2022-09-14 22:55:12
ትልቅ ሆቴል ውስጥ ሪሴፕሽን ሆኖ የሚሰራ የምንቀራረብ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ በስራ ላይ ሳለ ከእለታት ባንዱ ቀን አንድ ቦርሳ የያዘ ሰው ይመጣና 9 ቁጥር ተይዞ እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ክፍሉም አልተያዘም ነበርና ቁልፍ ተቀበለ፡፡ ባለቦርሳውም ሰውዬ አስተናጋጁን 9 ቁጥር ሻማ፥ ቢላ፥ አፕል እና ብርጭቆ እንዲያመጣለት ጠየቀ፡፡ ወዳጄም እየተገረመ የተባለውን ያቀርብለታል፡፡ ሰውዬም እየሳቀ ወደ ክፍሉ ይገባል፡፡ ባጋጣሚ 9 ቁጥር ክፍል ጎን ያለው ሪሴፕሽኑ ክፍል ነበርና ጓደኛዬ ሌሊት ላይ በጣም አስደንጋጭ ነገር ሰማ፡፡ የእንሰሳት ጩኸት፥ ኡኡታ፥ የህፃን ልጅ ለቅሶ፥ የሚሰባበሩ እቃዎች ድምፅ፡፡ በዚህ የተረበሸው ጓደኛዬ እስኪነጋ ጠብቆ የተፈጠረውን ለማወቅ ጓጓ፡፡ ጠዋት ላይም ባለቦርሳው ሰውዬ በሙሉ ፈገግታ ቁልፍ ሲያስረክብና አስተናጋጁ ምን እንደተፈጠረ ለማየት ሮጦ ሲገባ......ሁሉም ነገር ባለበት እንጂ የተቀየረ ነገር የለም፡፡ አልጋው በስነስርአት ተነጥፏል፡፡ ብርጭቆውም፥ ቢላውም፥ አፕሉም ሻማውም ባሉበት ተቀምጠዋል፡፡ ይህም የሆነው መስከረም አንድ ቀን ነበር፡፡ በ ነገሩ የተገረመው ወዳጄ ግራ እንደተጋባ ወራት አለፉት፡፡
ከአንድ አመት በኋላ በዚያው ተመሳሳይ መስከረም አንድ ቀን ባለቦርሳው ሰውዬ ተመልሶ መጣ፡፡ በድጋሜም 9 ቁጥር አልጋ ተይዞ እንደሆነ ጠየቀ፡፡ በዚህም አመት ክፍሉ ስላልተያዘ ቁልፍ ተሰጠው፡፡ በድጋሜም 9ቁጥር ሻማ፥ ብርጭቆ፥ ቢላ እና አፕል አምጡልኝ አለ፡፡ አመት ሙሉ ግራ የተጋባው ጓደኛዬም የማወቅ ጉጉቱ እየጨመረ የተባለውን አቀረበለት፡፡ በዚያም ሌሊት እነዛኑ የሚረብሹ ድምፆች ሰማ፥ የሚያለቅሱ ህፃናት፥ የእቃዎች መሰባበር እና የእንሰሳ ድምፆች፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ወደ ክፍሉ የሚወጣ ወይ የሚገባ ሰው መኖር አለመኖሩን ሲከታተልም አነጋ፡፡ ሲነጋ ባለቦርሳው ሰውዬ እንደተለመደው ከፈገግታ ጋራ ቁልፍ ሲያስረክብ ጓደኛዬ ሮጦ ቢመለከት ምንም ነገር የለም፡፡ አልጋው ባግባቡ እንደተነጠፈ፥ እቃዎቹም ምንም ሳይነኩ በተቀመጡበት ነበሩ፡፡
በዚህ ባለቦርሳ ሰውዬ ሚስጥር እጅግ ግራ የተጋባው ወዳጄ አመቱን ሙሉ በጉጉት ሲጠብቅ ከረመና መስከረም አንድ ደረሰ፡፡ እንደተለመደው ሰውዬው ከነቦርሳው መጣና 9ቁጥር ክፍልን ያዘ፡፡ እንደተለመደው 9ቁጥር ሻማ፥ ብርጭቆ አፕልና ቢላ ጠየቀ፡፡ እንደተለመደው ሌሊቱን ሙሉ አስፈሪ ድምፆች ሲሰሙ አደሩ፡፡ ሲነጋ እንደተለመደው ቁልፍ ሲያስረክብ 9 ቁጥር ክፍል ምንም አይነት ምልክት አልተገኘበትም፡፡ በዚህ ጊዜም አስተናጋጁ ይህንን ሚስጥር ከራሱ ከሰውዬው ሊጠይቅ ወሰነ፡፡
“አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ነበር “
“ጠይቀኝ” አለ ሰውዬው በፈገግታ::
“ለምንድነው ሁልጊዜ መስከረም አንድ ብቻ የምትመጣው?
ለምንድነው ሁልጊዜ 9 ቁጥር ክፍልን የምትይዘው?
9 ቁጥር ሻማው አፕሉ ቢላውና ብጭቆውስ ምን ያደርጉልሃል?
ሌሊት ላይ የሚሰሙት አስፈሪ ድምፆችስ የሚመጡት ከየት ነው?”
አለና ጠየቀው፡፡
ሰውዬም እየሳቀ
“ለማንም የማትናገር እና ሚስጥር የምትጠብቅ ከሆነ እነግርሃለሁ” አለው፡፡
ጓደኛዬም “ለማንም አልናገርም ንገረኝ” ሲል መለሰ፡፡
ሰውዬም ለማንም እንዳይናገር አስማለና ሚስጥሩን ነገረው፡፡
.
እነሆ ጓደኛዬም ሚስጥር ጠባቂና መሃላውን አክባሪ በመሆኑ የባለቦርሳውን ሰውዬ ሚስጥር ምንነት ለኔም አልነገረኝም
.
ምስጢር የምትጠብቁበት ዓመት ይሁንላችሁ
100 viewsGlamor, 19:55