "ኃጢአታችሁ እንደ ደም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች" ብለህ የለ? እንደ ደም የቀላው የእኔ ኃጢአት ነው:: ይኸው ሲፈስ ከሴቲቱ በላይ ቆየ::

ላቆመው ብል አልቆም አለኝ:: ያላሰርኩበት ጨርቅ ፣ ያልሞከርኩት ቅባት ፣ ያልሔድኩበት ባለ መድኃኒት የለም:: ገንዘቤን ከሰርኩ እንጂ ኃጢአቴ ግን መቆም አልቻለም:: እንዲያውም መጠኑ እየጨመረ ነው:: ባሕር ሆኖ ሊያስጥመኝ የደረሰ የኃጢአት ደም ከብቦኛል::

ለእኔ የሚሆን የቀሚስ ጫፍ ታጣ ይሆን? እኔ እንደ ሴቲቱ ታላቅ እምነት የለኝም ቀሚስህ ግን አሁንም ኃይል አለው:: ልትፈውሰኝ ና አልልህም ስታልፍ ግን ልዳስስህና ልዳን:: ጉዞህን ሳላሰናክል ሰው ሳይሰማ በልብስህ ጫፍ ብቻ ደሜን አቁምልኝ:: የእኔን ደሜን መግታት ላንተ ምንህ ነው? ደምህንስ አፍስሰህልኝ የለ?

እባክህን ደሜ ሳይቆም ሌላ ዓመት አልሻገር::
እኔ ኃጢአቴን "ያለፈው ዘመን ይበቃል" ማለት ቢያቅተኝም አንተ ግን ይበቃሃል በልልኝ::
በእምነት ማጣት የታጠፈውን እጄን ወደ ልብስህ ጫፍ ዘርጋልኝ:: እኔ ማቆም ያልቻልኩትን የበደል ደም ጸጥ አድርገህ "አንድ ሰው ዳስሶኛል ኃይል ከእኔ ወጥቶአል" በል:: እነጴጥሮስም ይደነቁ እኔም በሰላም ልሒድ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጳጉሜን 2015 ዓ.ም.

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
12.7K views , 13:30
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-09-06 22:10:37 በልጅነታችን ምኑም ሳይገባን በጳጉሜን ሦስት ዝናሙን ጠበል ነው ብለን “ሩፋኤል አሳድገኝ" እያልን ተጠምቀን ነበር:: አሁን ስናድግና መጽሐፍ ቅዱስ ሲገባን ደግሞ ሩፋኤል ማለት የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው ማለት እንደሆነ ስናውቅ - ቅዱስ ሩፋኤል በቁስል ላይ የተሾመ መልአክ እንደሆነ ስናነብ - የቤተ ሳይዳን ውኃ ያናወጸው መልአክ እንደሆነ ስንረዳ ትናንት ባለማወቅ የተጠመቅነውን ጠበል በደስታ እንጠመቀዋለን::

ልጅ ሆናችሁ "ሩፋኤል አሳድገኝ" ያላችሁ ሁሉ ቅዱስ ሩፋኤልን ያዕቆብ ለቅዱስ ሚካኤል እንደሠጠው ስም "ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ" (ዘፍ. 48:16) ብላችሁ ለመጥራት ውለታ አለባችሁ::

በዚህ ወቅት የታመመ ሰውም ቢኖር የሩፋኤል ዓይነት "... መልአክ ቢገኝለት መጽሐፈ እየራራለት፦ ቤዛ አግኝቻለሁና፡ ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው፡ ቢለው፥ ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል" ኢዮ. 33:23-25

ይህች በአንድ ወቅት የተጻፈች ስንኝ ነበረች :-

+ ሩፋኤል ይቅር በለኝ +

አሳድገኝ ብዬህ ሮጬ
ከልጆች ጋር ተሯሩጬ
በጠበልህ እየታጠብኩ
የውኃ ጨው እየቀመስኩ

ሩፋኤል አሳድገኝ
እንደ ታላቆቼ አድርገኝ
ብዬ እየጮህኩኝ ስጣራ
ሰምተኸኛል ከልጅ ተራ

ዘንድሮን ግን ተጠለልኩኝ
ጠበል ሲወርድ ተሸሸግሁኝ
ከበረከትህ ሸሸሁኝ
ከቡራኬህ አመለጥኩኝ
ሩፋኤል ሆይ ይቅር በለኝ

ስላበቃ ልጅነቴ
በቆሸሸ ሰውነቴ
በረከሰ ማንነቴ
እንዳላረክስ ጠበልህን
ተጠለልኩት ጥምቀትህን

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጳጉሜን 3 2012 ዓ ም
15.3K views , 19:10
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-08-30 23:23:10
14.4K views , 20:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2023-08-30 21:46:25 + ድንገት የተበጠሰ ገመድ +

የደብረ ዳሞ ገዳም በገመድ ብቻ የሚወጣ እጅግ ጥንታዊ ገዳም ነው:: ይህንን አቡነ አረጋዊ በዘንዶ የወጡትን ታላቅ ገዳም ለመውጣት በግንባታው ወቅት በአፄ ገብረ መስቀል የተሠራ ደረጃ ነበረው:: ሆኖም አቡነ አረጋዊ ደረጃውን ዳህምሞ (አፍርሰው) ብለው በማዘዛቸው እስከ አሁን ድረስ በገመድ የሚወጣበት ገዳም ሆኖአል::

የደብረ ዳሞ መውጫ ገመድ እጅግ ወፍራም ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተንጠላጥለው ወጥተው ወርደውበታል:: ይህ እጅግ ወፍራም ገመድ ለዘመናት ሲያገለግል ተበጥሶ ሰው ጥሎ አያውቅም:: በታሪክ የማይዘነጋና መሃል ላይ የተበጠሰበትና ሰው የጣለበት ቀን አለ:: (የዲያቢሎስ መተናኮል ነው የሚል አለ)

በዚያ ቀን በተበጠሰው ገመድ ላይ የወረደው መንገደኛ ጻድቁ አባ ተክለ ሃይማኖት ነበሩ:: መነኮሳቱን ተሰናብተው በዚያ ገመድ ሲወርዱ ተበጥሶ የማያውቀው ገመድ ድንገት ተበጠሰ:: ከላይ የሚያዩት አባቶች ቁልቁል እያዩ በድንጋጤ ጮኹ:: ሆኖም እግዚአብሔር ለጻድቁ የብርሃን ክንፍ ሠጥቶአቸው ከተበጠሰው ገመድ ተለይተው እንደ መልአክ በርረው ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ወርደው መሬት ላይ አረፉ:: ባረፉባት ሥፍራም ቤተ ክርስቲያን ተሠራባት::

ወዳጄ በሕይወትህ ድንገት የተበጠሰ ገመድ የለም? ሳትጠብቀው የተበጠሰ ገመድ ማንም ላይ ሳይበጠስ አንተ ላይ የጨከነ ገመድ የለም? ምን ዓይነት ገመድ አትበለኝ:: የእንጀራ ገመድ የኑሮ ገመድ የትምህርት ገመድ የፈለግኸው ገመድ በለው:: እሱን ተጠምጥመህ ይዘህ ወደ አንዳች ቦታ ለመድረስ የተማመንክበት ተስፋህን ሙሉ በሙሉ የጣልክበት ገመድ የለም? ድንገት ተበጥሶ ዙሪያው ገደል አልሆነብህም? ሰዎች ማንም ላይ ያልተበጠሰ ገመድ አንተ ላይ ሲበጠስ አይተው "ምኑ ዕድለ ቢስ ነው?" ብለው የተደነቁብህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "ከባሕር አደጋ ተርፎ ዕባብ የነደፈው እንዴት ኃጢአተኛ ቢሆን ነው?" ብለው በትዝብት ዓይን እንዲያዩህ ያደረገ በሕይወትህ ሳታስበው ተበጥሶ ዙሪያው ገደል የሆነ ሥፍራ ላይ የጣለህ የሕይወት ገመድ ይኖር ይሆናል::

በዕድልህ አትማረር በሕይወትህ ድንገት የሚበጠስብህ ገመድ የምትወድቅበት ሳይሆን ክንፍ አውጥተህ የምትበርበት ነው:: ፈጣሪ የተማመንክበትን የምታየውን ገመድ እንዲበጠስብህ ከፈቀደ ያላየኸውን ክንፍ ሊሠጥህ እንጂ ሊጥልህ አይደለም::  የሕይወትህን ገመድ የተበጠሰበትን ቀን "እግዚአብሔር ለመልካም አሰበው" ብለህ እንደ ዮሴፍ ታመሰግንበታለህ::
ገመድህን የሚበጥሰው ከገደል ሊጥልህ ሳይሆን በክንፍ አብቅሎ ሊተክልህ ነው:: የሚተክልህ በበረሃ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ነው:: ተራ ተክል የምትሆን እንዳይመስልህ:: የሃይማኖት ተክል (ተክለ ሃይማኖት) ትሆናለህ:: ተክለ መንፈስ ቅዱስ ተክለ ወልድ ተክለ አብ ትሆናለህ:: አብ የተከለው ደግሞ አይነቀልም!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 24 2013 ዓ ም
13.4K views , 18:46
ክፈት / አስተያየት ይስጡ