2023-03-20 07:06:41
ቀጂነት!፨፨//፨፨
አንድ ሰው በሕልሙ ፈጣሪን አገኘውና አጋጣሚውን በመጠቀም ሁል ጊዜ በእውኑ ያስብ የነበረውን ጥያቄ ጠየቀው ይባላል - በጥንት አፈ-ታሪክ፡፡ ጥያቄው እንዲህ የሚል ነበር፡- “ከአፈር ሰውን ማበጀት እኮ ያን ያህል ከባድ አይደለም፣ ለምን እንደተአምር ይታያል?” አጠያየቁ ለክርክር በተዘጋጀ ዝንባሌ እንደነበረ የፊቱ አስተያያት ያሳብቅበታል፡፡ ፈጣሪም፣ በታላቅ ትእግስትና ርህራሄ እየተመለከተው፣ “እስቲ ሰውን ከአፈር መስራት ቀላል ከሆነ ከአፈር ሰውን ፍጠርና አሳየኝ” በማለት መለሰለት፡፡ ሰውየውም አፈር ከመሬት ለማንሳትና ስራውን ለመጀመር ጎንበስ ሲል፣ ፈጣሪ አቋረጠውና “ያሰብከውን ሰው ለማበጀት ከመነሻው የራስህን አፈር መጠቀም አለብህ” አለው ይባላል፡፡
ቀጂነት፣ የእኛ ያልሆነውን ነገር የእኛ እንደሆነ ማስመሰል፣ አዲስ ነገር ከመጀመር ይልቅ ሌላው አንድ ነገር ሲጀምር አጠገቡ ሄዶ ያንኑ መድገም፣ አዳዲስ ነገሮች የጀመሩ ሰዎችን ስራ ማንቋሸሽና ማራከስ . . . የዘመናችን ችግር! ብዙ ሰው የራሱን ነገር ከመጀመርና አዲስ ፈር ከመቅደድ ይልቅ የሌላውን ማየት፣ መከታተልና መቅዳት፣ አልፎም ማራከስ ይቀናዋል፡፡ በቢልየን የሚቆጠር የአለም ሕዝብ የጣት አሻራ በማይመሳሰልበት … የዚህ ሁሉ ሕዝብ የአይን ንድፍ በሚለያይበት … የሁላችን የጸጉር መለያ ኮድ በማይገናኝበት … በየሃገራቱ የሚወርዱ የበረዶ ብናኝ ቅርፊቶች (Snowflakes) ቅርጽ በሙሉ አንድ አይነት ባልሆነበት … በፈጠራ ውበት በሞቀና በደመቀበት አለም ውስጥ እየኖርን የሌላውን ሰው ግኝትና ጅማሬ ካልቀዳን ወይም ካላዋደቅን የምንሻሻል ካልመሰለን፣ የሆነ የጎደለ ነገር አለ፡፡
በጉዳዩ ላይ በሚገባ ለማሰላሰልና ወደ እውነት ለመጓዝ . . .
- ሌላ ሰው ጋር የሌለና አንተ ጋር ብቻ ያለ የፈጠራ እይታና ብቃት ፈጣሪ ራሱ እንደሰጠህ ማስታወስ ለአዳዲስ ነገሮች እንድትነሳሳ ያደርግሃል፡፡
- ከምንምና ከባዶ ተነስተህ ምንም አይነት ነገር መፍጠር እንዳማትችል ማወቅ ሚዛናዊና እውነታን ያገናዘብክ ሰው ያደርግሃል፡፡
- ያለህ የፈጠራ ብቃት የተነሳው በሌሎች ፈር-ቀዳጅነት መሰረት ላይ መሆኑን መገንዘብ ሌላውን አክባሪ ያደርግሃል፡፡
-ለመነሻነት የምትጠቀምባቸውን የሌሎች ሰዎች ፈጠራዎች፣ ግኝቶችና ስራዎች እውቅና መስጠት ትልቅ ሰው ያደርግሃል፡፡
- የሰውን ሃሳብ፣ ፈጠራና የአእምሮ ንብረት አለመስረቅ ጨዋና መልካም ዜጋ ያደርግሃል፡፡
- የግድ ከሌላው ሰው ካልቀዳህና ካልኮረጅክ ምንም ነገር ማድረግ እንደማትችል ከማሰብ ነጻ መሆን ከጠባብነትና ከውስንነት እንድትወጣ ያደርግሃል፡፡
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q
3.0K viewsምኖረው እኔ ሚፈርደው ሌላ, edited 04:06