Get Mystery Box with random crypto!

የስብዕና ልህቀት

የቴሌግራም ቻናል አርማ human_intelligence — የስብዕና ልህቀት
የቴሌግራም ቻናል አርማ human_intelligence — የስብዕና ልህቀት
የሰርጥ አድራሻ: @human_intelligence
ምድቦች: መዝናኛዎች
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 88.58K
የሰርጥ መግለጫ

በዚህ ቻናል
⚡ህይወትን የሚያንፁ የስነ-ልቦና ምክሮች
⚡መሳጭ የፍቅር ታሪኮች እና ወጎች
⚡ጥልቅ ማህበራዊ እና ፍልስፍናዊ እይታዎች
⚡ውብ የጥበብ ስራዎች
በፅሁፍ እና በድምፅ/Audio ይቀርባሉ።
#ሼር በማድረግ ወዶጅዎን የዚህ የእውቀት እና የጥበብ ድግስ ታዳሚ እንዲሆኑ ይጋብዙ።

Ratings & Reviews

4.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

2

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 17

2022-09-02 15:42:20 ፀሎቴን ባሰማ ፥ እንደሰው ዝም አለኝ
እሱንም ዘመቻ ፥ ወሰዱት መሰለኝ
.......
የእቴሜቴ ጀምበር
ሲራክ ወንድሙ
.
እረኛ አይዘምርም ፥ ዝም ነው አድባሩ
ፋኖስ ክሩን አጥቷል ፥ መሸ ደህና እደሩ
ቡሬ መንደር ራቃት ፥ የለችም ከቤቷ
በሌት አልዘመረች ፥ ከፍቷታል ወፊቷ
ማልዶ ሌት ሚያነቃኝ ፥ ዶሮ በጉድ ወጣ
የሌት ድምፁን ሸጦ ፥ መውዜር ይዞ መጣ
ወዲያም ወደ ሰማይ
ከጎጆዬ በላይ
ፀሎቴን ባሰማ እንደሰው ዝም አለኝ
እሱንም ዘመቻ ወሰዱት መሰለኝ
.
የዛች የእዝነት አርማ ፥ የህዋ ላይ ሰንደቅ
እንዴት ቀን ከፍቶባት ፥ ውብ ጀምበሯ ትጥለቅ
ከዛች ከገራገር ፥ ከደጊቱ ዳሴ
እንደምን ብርቅ ይሁን ፥ ሰላም ለእለት ጉርሴ
ኧረ እንደምን በምን
ኧረ እንደምን በምን
አምነን ያነገስነው ብራ ቀን ይዳምን
እኔን አፈር ይብላኝ ፥ ለእኔ ቀኑ ይክፋ
አንቺን ያሳጣችሽ ፥ ያች አለም ትደፋ
እስከ መች አስከ መች ፥ የአረር ሙዳይ ቋጥረን
እንደጃኖ ኩታ ፥ ዝናር ጥለት አርገን
ሀገር እያጠፋን ፥ ያልፋል እንላለን ?
እንዴት ነው መሰንበት ?
መውዜር እንደነዶ በሚመዘዝበት?
ኧረ እንደምን በምን
ኧረ እንደምን በምን
አምነን ያነገስነው ብራ ቀን ይዳምን?
.
ከጩኸትሽ ማዶ ፥ ካኮረፈው ሰማይ
ቄራ ከመሰለው ፥ ከአድማስሽ ሸራ ላይ
እብሪት ያጠላበት ፥ ምስል ድንገት ካየው
ለቸር አንመስለኝም ፥ ያን ጊዜ ፈራለሁ
አርብ አርቡን አመሻሽ
የሰማዩ ገላ ሲመስል የደም ሻሽ
ንትብ የለበሰ
ከወደ አንገቱ ዘሞ የተዘለሰ
ይሁዳሽን ባላይ ፥ ወድቆ ሲያንሰራራ
መስቀል ሆኗል ለሻጭ ፥ ገዢ ራሱን ያኩራ
ከክርስቶስ ይልቅ ፥ ይሁዳ ነውና ሚረከብ መከራ
ምክኒያቱም ......
ዘመን እያሰፉ
ትውልድ ለሚነቅፉ
ነገር ጠንቷል ዛሬ ፥ አውቀውት ይረፉ
ለሻጭ መስቀል  ሊሆን ፥ ምሏልና ዛፉ
.
በኑረት ቀራንዮ ፥ በህይወት ጎለጎታ
ከገዳይሽ ቀዬ ፥ አንቺ ሆነሽ ጌታ
በሰማያ አኮርባጅ ፥ ወዲያ ስትላጊ
የመከራን መስቀል በሌት ተሸክመሽ ፥ መንገድ ስትፈልጊ
ጨረቃዋ ገባች ፥ ከደመና ጉያ
ከዋክቶች ሸሽተው ፥ እንደሰደድ ቋያ
ጠረንሽን ገፍተው ፥ ከገላሽ ሲርቁ
በንቄት ሸምቀው ፥ ሊጥሉሽ ዘለቁ
.
ዞር ብንል ወዲያ ፥ አራራይ መረዋ
ቀና ብንል ኦና ፥ የጠቆረ ህዋ
የፀሎትሽ ጩኸት ፥ ካልደረሰው ያ ' ቃል
እሱም እንደሰዉ ዘምቶልሽ ይሆናል።
..................... //// ..............
ሲራክ ወንድሙ 

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
4.2K viewsedited  12:42
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 22:15:55 አይገርምም!!

የተወለድነው በሌሎች ሰዎች እርዳታ ነው።

ስማችንን የተቀበልነው ሌሎች ሰዎች ባወጡልን መሰረት ነው።

የገቢ ምንጫችን የሚመጣው ከሌሎች ሰዎች ነው።

«ክብርና እውቅና የሚሰጡን ሌሎች ሰዎች ናቸው።

ገላችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያጠቡን ሌሎች ሰዎች ናቸው።ለመጨረሻ ጊዜ የሚያጥቡንም ሌሎች ሰዎች ናቸው።

ከዚህ አለም ስንሰናበት ቤታችንና ንብረታችን በሌሎች ሰዎች ይወሰዳል።

እጃችንን ይዘው በመደገፍ መራመድ ያስለመዱን ሌሎች ሰዎች ናቸው በመጨረሻም እጃችንን ይዘው በመደገፍ የሚያራምዱን ሌሎች ሰዎች ናቸው።

በመወለዳችን ምክንያት በደስታ የደገሱ የበሉት ሌሎች ሰዎች፤ ሰንሞትም በኃዘን የሚደግሱና የቀብር ስርአታችን የሚከናወነው በሌሎች ሰዎች ነው።

ይህ ሁሉ እውነታ እያለ "ነኝ "እና "አልኝ" በምንለው ነገር የምንመካበት ጉዳይ አይገባኝም። እስቲ ያወሰሰብናትን ሕይወትን
ቀለል እናድርጋትና ለመከባበርና ለመዋደድ ቅድሚያን በመስጠት እንኑር!!


@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
3.7K viewsedited  19:15
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 19:40:25 የቀጠለ
6.ግንኙነትን መፍጠር ወይም መነጠል (Intimacy vs. Isolation.)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ 18 አመት እስከ 40 አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ይህ የእድሜ ክልል ሰዎች ከቤተሰባቸው ውጪ ከሆኑ ሰዎች ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩበት ወቅት ነው፡፡የወደፊት የትዳር አጋራቸውንም በዚህ ወቅት ውስጥ ይለያሉ፡፡ይህ ሂደት ስኬታማ ከሆነ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖራቸዋል፣ለግንኙነቱ ቁርጠኝነት ያሳያሉ፣ደህንነት ይሰማቸዋል….ወዘተ፡፡ከሰው ጋር መገናኘትን የማይፈልጉና የሚፈሩ ከሆነ ግን የመነጠል ወይም የብቸኝነት ስሜት ይሰማቸዋል በዚህ የተነሳ ድብርት ውስጥ ሊገቡም ይችላሉ፡፡

7. ውጤታማነት ወይም ውጤታማ ያለመሆን ስሜት (Generativity vs. Stagnation)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ 40 አመት እስከ 60 አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡ይህ ወቅት ሰዎች ስራ ይዘው ፣ትዳር ይዘው ልጅ ወልደው…ወዘተ የሚኖሩበት ወቅት ነው፡፡በዚህም የተነሳ ሰዎች ላሉበት ማህበረሰብ ማበርከት ስላለባቸው ነገር ያስባሉ ጥሩ አገር ተረካቢ ልጅ እንዲኖራቸው ከመፈለጋቸውም በላይ ባሉበት የስራ መስክ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ ነገር መስራትን ይፈልጋሉ፡፡በህብረተሰብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውስጥም ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች ማሳካት ያልቻሉ ሰዎች ውድቀትና ውጤታማ ያለመሆን ስሜት ይሰማቸዋል፡፡

8.መተባበር ወይም ተስፋ መቁረጥ( Ego Integrity vs. Despair)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ60 አመት በላይ ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ ይህ እድሜ የጡረታ እድሜ ሲሆን ሰዎች ወደኋላ ተመልሰው የመጡበትን ሁኔታ የሚቃኙበት ጊዜ ያገኛሉ፡፡ ወደኋላ ተመልሰው የመጡበትን የሂወት መንገድ ሲቃኙ የስኬታማነት ስሜት ከተሰማቸው ከቀጣዩ ትውልድ ጋር በመተባበር ያላቸውን ነገር ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይፈልጋሉ ስኬታማ ያልሆኑ ከመሰላቸው ግን የተስፋ መቁረጥና የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሁም ድብርት ሊሰማቸው ይችላል ከዚህም አለፍ ሲል ሞትን እስከ መፍራት ሊደርሱ ይችላሉ፡፡

ማጠቃለያ፡-የተስተካከለ ማህበራዊ እና ሀይለ-ስሜታዊ እድገት እንዲኖረን መሰራት ያለበት ከልጅነታችን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከልጅነት ጀመሮ ከተሰራ ቀላል ይሆናል ነገር ግን አድገንም ቢሆን እራሳችንን የማስተካከል እድል አለን፡፡
በኤሪክሰን አባባል የዛሬ ጸሁፌን ላጠናቅ “ It is not toolate ”

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
4.2K viewsedited  16:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-29 19:40:25 የልጆች ማህበራዊ እና ሀይለ-ስሜታዊ እድገት(social and emotional development)


   ማህበራዊ እድገት ለሰው ልጅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የእድገቶች አይነት ውስጥ አንዱ  ነው፡፡ማህበራዊ እድገት የሚጀምረው ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ልጆች ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ የምናደርግላቸው ነገሮች የልጆች ማህበራዊ እድገት ላይ የራሳቸው የሆነ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽእኖ አላቸው፡፡በዚህ መስክ ብዙ የተመራመረው ተመራማሪ ኤሪክ ኤሪክሰን ሰዎች ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ እስከ እርጅና ድረስ ያለውን  የሰዎች የማህበራዊ እድገትን በስምንት ደረጃዎች ይከፍላቸዋል፡፡እነዚህ ስምንት ክፍሎች በእድሜ ክልል የተከፋፈሉ ሲሆን በአንደኛው ደረጃ ላይ ያለው የማህበራዊ እድገት ለቀጣዩ መሰረት ነው፡፡ ስምንቱን ደረጃዎች ከዚህ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡

1.ማመን ወይም አለማመን( Trust Versus Mistrust)

   ይህ የእድገት ደረጃ ልጆች ከተወለዱ ጀምሮ እስከ አንድ አመት ተኩል ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡በዚህ እድሜ ላይ ያሉ ልጆች ፍላጎታቸውን የሚገልጹት በማልቀስ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በሚደረግላቸው እንክብካቤ መጠን እና ቀጣይነት ሌሎችን ማመን ይጀምራሉ፡፡በዚህ ወቅት ላይ በአግባቡ የሚፈልጉት ነገር ከተሟላላቸው አለምን ማመን ይጀምራሉ የደህንነት ስሜትም ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን የሚፈልጉትን ነገር በአግባቡ እና ወጥ በሆነ መልኩ የማናሟላላቸው ከሆነ መጠራጠር እና መፍራት ይጀምራሉ፡፡በዚህም የተነሳ መጨነቅ፣ፍርሀት እና ከፍተኛ የሆነ እምነት ማጣት ሊታይባቸው ይችላል፡፡

2. በራስ መተማመን ወይም ማፈር እና እራስን መጠራጠር( Autonomy vs. Shame and Doubt)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ አንድ አመት ተኩል እስከ ሶስት አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡በዚህ ጊዜ ውስጥ ልጆች መንቀሳቀስ የሚጀምሩ ሲሆን እቃ ማንሳት በአሻንጉሊት መጫወት ይፈልጋሉ፡፡ ምግብም እራሳቸው መመገብ ፣ልብሳቸውን እራሳቸው መልበስ….ወዘተ ይፈልጋሉ፡፡ እራሳችን እንስራ በሚሉበት ጊዜ እንዲሰሩ  የምናበረታታቸው ከሆነ በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ያዳብራሉ፡፡እራሳቸውን ችለው በዚህ አለም ላይ የመኖር ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የምንተቻቸው ከሆነ  እንዳይሰሩ የምንቆጣጠራቸው ከሆነ ወይም ሁሉንም ነገር እኛ የምንሰራላቸው ከሆነ ነገሮችን ለመሞከር ሲያፍሩ ወይም እራሳቸውን ሲጠራጠሩ ይታያሉ፡፡

3. መነሳሳት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት( Initiative vs. Guilt)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ ሶስት አመት እስከ ስድስት አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ልጆች በዚህ እድሜ መጫወት ይጀምራሉ፣ለሚሰሩት ስራ እቅድ ያወጣሉ፣ለጫወታ ይነሳሳሉ ሌሎችንም ያነሳሳሉ …ወዘተ ልጆች ይሄ እድል ከተፈጠረላቸው የተነሳሽነት ስሜት እና በራሳቸው ችሎታ የመተማመን ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ነገር ግን እገዳ የምንጥልባቸው ከሆነ ወይም የምንቀጣቸው ከሆነ የጥፋተኛነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ነገሮችን በራሳቸው ለመስራት ከመነሳሳት  ይልቅ ሌሎችን መከተል ይመርጣሉ፡፡

4. በሰሩት ስራ መኩራት ወይም የበታችነት ስሜት መሰማት( Industry vs. Inferiority)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ ስድስት አመት እስከ አስራአንድ አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች መደበኛ ትምህርት ይጀምራሉ፡፡ልጆች በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ በሰሩት ስራ የመኩራት ባህሪን ያሳድጋሉ፡፡ስራን ጀምረው ሲጨርሱ የኩራት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡አስተማሪዎች ልጆችን በማነሳሳት እና ያሰቡትን ግብ እንዲያሳኩ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጾ አላቸው፡፡ በዚህም ልጆች ስራን እንዲሰሩ ከተበረታቱ እና በሰሩት ስራ ሽልማት ከተበረከተላቸው በራሳቸው ስራ የመኩራትን ባህሪ ያሳድጋሉ ከዚህም በተጨማሪ ያሰቡትን ግብ እንደሚያሳኩ በራሳቸው ላይ እምነት ይኖራቸዋል፡፡ነገር ግን በወላጅ ወይም በአስተማሪ ገደብ የሚጣልባቸው ከሆነ ወይም የሚቀጡ ከሆነ እራሳቸውን ይጠራጠራሉ፣የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል እንዲሁም የአቅማቸው ጫፍ ላይ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡

5.ማንነትን መለየት ወይም ግራ መጋባት( Identity vs. Role Confusion)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ 11 አመት እስከ አስራስምንት አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ይህ ወቅት የጉርምስና ወቅት ነው፡፡ጉርምስና ልጆች ከህጻንነት ወደትልቅነት የሚተላለፉበት ድልድይ ነው ልጆች በዚህ ወቅት ላይ እራስን ችሎ መንቀሳቀስ፣ ወደፊት ምን መሆን እንደሚፈለጉ መወሰን ፣ጓደኞቻቸውን መምረጥ …ወዘተ ይፈልጋሉ፡፡ልጆች በዚህ ጊዜ ላይ በዙሪያቸው ያሉ አማራጮችን ከማየታቸውም በተጨማሪ እራሳቸውን መፈለግ ይጀምራሉ በዚህም የተነሳ እኔ ማነኝ የሚለውን ጥያቄ ይመልሳሉ አካባቢያቸው ይህን ካልፈቀደላቸው ግን ግራ መጋባት ይፈጠርባቸዋል ወደፊት ምን መሆን እንደሚፈልጉም አያውቁም፡፡

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
4.2K viewsedited  16:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-27 08:45:25 የተጣለ ፈረስ
(በእውቀቱ ስዩም)

ዘመኑ ያለፈ
ጋማው የረገፈ ፤
የጎድን አጥንቱ ፤ ማበጠርያ መሳይ
ጠዋት  ህያው ፍጡር፥  ሌሊት የጅብ ሲሳይ
ከተማው መግቢያ ላይ
አቧራ የሚቅም
የተጣለ ፈረስ አጋጥሞሽ ፤ አያውቅም?

“ካሁን አሁን መጥቶ፤
ይወስደኛል ነድቶ 
ከጋጣው  አግብቶ ፤ ያበላኛል እብቅ “
እያለ ጌታውን ፥ተግቶ  የሚጠብቅ
የዛሬ ተጎታች ፤ የትናንቱ ሰጋር
ተባብሮ የከዳው፤ ጊዜ ከጌታው ጋር
የቸገረው አቅም፥
የተጣለ ፈረስ ፤ አጋጥሞህ አያውቅም?

ደሞስ መች ይጠፋል? ካንቺም ከኔም መንደር
የቀድሞ ወታደር፥
በጨነቀን ጊዜ ፥“በናት ሀገር ጥሪ “
የምናጣድፈው፥
በድል ቀን ከድግስ፥ የማናሳትፈው
ከነጣቂ መዳፍ ፥ አገር  የሚያስመልስ
በገዛ አገሩ ላይ፥
መብቱ ከወፍ አንሶ፤ ጎጆ የማይቀልስ፤
  
ደሞ መች ይጠፋል፤ ከኔም ካንተም ቀየ
መንገድ ላይ ምናልፈው፥  አይተን እንዳለየ
የቀድሞ አስተማሪ
ላብ እያጣቀሰ ፊደል አስቆጣሪ
ቀሪ ሀብት ባይኖረው፤
የቀረውን ዘመን፤ እያሰላ ኗሪ፤

ቪላችንን ሞልተን፥ በሱ ጎጆ ጉድለት
ማሰብ አስተምሮን ፥ የማናስበለት
ቀኖቹን በትኖ፤ ሌሊቶቹን ዘርቶ
ናላውን፥ ጉልበቱን ፥ ውበቱን  ሰውቶ 
የሚጎተት አገር፥ ከግቡ ለማድረስ
ሺህ መንገድ አቅንቶ፥ ሺህ ገደሎች  መውረስ
ሰው ቢሉት ሰው ነው ወይ?
የተጣለ ፈረስ ::


@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
7.5K viewsedited  05:45
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-22 22:01:36 “ለምን?” ብለህ ጠይቅ

ለመሻሻልና ለመለወጥ ከፈለክ፣ “ለምን?” ብለህ ከመጠየቅ አትረፍ!

•  “አሁን የምኖረውን ኑሮ በዚህ መልኩ የምኖረው ለምንድን ነው?”

•  “ገቢዬ ለምን በዚህ ብቻ ተወሰነ?”

•  “አምኜ የተቀበልኩትን የሕይወቴን ሂደት ለምን ተቀበልኩት?”

•  “የማደርገውን ነገር በዚህ መልኩ የማደርገው ለምንድን ነው?”

•  “በሕይወቴ መሻሻል የሚችል ነገር አለ ወይ? ካለስ ለምን
አላሻሽለውም? እንዴትስ ላሻሽለው እችላለሁ?”

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይህ ነው የማይባል የአእምሮ መነቃቃት ያመጣል፡፡ የተለመደውን የኑሮውን ሂደት “ለምን?” በማለት የማይጠይቅ ሰው በአንድ ቦታ ለመርጋትና ሃውልት ለመሆን ራሱን ያዘጋጀ ሰው ነው፡፡

አንድ ሰው ለመሻሻልና ለመለወጥ አእምሮውን ሊያነቃቃና የተለመደውን የየእለት የኑሮውን ዑደት “ለምን?” ብሎ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ይህ ከተነቃቃ አእምሮ የሚነሳ ራስን የማሻሻልና የመለወጥ ጉዞ ባሉበት ሳይረኩ ከዛሬ ሁኔታ የተሻለ ነገር ውስጥ ለመግባት አስፈላጊውን ነገር ወደማድረግ ይወስደናል፡፡

እንዲሁ የመጣውን ሁሉ በመቀበልና በማስተናገድ በእድል ለመሻሻል ከመሞከር፣ አእምሮዬ እንዲሻሻል ማንበብ፤ የገቢዬ ምንጭ እንዲሻሻል ሙያዬንና ብቃቴን ማዳበር፣ ማሕበራዊ ኑሮዬ እንዲሻሻል ደግሞ ባህሪዬን ማጤንና ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡

አንድን እውነታ መዘንጋት የለብኝም፣ የእኔነቴና የብቃቴ መሻሻል ዙሪያዬንና ሁኔታዎቼን ሁሉ ለመልካም የመለወጥ ብርታትና ተጽእኖ አለው፡፡ ስለዚህም፣ ማንነቴ፣ ብቃቴና ችሎታዎቼ መድረስ የሚችሉበት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ መጠየቅና መንቀሳቀስን አለማቆም ተገቢ ነው፡፡

አንዳንድ ዝም ብለህ ልትቀበላቸው የሚገቡህ ነገሮች የመኖራቸው እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁሉንም ነገር ግን ዝም ብለህ በጭፍንነት አትቀበል - “ለምን?” ብለህ ጠይቅ!!!

ዶ/ር እዮብ ማሞ

@Zephilosophy
@Zephilosophy
12.7K views19:01
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-21 22:19:30 እውነተኛ ፍቅር- ፕሌቶ

ግሩም ከሆነ የፍልስፍና እሳቤዎች አንዱን ፕሌቶ ከክርስቶስ ልደት 385 ዓመታት በፊት በጻፈው The symposium መጽሐፍ ውስጥ እናገኘዋለን። ይህ መጽሐፍ በታላቁ የቲያትር ደራሲ አጋቶን ቤት ስለተዘጋጀ የራት ግብዣ ያትታል። ብዙ ጠቢባን ጣፋጭ ምግብን ሊመገቡ፣ ወይን ሊጠጡ እና ቁምነገር ሊያወጉ ታደሙ፡፡ በወንበሮቻቸውም ላይ እንዳሉ የተጠበሱ ምግቦችን እና ጣፋጭ አትክልቶችን መመገብ ጀመሩ፤ ግማሾቹ የወይኑ ስካር በአናታቸው ላይ ይወጣ ጀምሯል። እናም የድግሱ አዘጋጅ የነበረው አጋቶን ሁሉም እየተነሱ ስለ ኤሮስ ወይም ስለ ፍቅር የሚስማቸውን እንዲናገሩ ጋበዛቸው፡፡ እናም ፕሌቶ ንግግር ማድረግ ጀመረ፤ ፍቅርን በሁለት ከፈለው -

የመጀመሪያው ምድራዊ ፍቅር ሲሆን፣ ሁለተኛው ፍጹም ንጹህ የሆነ መለኮታዊ ፍቅር ነው፡፡
ምድራዊ ፍቅር የፍቅር መነሾ ነው፡፡ ልክ መስላል ላይ የመጀመሪያውን ደረጃ እንደምንወጣው ሁሉ፣ ይህም ወደ ፍጹማዊ ፍቅር የሚያደርስ ጅማሮ ነው:: በውስጡም ወሲባዊ ፍላጎት እና ምኞትን ይይዛል። ይህ ፍቅር የሚገናኘው ከሰውነት አቋም እና ከፊት ማማር ጋር ስለሆነ፤ ቆዳ ሲሸበሸብ፣ ጸጉር ሲሸብት የሚጠፋ ፍቅር ነው።

ንጹህ ፍቅር - በአንጻሩ ከነፍስያ ጋር ይቆራኛል። በዚህ ፍቅር ውስጥ ስንሆን ከፊት ገጽታም በላይ ጠልቀን የምንገባበት እና ስለ ሰውነት መቀየር ግድ የማይሰጠን እንሆናለን፡፡ ይህ ሁለት ነፍሶች በፍቅር የሚወድቁበት ቦታ ነው።
ዛሬ ላይ እንደዚህ አይነቱን ፍቅር ለመግለጽ platonic love የሚል ቃልን እንጠቀማለን፡፡

ፕሌቶ የፍትወት ፍላጎትንም ይቅር አስፈላጊ አይደለም አላለም። ይልቁኑ አንድን ሴት በመልኳ ተማርከን ልንቀርባት እንችላለን፤ ሆኖም ይህን ምድራዊ ፍቅር ንጹህ ወደሆነው መለኮታዊ ፍቅር ማሻገር ይጠበቅብናል፡፡ ፍቅራችን ከሰውነቷ ጋር ብቻ መሆን የለበትም። ከዚህም በላይ ነፍሶቻችን ሊቆራኙ ይገባል። በእርጅና ዘመናችን አብሮን የሚሆን እና ከውበታችን መክሰም ጋር የማይጠፋ ፍቅር ውስጥ መሆን አለብን።

እውነተኛ ፍቅር እውር አይደለም፤ ሆኖም በማስተዋል እና በጥበብ ይመራል፡፡ ከመልክ፣ ከቁንጅናም በላይ ይሄዳል።የተጣመሩ ነፍሳት ፍቅራቸው ከምድራዊው ዓለም አይደለም::

@Zephilosophy
@Zephilosophy
11.2K views19:19
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-16 22:31:55 “የውሻዬና የመኪናው ነገር”
የምትፈልገው (Your wants) እና የሚያስፈልግህ (Your needs)

አንድ ሰው ለወዳጁ እንዲህ ብሎ አጫወተው፡፡ “የውሻዬና የመኪናው ነገር በጣም ነው ያደከመኝ፡፡ በሰፈራችን ያለፈው መኪና ሁሉ አንድም አይቀረውም፣ በብርቱ እየተከታተለ ይጮሃል፡፡ ያየውን መኪና ሁሉ ለተወሰነ ርቀት ካሳደደው በኋላ ተመልሶ ይመጣል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገና ሌላ መኪና ሲመጣ ጠብቆ ያንኑ ነገር ይደግማል፡፡ ስለእርሱ እኔ ደከመኝ”፡፡

ወዳጁ ይህንን ከሰማ በኋላ አንድ ጥያቄ ጠየቀው፣ “ለመሆኑ፣ ውሻህ መኪናን አባርሮ የሚደርስበት ይመስልሃል?” ሰውዬውም መልሱ እንዲህ የሚል ነበር፣ “እኔን የጨነቀኝ የመድረስ ብቃቱ አይደለም፣ ከዚህ በፊት በቀስታ የሚሄዱ መኪናዎች ላይ ሲደርስ አይቻለሁ፡፡ ልክ ሲደርስባቸው ፊቱን አዙሮ ይመለስና ሌላ የሚያልፍን መኪና እንደገና ለማሳደድ ይጠብቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀኑን ሙሉ ይህንን ሲያደርግ ነው የሚውለው፡፡ ውሻዬ የሰው ቋንቋ ቢችል፣ ጊዜህን በአግባብ ተጠቀምበት ብዬ እመክረው ነበር”፡፡

“የስኬት የመጀመሪያው መመሪያ ፍላጎት ይባላል - የምትፈልገውን ማወቅ፡፡ ፍላጎት አለህ ማለት ዘርህን ዘራህ ማለት ነው” - Robert Collier

አሁን በጽኑ የምትፈልገውን ነገር ቆም ብለህ አስበው፣ ብትደርስበትና በእጅህ ቢገባ ምን ታደርጋለህ? ለዚህ ጥያቄ ብዙም ሳታስብና ሳትጨናነቅ ቁልጭ ያለ መልስን መስጠት ካልቻልክ ምናልባት የምትከታተለው ነገር ለምንም ጥቅም የማይውል ጊዜ ማባከኛ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የሚፈልጉት ነገር ምን እንደሆነ አያውቁትም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ገንዘባቸውን ያፈስሳሉ፣ ጊዜአቸውን ይሰዋሉ፣ ብዙ ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ፣ ከዚያም ያንን ነገር ልክ እጃቸው እንዳስገቡት ሲያውቁ ቀድሞውንም የሚፈልጉት ነገር እንዳልሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ከዚያም እንደገና ሌላ ነገር መከተል ይጀምራሉ፤ አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡

አሁን በብርቱ የምትከታተለውን፣ ብዙ ጊዜህን የምታጠፋበትን፣ ገንዘብህን ያባከንክበትን ነገር በእጅህ ብታስገባው፣ በህይወትህ ካለህ ዋነኛ ዓላማ ጋር አብሮ ካልሄደና ወደትምሄድበት የሕይወት አቅጣጫ አንድ እርምጃ ካላራመደህ ጊዜህን በከንቱ እያባከንክ ነው፡፡ የማያዛልቅን ነገር ማባረር! የምትከተለው ነገር በምትሄድበት የሕይወት ዓላማ አቅጣጫ መሆኑን ማወቅ የአዋቂነት ሁሉ አዋቂነት ነው፡፡ መመለስ ያለበት ጥያቄ፣ “የምትፈልገው ነገር ምንድን ነው?” የሚለው ነው፡፡

ፍላጎትህን በማወቅ ስትደላደል ሌላው ሰው ላይ አይተኸው ያማረህ ነገር ሁሉ የግድ እንደማያስፈለግህ ማስተዋል ትጀምራለህ፡፡ በሕይወትህ በምትፈልገው (Your wants) እና በሚያስፈልግህ ነገሮች (Your needs) መካከል ለይተህ ማወቅ በብዙ ይጠቅምሃል፡፡ የምትፈልገው ነገር ሁሉ የሚያስፈልግህ ላይሆን ይችላል፤ በተቃራኒው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልግህን ሁሉ ለጊዜው ላትፈልገውና ልታስተላልፈው ትችላለህ፡፡ የእነዚህን ሁለት ነገሮች ልዩነት ጥርት ባለ መልኩ መለየት አለብህ፡፡ የምትመኛቸውንና የምትፈልጋቸውን ሁሉ ከመከተል ይልቅ በሚያስፈልጉህ ነገሮች ላይ ማተኮር ስትጀምር፣ ሁኔታው ለሌሎች ግር ቢልም ለአንተ ግን እውነታው ኩልል ብሎ ይታይሃል፡፡

በሚያስፈልገንና በእርግጥም ብንደርስበትና በእጃችን ብናስገባው ለመልካም አላማ ልንጠቀምበት በምንችል ነገር ላይ ትኩረትን መጣል ራስን የመግዛት ዲሲፕሊን ይጠይቃል፡፡ ራስን የመግዛት ዲሲፕሊን የንግስና ሁሉ ንግስና ነው፡፡

“እኔ በእርግጥ ንጉስ ነኝ፣ ምክንያቱም ራሴን መግዛት አውቅበታለሁና” - Pietro Aretino

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
16.3K views19:31
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-15 20:35:26 የሆኑ ባልና ሚስት ወደ አንድ እንስሳት ማቆያ ፓርክ በአጋጣሚ ይሄዳሉ እንዳጋጣሚ አንድ ዝንጀሮ አብራው ካለች ጓደኛው ጋር እየተጫወተ የነበረ ዝንጀሮ አገኙ ።

የሰውየው ሚስት እንዲህ አለች “ምን አይነት ፍቅር ነው ! እንዲህም አይነት አለ እንዴ ? አለች በመገረም! "

ከዚያም ወዲያው ዞዞር ማለት እንደጀመሩ ሌላ አንድ ወንድና ሴት አንበሳ ጎን ለጎን ተለያይተው ተቀምጠው አዩና........ ሚስትየዋ “ፍቅር የሌለበት ምን አሳዛኝ ትዕይንት ነው አለች በማዘን "

ይህን የሰማው ባልተቤቷ እንዲህ አላት
“ያን ድንጋይ ወደ አንበሳይው ወርውሪና ተመልከቺ አላት ” እሷም ድንጋዩን አንበሳው ላይ ስትወረውር አንበሳው አንበሳይቱን ለመከላከል ሲጮኽ አየች

ባልየውም ከዝንጀሮዋ ጋርም ድገሚው አላት እሷም ለአንበሳው እንዳደረገችው ድንጋዩን ወደ ዝንጀሮው ስትጥል ወንዱ ዝንጀሮ ዘሎ ዛፍ ላይ ወጣና ራሱን ለማዳን ሴቷን ጥሎ ሄደ ።

ባሏም እንዲህ አላት “በምታይው ነገር አትታለይ ያየሺው ሁሉ ፍቅር አይምሰልሽ ፡፡ ብዙ ጊዜ ባዶ ልብን ለመደበቅ ሲባል የሚያታልል ገጽታ ወይም አስመሳይነት ይኖራል ፡፡

ሌሎች ደግሞ አሉ ዝምተኞች ፣ ልባቸው ግን ቅን የሆነ በአሁኑ ጊዜ ፣ እንደዝንጀሮው የሆኑ ብዙዎች አሉ ፣ ጥቂቶች ደግሞ እንደ አንበሳው የሆኑ አሉ።

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
13.7K views17:35
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-08-15 20:13:08 እምቢ የማለት ጥበብ

በዓለማችን ላይ ብዙ ሰዎችን ከሚያጠቁ አጉል ጠባዮች አንዱ ‘አይሆንም’ ማለት ያለመቻል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በፍጹም ማድረግ የማይፈልጉትን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከቤተሰብ፣ ከዘመድ ወይንም ከጓደኛ በሚኖር ጫና ብቻ ‘አይሆንም’ ወይም ‘አልፈልግም’ ማለት ሳይችሉ ቀርተው እና የማይፈልጉትን ትምህርት መርጠው ሙሉ ሕይወታቸውን በማይሆን አቅጣጫ የቀየሱ ሰዎችን በግሌ አውቃለሁ፡፡ ይህ ‘እምቢ’ ማለት አለመቻል እጅግ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ የሥነ-ልቡና ምሁራን ‘ከሌሎች ውጫዊ ተጽእኖ መላቀቅ መቻል አንድ ሰው በሕይወቱ ከሚያስመዘግባቸው ድሎች እጅግ የላቀው ነው’ እስከማለት ደርሰዋል፡፡

አንድ ሰው ከእንቅልፉ ሲነሳ ብዙ ነገሮች ጊዜውን እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ስልኩ ይጮሃል፣ በኢሜይል መልእክት ይመጣለታል፣ የቅርብ ጓደኛው ቀጠሮ ለማስያዝ ይሞክራል፣ አለቃው ተጨማሪ ሥራ ሊያዘው ያስጠራዋል… ወዘተ፡፡ በዚህ መልኩ የዚያን ሰው ጊዜ ለሚፈልጉ ነገሮች በአጠቃላይ ‘እሺ’ የሚል ከሆነ መሥራት ያለበትን ሥራ በተገቢው ፍጥነት እና ጥራት መሥራት አይችልም፡፡ ሁሉንም እሺ በማለቱ እጅግ ይጨናነቃል፡፡ አንድ ሰው የራሱን ሥራ ጨርሶ ሌላ ፕሮግራም እያለው፤ ሥራውን ሳይሠራ የቀረ ባልደረባው ‘ይህቺን ሥራልኝ’ ቢለው እና ‘ይቅርታ፣ ዛሬ ሌላ ፕሮግራም አለኝ…’ ማለትን ሳይችል ቀርቶ ‘እሺ’ ቢለው፤ ፕሮግራሙን ማበላሸቱ አይደለም? በዚህ ምክንያት የሚበላሹ ነገሮችን ለማዳን እና ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ካስፈለገ በተገቢው መንገድ ‘አይሆንም’ የማለት ጥበብን መልመድ የግድ ይላል፡፡

ሰዎች ‘አይሆንም’ ማለት የማይችሉባቸውን ምክንያቶች የሚዘረዝሩ የሥነ-ልቡና ምሁራን ሁለት ዋና ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ሌላኛውን ሰው ለማስቀየም አለመፈለግ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ ሰው እጅግ የምንወደው፣ የምናከብረው ወይም ደግሞ የቅርብ ሰው ከሆነ ‘እንዳላስቀይመው’ ወይንም ‘እንዳላስቀይማት’ በሚል ሰበብ ሁሉንም ነገር እሺ ማለት ያለብን ይመስለናል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከዚያ ሰው ጋር ዘላቂ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ፤ ‘አይሆንም’ ማለታችን ግንኙነታችንን ክፉኛ እንዳይጎዳው ከማሰብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክፉ ሆኖ መታየትን በመፍራት፣ ከቡድን መገለልን በመፍራት፣ ግጭትን በመፍራት እና እድል ያመልጠኛል በሚል ፍራቻ ሰዎች ‘አይሆንም’ ማለት ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ በአስተዳደጋቸው ወቅት ‘አንተ! እሺ በል እንጂ!’ ወይም ‘አንቺ! እሺ አትይም?’ እየተባሉ ያደጉ ልጆች፤ እንዲህ አይነት ‘እሺ ባይነት’ ጠባይ ሊያጠቃቸው እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ያብራራሉ፡፡

በመሆኑም፤ በተገቢው መልኩ ‘አይሆንም’ የማለት ጥበብን ማዳበር ጊዜያችንን በፈለግነው መልኩ እንድንጠቀም ከማስቻሉም በተጨማሪ ከአላስፈላጊ ተጽእኖ እና ከሚፈጠር ጭንቀት ሊያድነን ይችላል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ ዶ/ር ኢዮብ ማሞ ‘የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ’ በሚለው ላይ ‘ትሁት አምቢታ’ እንዴት ሊጠቅመን እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ ፊት ለፊት ‘እምቢ’ ማለት የእውነትም ሰዎችን የሚያስቀይም ሊሆን ቢችልም፤ የትሁት እምቢታ ጥበብን ከለመድን ግን በቀላሉ ማስተናገድ እንችላለን፡፡ ምስሉን አብሬ አያይዣለሁ፤ በፓውሎ ኮኤልሆ ጥቅስ ጽሑፉን ልጠቅልል፡፡

‘ለሌሎች ‘እሺ’ ስትል ራስህን ግን ‘እምቢ’ እያልክ አለመሆኑን አረጋግጥ’ ፓውሎ ኮኤልሆ

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
12.5K views17:13
ክፈት / አስተያየት ይስጡ