2023-04-09 15:32:01
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የተሠጠ መግለጫ!
<< የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ለማፍረስ የብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሕገ መንግሥቱን፣ የክልሉን መንግሥትና የአማራን ሕዝብ ሉዓላዊነት የጣሰ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም! >> // የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት//
የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ የአገር ህልውና አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ ሁሉ ከፊት በመሰለፍ የጠላትን አከርካሪ በመስበር በደሙ የአገር ሉዓላዊነትን ለማጽናቱ የብልጽግና መራሹ መንግሥት ህያው ምስክር ነው። ሆኖም ይኼን ውለታ በካደ መልኩ ከሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ትጥቅ ለማስፈታት ወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ሆን ተብሎ ወደጎን በመተው የአማራን ሕዝብ ቀጣይነት ላለው ጥቃት የሚዳርግ ብሎም እገዛበታለሁ የሚለውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚጥስ ውሳኔ ነው። በመሆኑም ውሳኔው በሚከተሉት መሠረታዊ ምክንያቶች ተቀባይነት የለውም።
1. የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ለማፍረስ ገዥው ፓርቲ አንዳችም ሕጋዊ ሥልጣን የሌለው በመሆኑ፦
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 52/2/ሰ መሰረት፣ የፖሊስ ኃይል የማደራጀትና የራሳቸውን ሠላም ፀጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት የክልል መንግሥታት ሥልጣን ነው። የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስም በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት ክልሉና የአማራ ህዝብ ያሉበትን ስጋቶች በማጤን በክልሉ መንግሥት የተደራጀ የፖሊስ ኃይል ነው።
የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን እንደገና ማደራጀትም ይሁን ማፍረስ አስፈላጊ መሆኑ ከታመነበት መላው የአማራ ሕዝብና የክልሉ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎበት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ብቻ የሚተገበር እንጂ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ለማፍረስና ትጥቅ ለማስፈታት ገዥው ፓርቲ አንዳችም ሕጋዊ ሥልጣን የለውም።
2. ውሳኔው ወቅቱን ያልጠበቀ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ወደ ጎን ገሸሽ ያደረገ እና የሕዝብን ደኅንነትን አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ በመሆኑ፦
2.1. ባለፉት 4 ዓመታት በአማራ ክልል በምስራቅ አማራ የምድረ ገኝ፣ በሰሜን ሸዋ ደራ፣ ምንጃር፣ ሸዋሮቢት፣ አጣዬ እና መሠል አጎራባች ወረዳዎች በኦነግ ሸኔ የሚፈፀሙ በከባድ መሣሪያ የታገዙ ጥቃቶች ሊቆሙ ባለመቻላቸው ከተሞች ወድመዋል፤ በርካታ ሕዝባችን ለሞት ብሎም ለስደት ተዳርጓል። ይኼ ጥቃትና ውድመት ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
2.2. በዓባይ ሸለቆ ዙሪያ ሠርጎ ለመግባት የሚሞክረው የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን አደጋ ያልተቀረፈ ችግር ነው።
2.3. በምዕራብ አማራ በሱዳን ሠራዊትና መነሻቸውን ሱዳን አድርገው በሚንቀሳቀሱ ውስጣዊና ውጫዊ ታጣቂ ቡድኖች የአገርን ሉዓላዊነት በመጣስ የአገሪቱን ግዛት ወርረው ይዘው የሚገኙ ሲሆን፣ በሕዝባችን ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን ለማድረስ የሚደረጉ ሙከራዎችን ለማስቆም ብልጽግና መራሹ መንግሥት ፍላጎት እንደሌለው ታይቷል።
2.4. በክልሉ የሚንቀሳቀሱ እና በተደጋጋሚ የሽብር ተልዕኮ በመውሰድ በሕዝባችን ላይ የማያባራ እልቂት በማድረስ የሚታወቁ የታጠቁ አሸባሪ ቡድኖች ወደ ተሟላ የሰላም አማራጭ የገቡ ባለመሆኑና በማንኛውም ጊዜ ጥቃት ሊያደርሱ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ክፍት ናቸው።
አማራን በጠላትነት ፈርጀው የሚታገሉ ኃይሎች፣ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ቀጣይነት ባለው መልኩ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማሳሳት፣ የማንነት ገፈፋና ጅምላ ማፈናቀል ታይቶ በማይታወቅ ሀኔታ እየፈጸሙበት ይገኛሉ። እነዚህ ኃይሎች በትጥቅ የደረጁና የአገር ህልውና ሥጋት መሆናቸው በመንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን መንግሥት በእነዚህን ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለሕዝባችን ዘላቂ የደኅንነት ዋስትና ዛሬም ድረስ መስጠት አልቻለም። በዚህም ከሞት የተረፉት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ውሎ አዳራቸው በመጠለያ ካምፖችና በጎዳና ላይ መሆኑም የአደባባይ ሐቅ ነው።
በተጨማሪም በፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት መሠረት ትሕነግ ሙሉ ትጥቁን ያልፈታ መሀኑ የሚታወቅ ሲሆን ሂደቱም ግልጽነት የጎደለው መሆኑ እሙን ነው። የፌዴራሉ መንግሥት ከሚናገረው በተቃራኒ፣ የትሕነግ (የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር) አመራሮችና ሚዲያዎች በአማራ ሕዝብ ላይ የተጠናከረ የጥላቻ ቅስቀሳ እያካሄዱ እና አጎራባች የአማራ አካባቢዎችን በኃይል ለመንጠቅ እየተዘጋጁ መሆናቸውን በአደባባይ እየተናገሩ ይገኛሉ።
የአማራ ሕዝብ ከውስጥና ከውጭ እነዚህና የመሳሰሉትን ግልጽና ቀጥተኛ የደኅንነት ስጋቶች ተደቅነውበት እያለ፣ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ የኢፌዴሪ መንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ ለአማራ ሕዝብ ደኅንነት ደንታ ቢስ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
ከላይ ከጠቀስናቸው መሠረታዊ ምክንያቶች በተጨማሪ ክልሉ የራሱን ሰላም የመጠበቅ ውስጣዊ ሉዓላዊ መብቶች ያሉት ከመሆኑ ባለፈ፣ ሕዝባችንን ከድኅረ-ጦርነት የሰላምና መረጋጋት ስጋቶች የመጠበቅ እና ሰላምና መረጋጋትን የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣ በክልሉ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ክልሉ የፀጥታ አቅሙን የማጠናከር እንጂ የማሳሳት ሁኔታን የሚፈቅዱ አይደሉም። በሌላም በኩል የክልሎችን የራስን ውስጣዊ ሰላም የማስጠበቅ ሉዓላዊ መብቶች የሚጋፋ እና ከዚህ ቀደም ክልሉን ለጥቃት ያጋለጡ አገራዊ እና ክልላዊ ክፍተቶችን ከግንዛቤ ያላስገባ፣ ከቀደመው የፀጥታ አቅም ጉድለት የተከሰተውን የሕዝብ ጥቃት የሚያቃልል እርምጃ በመሆኑ እኛ የአብን አማራ ምክር ቤት አባላት ውሳኔውን አጥብቀን እንቃወማለን።
ስለሆነም እኛ የአብን የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት፦
ሀ. የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ የሕዝብ ደኅንነትና ሠላም ለማስከበር የተቋቋመ የሕዝብ ተቋም እንጂ የአንድ ፓርቲ የግል ንብረት አለመሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል። ስለሆነም የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ በሌለው ሥልጣን በሕገ-ወጥ መንገድ በማናለብኝነት የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ትጥቅ ለማስፈታትና ለማፍረስ የሚያደርገው የጥድፊያ ሙከራ ከፍተኛ አገራዊ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን በመገንዘብ ውሳኔውን እንዲቀለብስ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
ለ. የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስን ትጥቅ ማስፈታት የአማራን ሕዝብ የህልውና አደጋ ላይ መጣል መሆኑን በመገንዘብ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲህ ያለውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ ወቅቱን እና ነባራዊ ሁኔታውን ያልጠበቀ ትጥቅ አስፈቺ ውሳኔ እንዳይተገበር እንዲያደርግ እናሳስባለን።
ሐ. የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት የወከለው ሕዝብ ህልውና ከመቼውም ጊዜ በላይ አደጋ ውስጥ መሆኑን በመገንዘብ አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባ በመጥራት በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት እንዲደረግበት እንጠይቃለን።
በመጨረሻም፦
1. ለመላው የአማራ ሕዝብ፦
የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ ሕዝባችን እና አገራችን ከፍተኛ ማጥ ውስጥ በገቡበት ወቅት ነፍሱን ሳይሰስት ጠላትን ተከላክሎ እንደ አባቶቹ አገር ያቀና ልጅህ መሆኑን አውቀህ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ ሆነህ ከጎኑ እንድትቆም ጥሪ እናስተላልፋለን። የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የወሰነው ውሣኔ ሕግን የጣሰ፣ የክለሉን መንግሥትና የአማራን ሕዝብ ሉዓላዊነት የደፈረ በመሆኑ ውሳኔው እንዲቀለበስ በጽናት እንድትታገል እንጠይቃለን።
4.3K views12:32