2022-11-01 22:05:26
ዶናልድ ሌቪን በኢትዮጵያ የበላይ ገዢ የሆነ አንድ ብሔር አለ የሚለውን ለማሳየት የግድ ‹‹መንዙና ጎንደሩ፣ ጎጃሙና ይፋቱ፣ ወዘተ.›› የሚገናኝበት የጋራ ‹‹አማራ›› የሚባል ህዝብ መፍጠር ስላለበት፣ እንዴት የሸዋ ንጉሦች ከጎንደር ቡራኬ እያገኙ የሚገዙ ነገሥቶች መሆናችን፣ ዝምድናቸውንና መተጋገዛቸውን፣ የባህላቸውን ተመሳሳይነት ለማስረዳት እጅጉን ይጋጋጣል ዶናልድ ሌቪን!
ይህቺንም አማራ የሚባል በደምና በባህል የተሳሰረ ገዢ መደብ አለ የምትል ትርክቱን፣ ህወሃት ወስዶለት ‹‹የአማራው ገዢ መደብ›› ብሎ በማኒፌስቶው አስገብቷታል፡፡ ከነወልቃይቷ፣ ከነአማራ ገዢ መደብ፣ ህወሃት ከዶናልድ ሌቪን ቀብ አድርጎ በማኒፌስቶው በእስኪሪብቶ ከነተሳለ ካርታ ጭምር ኮፒ አድርጎት እናገኛለን፡፡ ለዚህም ነው ዶናልድ ሌቪንን ሞት ከመቅደሙ በፊት፣ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት ህወሃቶች የንጉሥ አቀባበል፣ የንጉሥ መስተንግዶና የንጉሥ ሽኝት ያደረጉለት፡፡
እና አሁን ይህን የአለን ሙርሄድ የናፒየር ዘመቻ ካርታ ስመለከት፣ ቀደም ብሎ ‹‹አማራ›› እየተባለ ይጠራ የነበረው ኋላ ‹‹በጌምድር››ም ‹‹ጎንደርም›› እየተባለ የሚጠራው የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ብቻ ነበር ማለት ነው ወይ? የሚል ብርቱ ጥያቄ አጫረብኝ፡፡ እንዲያ ቢሆን ነው እንጂ፣ ያ ዶናልድ ሌቪን ሸዋውም፣ ጎንደሩም፣ ጎጃሙም በጥቅል የአማራ ወገንነት የሚሰማቸው ‹‹አማሮች ናቸው›› የሚለውን ለማስረዳት እንዲያ የተጋጋጠው! እውን ለዚያ ይሆን?
ባይሆን ኖሮማ፣ ግልጽ ቢሆን ኖሮ፣ ለምን እንዲያ የጎንደርንና የመንዝን ግንኙነት ከሰማይ ከምድር እየቧጠጠ ለማስረዳት ተጣጣረ? ለምን አጠቃልሎ ‹‹አማራ›› ብሎ የጠራቸው ግዛቶችና ገዢ መሳፍንት ለዘመናት እርስ በርስ ሲፋለሙ የመኖራቸውን ነገር ለምን አልገለጸውም? በነገራችን ላይ ህወሃቶች ‹‹አማራ ክልል›› ብለው ሲያሰምሩም፣ ያንንም የኮረጁት (በብዙ መልኩ) ይኸው ጠንቀኛ አሜሪካዊ ዶክተር ዶናልድ ሌቪን በጻፈላቸው ‹‹የአማራነት›› ትርጉምና ማንነት መሠረት እንደሆነ አምናለሁ በግሌ፡፡
ከሰውየው ትንተናና፣ መሬት ላይ በህወሃት ዘመን ተተግብሮ ካየነው ነገር በመነሳት ነው ይህን የምለው፡፡ እና ዶናልድ ሌቪን ታላቅ ጀብዱ የሠራ የተከበረ ንጉሥ ተደርጎ ‹‹እንደ ባለውለታ›› በመለስ ዘመን ከተቸረው ልዩ ክብርና እንክብካቤ ሁሉ ተነስቼ ነው ይህን የምለው፡፡ እንጂ ከእርሱ ነው ተከዜንም መሻገር እንዳለብን፣ አማራ የሚባል ገዢ መደብ እንዳለ፣ አማራ የሚባለው ክልል ከየት እስከ የት መሆን እንዳለበት፣ ትግራይስ ከየት እስከየት መሆን እንዳለበት የኮረጅነው ከዶናልድ ሌቪን ነው የሚል ጽሑፍም ሆነ ማስረጃ አግኝቼ አይደለም፡፡
ከዶናልድ ሌቪን ሁሌ የሚገርመኝ ነገር፣ ዶናልድ መጽሐፉን ሲያሳትም በወቅቱ ኤርትራም የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡፡ በዶናልድ መጽሐፍ በሰፈረው ካርታም ላይ ትታያለች፡፡ ዶናልድ ግን ከተከዜ ወዲህ በአማራው ግዛት ያለውን የወልቃይት-ሑመራ-ወዘተ. በትግርኛ ተናጋሪነቱ ወደ ትግራይ ሊካለል ይገባዋል - ብሎ ነጥሎ በሰንጠረዥ አስምሮ መጻፉ - እጅግ ይደንቀኛል!
ዶናልድ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ በአንድ ክፍለሀገር ሥር መተዳደር አለባቸው ብሎ ካመነ - በካርታው ኤርትራንስ ለምን በሰንጠረዥ አላመለከታትም? ኤርትራውያንም ትግርኛ ተናጋሪ ናቸው (ብዙዎቹ)! የዶናልድ መርዝ በአማራው ላይ ተረጭቶ፣ በኤርትራ ላይ ግን ፎረሸ! ሁልጊዜ የሚገርመኝ - ይሄን ከዋለልኝም የቀደመ መርዘኛ ሰውዬ - ነሆለል የአማራ ካድሬዎች - ‹‹መንዜው ሌቪን›› የሚል ሁሉ ማዕረግ ጨምረውለታል! ኧረ ሌላም ሀገር-በቀል የማዕረግ ስም አውጥተውለታል!
ይህ ዓይነቱ መንፈዝ (መጃጃል) ሁልጊዜ ሲገርመኝ ይኖራል! ለማንኛውም በአለን ሙርሄድ ‹‹The Blue Nile›› መጽሐፍ ባገኘሁት የተከዜ ወሰንን የሚያሳይ ካርታ ተመስርቼ፣ ስለዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ካነሳሁ ሳልወድ የግድ ስሙን ማንሳት የነበረብኝን የዶናልድ ሌቪንን ስም ከነጦሰኛው ‹‹WAX & GOLD...›› (ሰምና ወርቅ - ብሎ ሰይሞ - ጦስ አመንጭቶብን ያለፈውን) መጽሐፉንም ጨምሬ አነሳሁ፡፡
በተረፈ ያነሳኋቸው ሁሉ በግላጭ በካርታና በመጽሐፍት ከቀረቡት እውነታዎች ውጭ፣ ድምዳሜዎቹ በራሴ እምነት በምክንያት የማምንባቸው መሆናቸውን መግለጼ እንዳይዘነጋብኝ፡፡ የተለየ ሀሳብ ያለው ካለ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም፡፡ ከፀቦቻችን ባሻገር የተሰወሩ፣ ለዘመን የታሹ፣ ረዥም የውጪ የክፋት እጆች አሉ፡፡
እነዚያን የክፋት እጆች በእውነት ላይ ተመስርተን ማብቃት፣ እና በህዝባችን መካከል ጦርነትን ሳይሆን ፍቅርን፣ መቃቃርንና መለያየትን ሳይሆን መቀራረብንና መተጋገዝን፣ ጥላቻን ሳይሆን ወገንነትን፣ ቂምበቀልን ሳይሆን እርቅን፣ ሽምግልናን፣ እርቀ-ሠላምን፣ ምህረትን ማስፈን የዚህ የእኛ ትውልድ ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ ለኛ ከራሳችን በላይ ማንም መፍትሄ ይዞ አይመጣልንም፡፡
እውነትንና ቅንነትን ተጠምተናል፡፡ ሠላምን ተርበናል፡፡ እርቅንና መረዳዳትን ታርዘናል፡፡ ፈጣሪ ይርዳን፡፡
እዚሁ ላይ ላብቃ፡፡
#Assaf Hailu
2.2K viewsedited 19:05