2022-09-12 08:02:27
በምክንያት አትታሰር
ለውድቀታችን ብዙ ምክንያቶችን መስጠት ለምደናል። ወደ ኃላ ለቀረንበት፤ የፈለግነውን ሳይሆን ያልፍለግነውን ለመሆናችን፤ምክንያቱን ብንጠይቅ፤ እጅግ ብዙ ነገሮችን ለመደርደር
እንችላለን። ግን ሁሌም ምክንያቶች በኖሩን ቁጥር፤ ውድቀታችንን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን ማለት ነው ፤ እንደዛ ማለት ብቻም ሳይሆን ለወደፊቱ ውድቀታችንም ዝግጁ ያደርገናል::
ህልም ካለህ እና ህልምህ ለህይወትህ ትልቅ ትርጉም ካለው፤
ከባዶ ማንነት ወጥትህ፤ ትርጉም ያለው ማንነት እዲኖርህ
ከፈለግክ ምክንያት መስጠትህን አቁም። ሁላችንም ለውደቀታችን ማስተባበያ የሚሆን ብዙ ምክንያቶችን ማቅረብ
እንችላለን…..በገዛ ህይወታችን ሃላፊነት ስለሚጎድለን፤
እራሳችንን እንዳንለውጥ ምክንያቶቻችን አስረው ይይዙናል::
ስኬታማ ሰዎች ግን ለውድቀታቸው ምክንያትን መስጥት የማይወዱ ሰዎች ናቸው። ስኬታማ ስል ገንዘብን ወይም የሃብት ክምችትን ብቻ እንደ ስኬት መለኪያ ቆጥሬው አይደለም። ስኬት
በራሳችን መመዘኛ የሚለካ ነው።አንድ የሚያስማማን ነገር ግን
ስኬታማ ሰዎች፤ የመረጡትን ኑሮ መኖር የቻሉ ናቸው። ልባቸው የወደደውን፤ ለህይወታቸው ትርጉም የሚሰጠውን መንገድ የተከተሉ፤ ብርሃናቸው ከራሳቸው አልፎ ለሰው የሚያበሩ ሰዎች
ናቸው::
በዘልማድ ኑሮ ውስጥ ተዘፍቀን፤ ማህበረሰቡ ባወጣልን
መስፈርት፤ አካባቢያችን ባሰመረልን መስመር፤ ችሎታችንን
ገድበን እስከመቼ እንኖራለን? ህልሞቻችንን ሌሎች ማየት
ስለተሳናቸው ብቻ ቅዠት እየመሰለን፤ እውን የሚሆኑ ብዙ ህልሞችን እስከመቼ እናጨልማለን? አላማችንን እንደራሳችን አድርጎ የሚመለከትልን ሰው ስላጣን፤ አላማችንን በተስፋ መቁረጥ ጉድጓድ ውስጥ ቆፍረን ቀበርነው። ችሎታችንን ሰው እንዲነግረን ስንጠብቅ፤ አቅም እና ችሎንታችንን፤ እንደቅጠል ጠወለጉብን:: እራሳችንን የሚመስል ከሰው መሃል ፈልገን ስላጣን፤ ሰውን ለመምስል ሙግት ጀመርን። ሌሎችን መስለን ተራ ሆንን፤ ስራችን የሌላውን መስሎ ተራ ሆነ። መመሳሰል ህይወታችንን የሚያቀልን መሰለንና፤ እኛነታችንን እረስተን ተመሳሰልን፤ ያኔ ልዩነታችን ሞተ፤ ከልዩነታችን ጋር እኛነታችን አብሮ ሞተ፤ከኛነታችን ጋር ህልማች ሞተ። የገዛ ውበታችን ጠፋ ምክንያቱም
ውበት በልዩነት ውስጥ የሚንጸባረቅ ነበርና::
ስንቶቻችን የምንወደውን ስራ አየሰራን ነው? ትርጉም የሚሰጠን ኑሮ፤ ለመኖር ምክንያት የሚሆን እሴት ያለን ስንቶቻችን ነን? አብዛኛዎቻችን ችግራችንን ለምደነዋል፤ ውድቀታችንን ተቅብለነዋል፤ ስለምንኖረው ኑሮ ምንም አይነት ነገር የማድረግ አቅም የሌለን ይመስለናል፤ ህይወታችንን የሚለውጥ ሰው ወይም አጋጣሚ እስኪመጣ እንጠብቃለን፤ በዛ መሃል ውስጣችን ቀስ በቀስ ይሞታል።
ብዙዎች የሚያውቁት ጥቂቶች ግን የሚኖሩበት እውነታ ግን ይህ
ነው።ለህይወትህ ሃላፊነት ከወሰድክ እና መሆን የምትፈልገውን ከወሰንክ በዚህ ምድር ላይ ካንተ በቀር ከጉዞህ የሚያስቀርህ ማንም የለም። እርግጥ ነው መንገድህ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይሆንልህም፤ ብዙ ችግር ያጋጥመሃል ምክንያቱም የስኬት
መንገድ ቀላል ቢሆን ኖሮ ሁሉም ይሳካለት ነበር። ግን ከባድ
ነው…….መንገድህ ሊያቀልልህ የሚችለው አንድ ሚስጥር አለ
እሱም ህይውትህን ለመቀየር ምን ያህል ትፈልጋለህ?
ናፖሊዮን ሂል አንድ ሰው ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችለውን
ሚስጢር እንዲህ ይናግረዋል “ሰዎች አሸናፊ እንዲሆኑ
ሊኖራቸው የሚገባ ባህሪ አለ እሱም ፤ የሚፈልጉትን ነገር
በእርግጠኝነት ማወቅ፤ መወሰን እና ውሳኒያቸውን በተግባር
ለማዋል የሚያስችላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ማዳበር።” እኒዚህ
ሶስት ነገሮች አንድ ላይ ሲዋሃዱ ህይወታችንን ወደፈለግንበት
አቅጣጫ እንድንመራ የሚያስችለንን መሪ ጨበጥን ማለት ነው።
ብዙዎቻችን በህይወታችንየምንፈልገውን ነገር አናውቅም፤ብናውቅ እንኳን መወሰኑ ይከብደናል። ለምን?ለመለወጥ ስለምንፈራ? ዛሬ ያለንበትን ቦታ ስለለመድነውና መጪውን
ስለማናውቅ?ሌሎች አይሳካም አይሆንም ስላሉን? አቅማችንን
ማንም ነግሮን ስለማያውቅ? ወይስ ውድቀትን ፈርተን?ሁላችንም ምክንያቶች አሉን፤ እኒህ ምክንያቶች ደግሞ ባለንበት
ቦታ እንድንቀር የሚቸነክሩን ሚስማሮች ናቸው። ለውድቀትህምክንያት እስከሰጠህ ድረስ…ካሰብክበት አትደርስም ምክንያቱም ፤ የመለወጥ ፍርሃትህ ሌላ ምክንያት መፍጥር አያቆምምና።ከዚህ አለም ስትሄድ በምን መታወስ ትፈልጋለህ? ዳግም
በማታገኛት አንዴ በተሰጠችህ በዚህች አጭር ህይወት ምን ማድረግን ትመርጣለህ? መለወጥ የምትፈልገው ምንድን ነው?የምትፈልገውን እና የሚያስደስትህን ስራ መስራት?መልካምቤተሰብ መመስረት? መማር? ከሱስ መላቀቅ? የጀመርከውን
ስራ መጨረስ? ለምትወዳቸው ሰዎች መኖር? ወይስ ምን?
የራስህን ህልም መኖር ካቃተህ የሌላውን ሰው ህልም እውን
ለማድረግ ስትለፋ እንደምትኖር እመን፤ አይ የራሴን ህልም
ማሳካቱን እመርጣለው ካልክ ደግሞ፤ ሶስቱን ነገሮች አስታውስ፤
የምትፈልገውን ነገር እወቅ
ወስን
ለመለወጥ ፍላጎት ይኑርህ። ከምንም በላይ ምክንያት መስጠትህን አቁም።ሁሉም ስዎች ትልቅ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሊሆኑባቸው የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች አሏቸው። ልዩነቱ ደካሞች በምክንያት ታስረው፤ከአቅማቸው በታች ሲኖሩ፤ ጠንካሮች ግን ችግሮቻቸው እና እንቅፋቶቻቸውን የውድቀት ምክንያት ከማድረግ ይልቅ፤
እራሳቸውን ይበልጥ ያጠነክሩበታል………ከመንገዳቸው የሚያቆማቸው ምንም ነገር የለም፤ ማንም ከአላማቸው
አይገዝፍባቸውምና::ያንተስ አላማ ምን ያህል ግዙፍ ነው?
Credit to Biniyam Girmachew
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence
12.3K viewsedited 05:02