2022-11-01 22:05:26
ተሰውረው ያልተሰወሩ የሁለት ካርታ ሐቂቆች!
ይህን ካርታ ያገኘሁት ከየት ነው? ከመጽሐፍ፡፡ ከAlan McCrae Moorehead መፅሐፍ ነው፡፡ በ1956 ዓመተ ምህረት ላይ ካሳተመው መጽሐፉ፡፡ አለን ሙርሄድ ማነው? ትውልዱ ከአውስትራሊያ የሚመዘዝና የተማረ፣ በእንግሊዝ የኖረና የሞተ፣ ባካበተ ልምዱና ተመራምሮ ለህትመት ባበቃቸው አያሌ የጦርነት ታሪኮች፣ በተለይም እጅግ በታወቀባቸው ሁለት ተከታታይ መጽሐፎቹ የታወቀ ነው፡፡
የመጀመሪያው መፅሐፉ ‹‹The White Nile›› የተሰኘው ነው፡፡ አስከትሎ ያሳተመው ‹‹The Blue Nile›› የተሰኘው መጽሐፍ ስለራሳችን የአባይ ወንዝና በእርሱ ዙሪያ የተደረጉ አያሌ ጦርነቶችን ከተርኪሽ ኢምፓየር እስከ ፈረንሣዩ ናፖሊዮን የግብጽ ወረራን ተከትሎ ከእንግሊዝ ጋር የተደረገውን የጦፈ ውጊያ ይተርካል፡፡
ከዚያም አልፎ በሁለተኛው መጽሐፉ፣ የእንግሊዙን (የህንዱን እዝ) ጄነራል ናፒየርን ወደ ሀበሻ ምድር የተደረገ የጦርነት ጉዞ ከመነሻው እስከ ፍጻሜው በሚገርም ዝርዝር ማስረጃዎች እያስደገፈ ለዓለም ያስነበበ ብርቱ የታሪክ ተመራማሪና፣ ጉምቱ ፀሐፊ ነው፡፡ የጥንት ታሪኮቹን ልክ አሁን ያሉ አስመስሎ ነው የሚተርካቸው፡፡ ደግሞ የዕውቀት ሀብቱ፡፡ የመረጃው ብዛቱ፡፡ ጉድ ነው፡፡
እነርሱ መቼም ሰው ማክበር ያውቁበታል፡፡ ለዚህ ታላቅ አበርክቶቱ፣ አለን ሙርሄደ የብሪትሽ ኢምፓየርን እጅግ ከፍተኛውን ‹‹ኦርደር›› ከንግሥቲቱ እጅ (እንደ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንከርስት)፣ እንዲሁም የአውስትራሊያን ከፍተኛውን ‹‹ኦርደር›› ጨምሮ፣ በርካታ የዕውቅና ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡ በአለን ሙርሄድ የህይወት ታሪክ ፊልም ተሠርቶለታል፡፡ መጽሐፍ ተፅፎለታል፡፡
ሙርሄድ የናፒየርን የአቢሲንያ ዘመቻ ሲጽፍ ኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ፣ ግብጽን፣ ህንድን፣ ሱዳንን፣ የብሪትሽ ሙዝየሞችንና የዘማቾችን የግል ማስታወሻዎች አስሶ ነው፡፡ በመጨረሻ የዛሬ 40 ዓመት ገደማ በ73 ዓመት ዕድሜው እዚያው እንግሊዝ ውስጥ በሞት ተለየ፡፡ የዚህን ሰው በተለይ በሁለተኛ መጽሐፉ በአባይና በአፄ ቴዎድሮስ የመቅደላ ታሪክ ዙሪያ የጻፋቸውን ታሪኮች ወደፊት ወዳገርኛ የሚተረጉመው ቢገኝና ትውልድ ቢማርበት እያልኩ አስባለሁ፡፡
ታዲያ ይህን ሁሉ መግቢያ ስለ አለን ሙርሄድ ጻፍኩ፡፡ ለዛሬ ብዙም የምጨምረው የለኝም፡፡ ግን የታሪክ ፀሐፊው Alan Moorehead የመጽሐፉን ገጽ በሚያክል መጠን እንዲሆኑ፣ ሶስት ጊዜ በታጠፉ በብሪትሽ ካርቶግራፈሮች የተሠሩ ሁለት ታሪካዊ ካርታዎችን በመጽሐፉ ሸጉጦልን ነው ያለፈው፡፡
ይህ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ፎቶ አንስቼ ያቀረብኩት ሁለተኛው ካርታው ነው፡፡ የናፒየርን የዘመቻ መስመር - ከዙላ ወደብ እስከ መቅደላ አፋፍ ድረስ ያለውን በዚህ ታሪካዊ ካርታ ላይ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ግን አሁን ከዚህ ካርታ ላይ እጅግ የመሰጠኝ ነገር የናፒየር የዘመቻ መስመር አይደለም፡፡ በወቅቱ የአማራና የትግሬ መካለያ ተደርጎ በካርታው የሰፈረው የተከዜ ወንዝ የመሆኑ ነገር ነው ቀልቤን የሳበው፡፡
ይህን ካርታው የሚያመለክተውን ታሪካዊ ሀቅ፣ ቢያንስ ከዚህ ቀደም ጨምሮ ከሶስተኛ መጽሐፍ ላይ አግኝቼ ሳቀርበው ነው፡፡ በነዚህ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙዎችም ሌሎች ቀደምት ሥራዎች ውስጥ ተደጋግሞ የምናገኘው የታሪክ ሀቅ ነው ይህ፡፡ የአማራና የትግሬ ታሪካዊ የአስተዳደር ወሰን፣ ‹‹ከተከዜ መልስ›› እና ‹‹ከተከዜ ማዶ›› እየተባለ፣ የተከዜን ወንዝ ተከትሎ እንደተሠራ - ተብሎ ተብሎ የተሰለቸ ጉዳይ ነው፡፡
እነዚህን እውነቶች የማቀርበው ለምንድነው? በእውነት ላይ የተመሠረተ፣ ሀቀኛ ንግግርና ድርድር እንዲኖር ከመመኘት ነው፡፡ እውነትን በማደባበስ ሳይሆን፣ በእውነት ላይ ቆሞ መወያየት፣ ከዚያ ስለመልካም ጉርብትና፣ ስለ ቀጣዩ የጋራ ኑሮና የህዝቦች ትስስር ከልብ ተማምኖ፣ በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ ብዙ አማራጮች ያሉት መፍትሄ ማበጀት ይቻላል፡፡ የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡
ከሰው ጋር ትጣላለህ፡፡ ከፈለግክ ከእግዜርህም ጋር ትጣላለህ፡፡ ሰው ከራሱም ጋር ይጣላል፡፡ ከእውነት ጋር ግን አትጣላም፡፡ እውነት ነው መውጪያችን፡፡ እውነት ነው መዳኛችን፡፡ በአንድ ወቅት የዶክተር አረጋዊ በርሄን የዶክትሬት ጥናት በአስረጅነት እንደጠቀስኩት፣ ብዙ ይህን ካርታውን የሚያመለክተውን እውነት አምነው የሚቀበሉ፣ ከእውነት ጋር እርቅ የፈጸሙ ሰሜነኞች አሉ፡፡ እልህ በእውነት አስታራቂነት መብረድ አለበት፡፡
እውነቱ ይህ ከሆነ፣ ለህዝቦቻችን እንዲጠቅም ምን ብናደርግ ይሻላል? እኔ ይሄ ስጋት አለብኝ? ካንተ ይሄንን እፈልጋለሁ፣ እኛ ይሄን ጥቅም ማግኘት እንሻለን፣ ይሄኛው ለወደፊቱ ሁላችንንም ይጠቅማል፣ ያ በእንዲህ ያለ መልኩ ቢኬድበት፣ ... እያሉ በእውነት ላይ ቆሞ መደራደርም ሆነ፣ ስለመጪው የጋራ ሀገርና የህዝብ ትስስር መወያየት፣ ነገርን ዳግም ላያቆጠቁጥ ያደርቀዋል፡፡
አለበለዚያ በድርቅና የተነሳ፣ ስንት ተዓምር ሊሠራ የሚችል ትኩስ ወጣት ነው የሚያልቀው፡፡ ሌላ ትርፍ የለውም፡፡ በድርቀት የሚደርቅ ጠብ የለም፡፡ አበቃ ሲባል ዳግም እያቆጠቆጠ የሚነሳ የእርስበርስ መናጨትና የዜጋ እልቂት ብቻ ነው ትርፉ፡፡
መጽሐፉን ለጊዜው ትቼ፣ በካርታው መነሻነት ይህን ያህል ካልኩ፣ ከዚህ ታሪካዊ ካርታ ላይ ጥያቄ ያጫረብኝን ሌላውን ተጨማሪ ነገር አንስቼ ላብቃ፡፡ የናፒየር ካርታ ላይ ‹‹AMHARA›› ብሎ ከተከዜ መለስ ያሰፈረበት ሥፍራ አለ፡፡ ‹‹ጎንደር›› በሚለው ፋንታ ‹‹አማራ›› ብሎ እናገኘዋለን፡፡ እና በወቅቱ ‹‹አማራ›› ተብሎ የሚጠራው ጎንደር ብቻ ነበር ማለት ነው? ምክንያቱም በዚህ ካርታ ‹‹ጎንደር›› ተብሎ የተጠቀሰ ነገር የምናገኘው ጎንደር ከተማዋን ነው፡፡ እንጂ ጎንደርን አጠቃላዩን አይደለም፡፡
በመተማ በኩል ያለው የቴዎድሮስ ሀገር ጎንደር በዚህ ካርታ ‹‹ቋራ›› በሚል ተቀምጧል፡፡ በእርግጥ ያ አካባቢ የጎንደር አካል ይሁን እንጂ በስም ግን እስካሁንም ቋራ እየተባለ የሚጠራ ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ ይህ ካርታ ‹‹DAMOT›› ይለናል፡፡ ‹‹GOJAM›› ይላል፡፡ ‹‹SHOA››ን ያስቀምጣል፡፡ ከተከዜ ማዶ ያለውን ‹‹TIGRĔ››ን ያሳያል፡፡
ይህ የካርታው አገላለጽ ጥያቄን ያጫረብኝ፣ ከዚህ ቀደም አካፍዬው የነበረውንና፣ ‹‹WAX & GOLD...›› በሚል በ1950ዎቹ ባሳተመው መጽሐፉ የፊት የውስጥ ገጽ ላይ የአማራና የትግራይ ወሰን ከተከዜ ወዲህና ወዲያ እንደሆነ በካርታው አስፍሮ ሲያበቃ፣ የሑመራ-ወልቃይት-ፀገዴ-ፀለምትን ሥፍራ በካርታው ላይ በሰንጠረዥ ለይቶ በማመልከት፣ እነዚህ ስፍራዎች ትግርኛ ተናጋሪ ያለባቸው ቦታዎች ስለሆኑ፣ ከትግሬ ጋር ሊከለሉ ይገባል የሚል ብይን ሰጥቶ ያለፈው - የዶ/ር Donald Nathan Levine ነገር ሁልጊዜ ስለሚመጣብኝ ነው፡፡
እስካሁን ይህን የዶናልድ ሌቪንን መጽሐፍ በጥልቀት ያሄሰው ሰው ባያጋጥመኝም፣ ነገር ግን ሌቪን ‹‹አማራ›› የሚባል የሸዋውን፣ የጎንደሩን፣ የጎጃሙን ግዛትና ህዝብ ያጠቃለለ የጋራ የገዢ ነገሥታት ማንነት እንዳለ ለማሳየት የተሟሟተውን ነገር - አሁን ይህን የአለን ሙርሄድን የናፒየር ካርታ እያየሁ ደጋግሞ አቃጨለብኝ፡፡ ህወሃት ከመመሥረቷ በፊት ይህን ከተከዜ ወዲህ ያለውን ጭምር የትግራይ ሊሆን ይገባል የሚል ሀሳብ በመጽሐፉ አትሞ ያቀበላቸው ዶናልድ ሌቪን ነው፡፡
2.1K views19:05