2021-11-04 22:25:15
እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እና ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
<3 ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ <3
ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች። በቤት ውስጥም ስምዖን፣ ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እኅትም ነበረችው።
እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ - ማውታ (ድሃ አደግ) ሆኖ ነበር። ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ። የበረከት፣ የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው።
እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች። የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር። በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር። እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም። ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው። (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል።)
እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወራት ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ። ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም። አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና።
ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው። ስለዚህም፦
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ።
(መልክዐ ስዕል)
ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል።
ለዚህም ምክንያቱ
፩.ለሠላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፣
፪.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣
፫.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው፣
፬.ጌታችን ከትኅትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው። (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና።)
ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ።" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል።
(ያዕ. ፩፥፩)
ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው።
¤ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ።
¤ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ።
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም።" ብሎ ማክፈልን አስተማረ።
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ።
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ።
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ።
¤ሙታንን አስንስቶ፣ ድውያንን ፈውሶ፣ የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ፣ አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተአምራትን ሠራ። እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ።
በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት። እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው፤ የእኔም ወንድሜ ነው።" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር። (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት)
በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ። "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦
አምላክ፣
ወልደ አምላክ፣
ወልደ አብ፣
ወልደ ማርያም፣
ሥግው ቃል፣ እግዚአብሔር ነው። እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም።" አላቸው።
ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት። በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት። አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው። ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ። ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሐምሌ ፲፰ ቀን ሔደ።
ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር። በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ፣ ጸጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም።
"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል።
ከጾም፣ ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር። ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን። በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን።
<3 ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ <3
ቅዱሱ ሐዋርያ ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእትና ከሰባቱ ዲያቆናት ነው። በሐዲስ ኪዳን ስማቸው ከተጠቀሰ ሐዋርያትም አንዱ እርሱ ነው።
(ሐዋ. ፮፥፮)
በትውፊት ትምህርት እንደ ተማርነው ቅዱስ ጢሞና ጌታችንን የተከተለው በመዋዕለ ስብከቱ ነው።
በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል (፲፥፩) ላይ እንደ ተጠቀሰው "ወፈነዎሙ በበክልኤቱ" እንዲል ሁለት ሁለት አድርጐ ሲልካቸው ቅዱስ ጢሞና አንዱ ነበር። በሔዱበትም በስሙ አጋንንት ተገዝተውላቸው፣ ድውያንም ተፈውሰውላቸው ደስ ብሏቸዋል። ጌታችን ግን "አጋንንት ስለ ተገዙላችሁ ደስ አይበላችሁ። ይልቁንስ ስማችሁ በመንግስተ ሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።" ብሏቸዋል።
(ሉቃ. ፲፥፲፯)
ቅዱስ ጢሞና ጌታችንን እስከ ሕማሙ አገልግሎ፣ የጌታን ትንሣኤ ተመልክቶ፣ በዕርገቱ ተባርኮ፣ በበዓለ ሃምሳም ቅዱስ መንፈሱን ተቀብሎ ከፍጹምነት ደርሷል። በመጀመሪያው ዘመንም ሐዋርያት አበው ለአገልግሎት ሰባቱን ዲያቆናት ሲመርጡ እርሱን መንፈስ ቅዱስ አብሮ መርጦታል።
(ሐዋ. ፮፥፭)
በቅዱስ እስጢፋኖስ ሥር ሆኖም እንደሚገባ አገልግሏል። ከቅዱስ እስጢፋኖስ መገደል በኋላም እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በዓለም ወንጌልን ሲሰብክ ኑሮ በዚህች ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል።
ከበረከቱ ያድለን።
ጥቅምት ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዮሴፍ)
፪.ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ ወዲያቆን
፫.ቅዱስ አግናጥዮስ
፬.ቅዱስ ፊልጶስ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ
፫.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
"የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት። ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።"
(ያዕ ፩፥፩-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በቴሌግራም @wdasemaryam ይከታተሉን።
1.2K views✥ድንግል ሆይ ሁሉን ከሚያስብ ሁሉን ከማይዘነጋ ከልጅሽ አሳስቢ✥, 19:25