2023-04-15 13:51:22
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ስለ ህወሃት የጦር ዝግጅት አገኘሁት ያሉት መረጃ!
ህወሃት አርሚ 44 የተባለው የጦር ክፍል፣ በጎንካ፣ሰበበራ ወጀራት አካባቢ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገ ይገኛል። በቅርቡ ደግሞ በ6 ኤፕሪል 2023 በሃውዜን ፣ ነበለት ፣ወርቃ ኣንባ እንዲሁም በአግበ እሰከ የጭላ ባለው ኣከባቢ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ሰልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በተጨማሪም ከክፍቶ ፣ጋርጃለ፣ታኦ በሚባሉ በአላማጣ ኣከባቢ በሚገኙ ቦታዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወኔ ሰራዊት በእዚሁ እለት ገብቷል። እስከ እዚህ እለት ደረስ የወያኔ ታጣቂዎች የፈቱት ትጥቅ የለም። የተሰጣቸው መምሪያ የለም። መረጃዎች የሚያሳዩት የወያኔ ታጣቂዎች በከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ሰልጠና መጠመዳቸውን ነው። ይህ መረጃ እንደጠቆመው ይህ የወያኔ እንቅስቃሴ በማእከላዊ መንግስት እንደሚታወቅ ነው። ወታደራዊ ስልጠና ለምን እንዳስፈለገ ወያኔዎች ለወታደሮቻቸው የሚሰጡት ማብራሪያ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ባወጣኋቸው ጽሁፎች እንደገለጽኩት በህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በይፋ ሲነገር የነበረው “የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ ስምመነቱን ከሚቃወሙ ከአማራና ከኤርትራ ሃይሎች ጋር ለምናደረገው ጦርነት ነው” የሚል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ወያኔ ከተተኳሽ ውጭ ያሉ ወታደራዊ ሎጂስቲክን ከአዲስ አበባ በወያኔ ደጋፊዎች ባላሃብቶች አስተባባሪነት እየተገዙ በአፋር በኩል በመኪና አስከ 100000 ሽህ ብር ጉቦ እየከፈሉ እያስገቡ ነው። ልብስ፣ የፕላስቲክ ኮዳዎች፣ ጫማዎች የጫኑ በርካታ የጭነት መኪናዎች ትግራይ ይገባሉ። የተተኳሽ እጥረት ለማስወገድ ወያኔ ሰፊ የኮንትሮባንድ ግዥ በማካሄድ ላይ ይገኛል። የክላሽ፣ የብሬን ፣የድሸቃ ተተካሽ በኮንትሮባንድ እየተገዛ በአፋር ጉጉውዶ ዳንደ ወደ ሞኮኒ በግመሎች እንደሚገባ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ከዚህ በፊት ወያኔ ከትግራይ ውጭ ለሽብር ስራ የመመለመላቸው በሽዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች እንዳሉ አሳውቀን ነበር። ከእነዚህ ሰልጣኞች መሃል ይሁኑ አይሁኑ ባይታወቅም በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች በአዲስ አበባ በኩል ወደ ወለጋ በመሄድ ኦነግ ሸኔ እየተቀላቀሉ እንደሆነ፣ በርካታ የሚታወቁ የወያኔ የልዩ ሃይል ኮማንዶ አባላት አዲስ አበባ ውስጥ እየገቡ እንደሆነ፣ የወያኔ ከፍተኛ የመረጃ አባላትም አዲስ አበባ ውስጥ እንዳሻቸው የሚንቀሳቅሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህን እና ሌሎች መረጃዎችን መንግስት ቢሰማም ባይሰማም ማድረስ ለሚችሉ አካላት ማስተላለፋችንን አላቆምንም። እነዚህ የወያኔ የሰራዊት አባላት በአዲስ አበባ ወስጥ አንዳንድ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች መታየት ጀምረዋል። የበለጠ መጣራት የሚገባቸው መረጃዎች በእጃችን ላይ ይገኛሉ።
ከአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ሲተራመስ በነበረባቸው ቀናት ውስጥ ወያኔ በሌላ በኩል የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ይህን ይመስላሉ። በሱዳን ግንባር ኣርሚ 27 አርሚ 31 እን አርሚ 70 በስየ አብርሃ እና ሳምሬ ብዱን፣ በበረከት እና በማይካድራ በኩል በረሀውን ይዘዉ ወልቃይት ለመቆጣጠር እቅድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው። የወያኔ የምእራብ እዝ፣ 5ክ/ጦር ማይጠብሪ ለመያዝ በቀኝ እና በግራ እቅድ አውጥቷል። የአማራ ልዩ ሃይል ግን በዚህ ወቅት ተበትኗል።
በሰሜን ጎንደር የሚገኙትን የማይፀምሪ ግንባር 3ቱ ወረዳዎችን እና የወልቃይት ቀጠናዋችን ለመቆጣጠር በማሰብ ጁንታው እራሱ የአደራጃቸውን የወረዳዋችን አመራሮች ሽሬ ላይ አዘጋጅቶ በአሁኑ ሰአት እየተጠባበቀ ይገኛል። በወያኔዎች ካምፕ እየተነገረ ያለው የፌደራል መንግስት በእነዚህ ማይፀብሪ እና ወልቃይት ግንባር አካባቢዎች በቅድሚያ መከላከያ አስገብቷል፣ ቀጣይ የፌደራል ፖሊስ ያስገባል። ከላይ የተጠቀሱት ቦታዎች በ2ቱ ሰራዊት ከተሸፈነ በኋላ የአማራ ልዩ ሃይል ጠቅሎ እንደወጣ በቀጥታ ትገባላችሁ የሚል ቃል በፌደራል መንግስቱ ተሰጥቶናል የሚል ነው። ጁንታ ተዋጊዎቹን በእዚህ አባባል ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጎ በመጪው 3ቀናት ውስጥ ለመግባት ተዘጋጅቶ እየተጠባበቀ ነው።
እንዲህ አይነት ቃል በፌደራል መንግስቱ ይገባላቸው ወይም አይገባላቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም ጁንታው ለታጣቂዎች “መንግስት በገባው ቃል መሰረት እማይፈፅም ከሆነ በሃይል እንገባለን” የሚል አማራጭ እቅድ እንዳለው ለሰራዊቱ ገልጿል።
ከመንግስት የደህንነት ሰዎች የሚመጣው መረጃ፣ “ይህ የጁንታ ታጣቂ የጥፋት ቡድን እስከ አሁኑ ሰአት ድረስ ትጥቅ አልፈታም። እንደ ጁንታ፣ የመጨረሻ ውሳኔው የወልቃይት፣ ጠለምት*፣ራያ ቦታዋች ካልተመለሱ ትጥቅ አንፈታም በማለት ለጥፋት ተዘጋጅተው ጥፋት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ይታወቅ” የሚል ነው። ቦታዎችን መጥቀስ አስፈላጊ ባይሆንም፣ ልዩ ሃይሉ ለቆ በመሄዱ በመከላከያ ሆነ በሌላ ሃይል ያልተሸፈኑ፣ ወያኔዎች ጦራቸውን ያለምንም ከልካይ ማስገባት የሚችሉባቸው ግንባሮች እየተፈጠሩ ነው።
በአንደኛው ግንባር ከዚህ ቀደም የህወሓት ወታደሮች የነበሩትን በጦርነቱ ያልተሳተፉትን በጀሌ ያለ ትጥቅ በምህረት ስም አስገብቷል። ጁንታው በማይጠብሪ ወረዳ አዲማይዳጉሳ፤ ማይተክሊት ና ሀይዳ የሚባሉ ቦታዋችን፣ በአካሉ አብርሃና ሀጎስ መስፍን በሚባሉ የጁንታው አመራሮች በቁጥጥር ስር አድርጎቸዋል። ይህ ቦታ ማለት የተከዜ ወንዝን ተሻግሮ በግራ ክንፍ፣ ወርቅ ማውጫው ይዞ ለማይጠብሪ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት 40 ክ/ጦር የአንገረብ መደማምር ወይም ለሁመራ በቅርብ ርቀት ሸረሪና የሚባለው ቦታ ላይ ተጠግቶ ይገኛል። በተጨማሪም በአዲጎሹ፣ በቁራሪትና ማይጋባ የተከዜ ወንዝን ተፋሰስ ይዞ የተጠጋ ሀይል አላቸው። ይህን መረጃ ለአማራ ክልል መሪዎች በራሳቸው የደህንነት መዋቅር እንዲደርስ የተደረገ ቢሆንም በጠቅላላ በሃገርና በክልሉ የደህንነት መስሪያ ቤት ዙሪያ የሚታየው መዝረክረክ የሚያሳስባቸው አካላት በኛ በኩል ለክልሉና ለፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ መሪዎች እንዲደርሳቸው ይሉኩልናል። ደርሶናል የሚል ምላሽ ባናገኝም ተመሳሳይ መረጃዎችን ባላፉት ሁለት አመታት ስናደርስ ቆይተናል።
ሌላው ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር በተያያዘ ችግር የፈጠረው ጉዳይ፣ የፌደራል መንግስቱ የወልቃይትና የራያን ጉዳይ እንዴት ሊፈታው እንዳሰበ ግልጽ አለማድረጉ ነው። በወያኔ በኩል በተደጋሚ በውስጥ በስብሰባዎቻቸው ሆነ በአደባባይ የሚናገሩት ግልጽ ሆኗል። የእነዚህ ሁለት ቦታዎች ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት እንደሚፈታ ከመንግስት ጋር ተግባብተናል እያሉ ነው። በወያኔ በኩል በህገ መንግስቱ መሰረት ማለት ቦታዎቹ መጀመሪያ በቅድሚያ ወደነበሩበት የትግራይ አሰተዳደር ተመልሰው ከዛ በኋላ በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚነሳ የማንነትና የይገባኛል ጥያቄ ካለ በህገ መንግስቱ ይፈታል ማለት ነው።
ወያኔዎች ለሰራዊት አባላቶቻቸው ለደጋፊዎቻቸው ደጋግመው ይህን እየተናገሩ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ከፕሪቶሪያው ስምምነት መሃል ብዙ ተግባራት ቢያከናውንም ካልፈጸማቸው ተግባራት መሃላ የአማራን ሃይሎች ከወቃይትና ከራያ አሰውጥቶ ለትግራይ ማስረከብ እንደሆነ ጌታቸው ረዳ በሌላ ሚድያ ሳይሆን በኢትዮጵያ ቴለቪዥን ላይ ቀርቦ ተናግሯል።
603 views10:51