2022-10-26 09:04:55
ስቃይን መጋፈጥ
ምንጭ ፦ ደስታን የማግኘት ጥበብ
ትርጉም ፦ ዳኜ መላኩ
በቡድሀ ጊዜ ካይሳኦታሚ የተባለች አንዲት ምስኪን እናት አንድ ልጇን በሞት ተነጠቀችና ከባድ ሀዘን ወደቀባት፡፡ ይህቺ ምስኪን እናት የመጽናኛ ልጇ ሞት የምትቋቋመው አይነት አልነበረምና እጣ ፈንታዋን በጸጋ መቀበል ተሳናት፡፡ እናም ልጇን ከሄደበት አለም የሚመልስ መድሀኒት ፍለጋ አዋቂ፣ ጠቢብ ካለበት ስፍራ ሁሉ መዞር ጀመረች፡፡ ከአንዱ ጠቢብ ወደ ሌላው እየዞረች የሞትን መድሀኒት ስታጠያይቅ ሰዎች ወደ ቡድሀ ይመሯትና ቡድሀ ዘንድ ትቀርባለች፡፡
እንደ ባህሉ እጅ ነስታ ስታበቃም ቡድሀን ‹‹ልጄን ከሞት የሚመልስ መድሀኒት ልታገኝልኝ ትችላለህ?›› ስትል ትጠይቃለች።
ቡድሀም ምንም ሳያቅማማ ‹‹አዎን..... አንድ የማውቀው መድሀኒት አለ›› ይልና አክሎም ‹‹ሆኖም መድሀኒቱን ለመስራት የሚያስፈልገው ቅመማ ቅመም መገኘት አለበት›› ይላታል፡፡
እናቲቱ ልጇን ከሞት የሚመልስ መድሀኒት በመኖሩ እፎይ ትልና በተስፋ ‹‹ምንድን ነው የሚያስፈልገው? ምን ላምጣ?›› ስትል ትጠይቃለች።
‹‹አንድ ጭብጥ የሰናፍጭ ፍሬ ማምጣት ይኖርብሻል›› ይላታል ቡድሀ፡፡
እናትየው የሰናፍጭ ፍሬውን ካለበት ፈላልጋ እንደምታመጣ ቃል ገብታ ትነሳለች። ሆኖም ቡድሀን ተሰናብታ ልትወጣ ስትል አንድ ማስጠንቀቂያ አክሎ ይነግራታል። ‹‹ሰናፍጩን ማምጣት ያለብሽ ሞት ገብቶ ከማያውቅበት ቤት ነው፡፡ ልጁን፣ ሚስቱን፣ ወላጆቹን ወይም አገልጋዮቹን በሞት ካልተነጠቀ ሰው ቤት ነው ሰናፍጩ መምጣት ያለበት» ሲል ያስጠነቅቃታል፡፡
እናትየው በዚሁ ትስማማና የሰናፍጭ ፍሬውን ማፈላለግ ትጀምራለች። ከቤት ቤት እየዞረች ታጠያይቃለች፡፡ በየገባችበት ቤት የጠየቀቻቸውን ሰናፍጭ ለመስጠት ቢስማሙም በቤታቸው ውስጥ ሰው ሞቶባቸው እንደሆን ስትጠይቅ ሁሉም በሞት የተነጠቁትን ይነግሯታል፡፡ አንዳንዶቹ ልጃቸውን፣ አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን በሞት አጥተዋል፡፡ አንዳንድ ቤት ውስጥ ባል ወይም ሚስት ስትሞት ቤቶች ውስጥ ደግሞ ሰራተኛና የሴት አገልጋዮች በህይወት የሉም፡፡ እናቲቱ በየቤቱ እየገባች ብትጠይቅም ሞት ቀድሟት ያልገባበት ቤት ልታገኝ አልቻለችም፡፡
ካይሳኦቶሚ ሞት ያልደረሰበት ቤት እንደሌለ ስትረዳ፣ በርግጥ ሞት በርሷ ላይ ብቻ የወደቀ ሀዘን እንዳልሆነ ተገነዘበች፡ ሁሉም ሰው የሚወደውን አጥቷል። ሞት በሁሉም ላይ የሚደርስ የህይወት እጣ ፈንታ ነው፡፡ ይህን በማየት ካይሳኦቶሚ የልጇን ህይወት አልባ አካል ይሁን ብላ ተቀብላ ወደ ቡድሀ ተመለሰች፡፡ ቡድሀም በታላቅ ርህራሄ እንዲህ ሲል አጽናናት
‹‹ልጅሽን በሞት ያጣሽው አንቺ ብቻ አይደለሽም፡፡ የሞት ህግጋት በምድራዊ ፍጡራን ላይ ሁሉ የተጣለ ነውና ከቶውኑ ቋሚ የሆነ የለም።"
«የእናቲቱ ጉዞ በርግጥ ከምድራዊው ሀዘንና ስቃይ ነጻ የሆነ ሰብአዊ ፍጡር እንደሌለ የሚያመላክት ንግርት ነው፡፡ ይህን እውነታ መገንዘብ ውስጣዊ መረጋጋትን የሚያሰርጽ ታላቅ ሀይል አለው። ስቃይ የሁሉም ሰው እጣ ፈንታ መሆኑን ማወቅ ብቻውን ሀዘንና ህመማችንን ባያስወግደውም ይህንን ተፈጥራዊ እውነታ መቀበል ችግርና ህመምን በመታገል የምናተርፈውን ተጨማሪ ስቃይ ይቀንሳል።
"ህመምና ስቃይ በሁሉም ላይ የሚደርስ የህይወት ገጽታ ቢሆንም ምንም ጉዳት እንዳልደረሰብን ሁሉ በቀላሉ ልንቀበለው እንችላለን ማለት አይደለም። አሳዛኝ የህይወት ዱብዳዎችን ማስተናገድ በእጅጉ ከባድ ነው። ይህ በመሆኑም ሰዎች ስቃያቸውን ለማምለጥ የሚረዱ የተለያዩ ዘዴዎችን ፈብርከዋል። አንዳንድ ጊዜ ስሜትና አስተሳሰባችንን የሚያደነዝዙ መድህኒቶችን በመጠቀም ከስቃያችን እፎይ ለማለት እንሞክራለን። አንዳንዴም የህይወት እውነታዎቻችንን የሚያስረሱ አልኮልና አደንዛዥ እጾችን በመጠቀም ከችግራችንም ከራሳችንም ለማምለጥ እንማስናለን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከስሜታዊ ስብራቶቻችን ለመሸሽ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ውስጣዊ የሆነውን ስነ ልቦናዊ ትግል እናካሂዳለን፡፡ አንዳንዴም ችግራችንን በመካድ ስቃዩን ላለመጋፈጥ ስሜታችንን በውስጣችን እናዳፍናለን፡፡ ወይንም ችግሩ መኖሩንን እናምንና ህመሙን ላለማሰብ አእምሯችንን ጎጂና ትርጉም አልባ በሆኑ ጉዳዮች እንጠምዳለን፡፡ ብዙዎቻችን ደግሞ ችግራችንን ላለመቀበል ጥፋታችንን በሌሎች ላይ አላከን ሰዎችን እንወቅሳለን፡፡››
‹‹ስቃይ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው፡፡ ለጊዜው ልናስታግሰው ብንችልም ለዘላለሙ ልናስወግደው አንችልም፡፡ ፈውስ እንዳላገኘ ቁስል ውስጥ ለውስጥ እየመረቀዘ በየጊዜው እዥ ያነባል፡፡ በየጊዜው የሚሰጠው መድሀኒት ውጪውን ቢያደርቀውም ውስጡ መግል እንደቋጠረ ይቀራል።
«ምናልባት ስቃይን በአልኮልና በአደንዛዥ እጽ ለጊዜው መሸሽ ይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም በዚህ የማያቋርጥ የሽሽት ሂደት የሚፈጠረው ግላዊና ማህበራዊ ጉዳት ወደ አልኮል ከመራን ስቃይ የባሰ ህመምና ችግር ይፈጥራል፡፡ ስቃያችንን ላለመቀበልና ለማዳፈን በውስጣችን የምናካሂደው ስነ ልቦናዊ ትግል ህመማችንን በጥቂቱ ሊያስረሳን ቢችልም ችግሩ ሳይፈታ ተቀምጦ ይቀራል፡፡
ስቃይ ከሰው ልጅ ህልውና ሊወገድ የማይችል ተፈጥሯዊ ገጽታ መሆኑን በመግለጽ ቢጀምሩም፣ አቀራረባቸው ከዚህ ስቃይ ነጻ መውጣት የምንችልበት መንገድ እንዳለ የሚጠቁም ነበር፡፡ ሆኖም በዳላይ ላማው እምነት ሁሉም ነገር እውነታውን ተቀብሎ ከመጋፈጥ ይጀምራል፡፡
‹‹በእለት ተእለት ህይወታችን ውስጥ ችግሮች መከሰታቸው የማይቀር ነው፡፡ በማንኛውም ሰው ህይወት ውስጥ ከሚከሰቱ ሊወገዱ የማይችሉ ችግሮች ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሱት እርጅና፣ ህመምና ሞት ናቸው ስለነዚህ ችግሮች አለማሰብ ችግሮቹን በማስረሳት ጊዜያዊ እፎይታ ሊሰጠን ቢችልም ችግሮቹን ከመሸሽና ከመራቅ ይልቅ ፊት ለፊት መጋፈጡ የችግሮቹን ጥልቀትና የሚያስከትሉብንን ጉዳት በትክክል ለመገንዘብ ያስችላል፡፡
‹‹በጦርነት ውስጥ ስለ ጠላትህ ትጥቅና የውጊያ ስልት ትኩረት ላለመስጠት ብትሞክር ተገቢውን ዝግጁነት ከማጣትም ባሻገር በፍርሀት ትታሰራለህ፡፡ ሆኖም የጠላትህን አቋም፣ ትጥቅና የውጊያ ብቃት ጠለቅ ብለህ ብትመረምር በተሻለ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ውጊያውን ትጀምራለህ፡፡ ስለ ጦርነት በቂ እውቀት የሌለው፣ ሽጎጥና ቦምብ አይቶ የማያውቅ ወታደር እራሱን በበቂ ሁኔታ ሳያዘጋጅ ለጦርነት ቢሰለፍ ምናልባት ገና ሳይመታ በድንጋጤ እራሱን ሊስት ይችላል፡፡ ሆኖም የሚገጥመውን ሁኔታ አስቀድሞ ሲያስብበት ከሁኔታው ጋር አብሮ ለመሄድ ይቀለዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ችግሮችህን ከመርሳት ይልቅ ፊት ለፊት ለመመልከት ብትሞክር ችግርህን በተሻለ መልኩ የመፍታትና የማስተናገድ እድል ይኖርሀል፡፡››
@Zephilosophy
@Zephilosophy
10.8K views06:04