2021-12-10 18:10:44
ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤልያስ
ታህሳስ 1 ቀን የዚህ ታላቅ ነቢይ የተወለደበት ነው፡፡ ትውልዱ
እሥራኤላዊ ሲሆን አባቱ ኢያስኑዩ እናቱ ደግሞ ቶና ይባላሉ፡፡
የተወለደውም ከክርስቶስ ልደት 900 ዓመት በፊት ነበር፡፡
በተወለደበት ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል፡፡ ብርሃን
የለበሱ 4 መላእክት በእሳት መጐናጸፊያ ሲጠቀልሉት ወላጆቹ
በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው፡፡ ካህናቱ
ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእሥራኤል
ይነግሥ ይሆን? ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል፡፡
ቅዱስ ኤልያስ የተወለደበት ወቅቱ ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት
እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት በኢሎፍላውያን እጅ
የነበሩት ጣዖታት ዳጐንና በአል በዚያ ዘመን ወደ እሥራኤል
ገብተው ነበር፡፡ ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል
ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን ጠንቅቆ ያወቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው
ነበር፡፡ በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው፡፡
የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ፡፡ ቅዱሱ አብዛኛውን ጊዜ
መኖሪያው በተራሮችና በዱር ነበር፡፡ በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ
ለእርሱ ቤቱ ነበር፡፡ በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ
ለድንግልና (ድንግል ነበርና)፣ ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና) እና
ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ
ነቢይ ነው፡፡
አክአብና ኤልዛቤል ምሰኪኑን ናቡቴ ከአባቶቹ እርስት አፈናቅለው
በግፍ በገደሉት ጊዜ፤ ንጉሱንና ንግስቲቱን ሳይፈራና ሳያፍር
በግልጽ የዘለፈ ነብይ ነው፤ ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይንም
የለጎመ ነው፡፡ ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ፡፡ እርሱን ግን
በቀርሜሎስ ተራራ ቁራ ይመግበው ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ
ነበር ይሔው ቢቀርበት ጸለየ እግዚአብሔርም ከኮራት ወደ ሰራፕታ
እንዲወርድ አዘዘው በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ
ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ፡፡ ልጇ ሕጻኑ ዮናስ ቢሞትም
በጸሎቱ አስነሳላት፡፡ ቀጥሎም በጸሎት ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት
የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል ሕዝቡም፡፡ ይህንንም ያዕቆብ
በመልእክቱ እንዲህ ሲል መስክሯል ያዕ 5 ÷16 "የጻድቅ ሰው
ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ
ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ
ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥
ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች"
ነቢዩ ከኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር
ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል፡፡ መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት
ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ሐሰተኛ ነቢያትን በወንዝ
ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል:: ይሕንን የሰማች ኤልዛቤልም
ትገድለው ዘንድ አሳደደችው፡፡ "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና
ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት
ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ
ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው፡፡
እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ
ኤልያስ በክፋተኞች ላይ 2 ጊዜ እሳትን አዝንሟል::
የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን
"የምትሻውን ለምነኝ" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን" አለ፡፡ 3 ጊዜ
ሊያስመልሰው ሞከረ፡፡ ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው፡፡
ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ
እሳት ወርዶ ነጠቀው ለኤልሳዕም መጎናጸፊያውን ጣለለትና
አረገ፡፡
(1ኛ ነገስት ምዕራፍ 17 እስከ 2ኛ ነገስት ምዕራፍ 2 ታሪኩን
በስፋት ያንብቡ )
የቅዱሳን ነቢያት ረድኤት በረከት አይለየን፡፡
@wdasemaryam
1.2K viewsDesalegn Dagne ✥ድንግል ሆይ ሁሉን ከሚያስብ ሁሉን ከማይዘነጋ ከልጅሽ አሳስቢ✥, 15:10