2022-10-06 08:17:19
#_የፍቃድ_ጾም_ነው_እያልን_ያልተጠቀምንበት_ታላቁ_የጽጌ_ጾም!
#_ጾሙን_በመጾማችን_ምን_አይነት_ጸጋ_እና_በረከት_እናገኛለን?
/ቪዲዮውን ለማየት ያልተቻላችሁ ይኸው በጽሑፍ ቀርቦላቹኃል!/
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
ሼር በማድረግ ለእመቤታችን ልጆች አዳርሱ!
የወለላይቱ እመቤት ልጆች በቅድሚያ እንኳን ለእናታችን ለወለላይቱ እመቤት የስደቷ መታሰብያ ለሆነው ጾመ ፅጌ አደረሳችሁ፡፡ ፅጌ ጾም የምንለው በአጭሩ የእመቤታችንን የስደቷን ጊዜ የምናስብብት ጾም ነው፡፡ ይህም ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን ያለው ነው፡፡
በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ሕግና ሥርዓት መሠረት ከመስከረም 26 ቀን እስከ ሕዳር 6 ቀን ያለው 40 ቀን የወለላይቱን እመቤት እና የተወዳጅ ልጇን ስደት በማሰብ ዘመነ ፅጌን ወይም ወርኃ ፅጌን ታስባለች ታከብራለች፡፡
ይህ 40 ቀን የእመቤታችን እና የልጇ ስደት የሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ወቅቱ የአበባና የፍሬ ስለሆነ እመቤታችን በአበባ ጌታችን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን በአምላክነቱ እሷ በአምላክ እናትነቷ በተለያዩ ምስጋናና ጥዑም ዜና ይመሰገናሉ፡፡
ስደት ሲነሳ ሐዋርያት በወንጌል የተነሳ ተሰደዋል ሞተዋል፡፡ ቅዱሳን ስለ ክርስቶስ ፍቅር በየገዳሙ ተሰደዋል፡፡ እነዚህና ሌሎችም ስለ ስሙና በስሙ ምክንያት ሲሰደዱ የእመቤታችን ስደት ግን ልዩ ነው፡፡
የወለላይቱ እመቤት ልጆች እመቤታችን ልጅዋን ቅዱስ አማኑኤልን ይዛ ነው የተሰደደችው፡፡ ቅዱሳን በአምላካቸው ስም ሲሰደዱ እመቤታችን ደግሞ አምላክን ይዛ ተሰዳለች፡፡
እመቤታችን የተሰደደችው ምድራዊ ንጉስ ሄሮድስን ፈርታ ሸሽታ አይደለም፡፡ እሷማ ይዛው የተሰደደችው ሄሮድስን በዓይኑ እይታ ብቻ ከምድረ ገጽ የሚደመስሰውን አልፋና ኦሜጋ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛው ነው፡፡ ደግሞም እናውቃለን በየሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ 5 ቁጥር 1-10 ላይ ልጅዋ ሐናንያና ሰጲራን ሳይመታ የጣለ እና የገደለ ነው፡፡
ስድት የማይገባት የእኛ እናት ወለላይቱ እመቤት የእኛን የኃጢአተኞችን ፈንታ ነው የተሰደደችው፡፡ እመቤታችን በመሰደድዋ ከገነት እንድንሰደድ ያደረገን ሰይጣንን አሳዳዋለች፡፡ በስደትዋ ወቅት በቀላሉ የማይነገር ከሕሊና በላይና ልብ ሰባሪ መከራ ተቀብላለች፡፡ በዚህም ስደትን ተሰዳ ባርካ ሰጥታናለች፡፡
በተለይ በውጭ አገር ያላችሁ ወንድም እህቶቼ በስደታችሁ መከራ ሲገጥማችሁ ስደትን ከእናንተ በበለጠ የእግር ጥፍራ እስኪነቀል ሀገር ለሀገር የተሰደደችውን እመቤታችንን እያስታወሳችሁ ተጽናኑ በነገሮች ሁሉ እንድትረዳችሁ ተማጸኗት፡፡
የወለላይቱ እመቤት ልጆች አሁን ስለ ስደት ለማውራት ሳይሆን በስደትዋ ምክንያት ታስቦ ስለሚጾመው ስለ ፅጌ ጾም ነው፡፡ በመሠረቱ ጾም ጾም ሲባል መጾሙ ላይ እንጨቃጨቃለን መብላቱ ላይ ግን እንስማማለን፡፡ ይህ የሚሆነው ለነፍሳችን ሳይሆን ለሥጋችን ስለምናደላ ነው፡፡
ለስንት ዘመን ስንበላ የከረምነው ዓሳ ‹‹ይበላል አይበላም›› እያልን የምንጨቃጨቀው የመጾም ሳይሆን የመብላት ፍላጎታችንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው የዓሳ ጉዳይ ሐሳብ ሆኖብን ጎራ በመለየት በመብላት የተጠመድነው፡፡
ወዳጆቼ ይህ ችግራችን ገፍቶ በገና ጾም ቅበላ ላይ ገና ጾም የሚገባው ‹‹ህዳር 14 ነው አይደለም ህዳር 15 ቀን ነው የሚገባው›› እያልን የምንወዛገበው አንዱ የመብላት ፍላጎታችን ማሳያችን ነው፡፡ ብቻ ጾም ሲነሳ ጻር የሚሆንብን ሥጋን ለመብላት ካለን ሥጋዊ ፍቅር እንጂ ሌላ አይደለም፡፡
እውቀትና ጥበብ እንጂ ሃይማኖት የሌላቸው የሰለጠኑት ምዕራባውያን እና ሌሎች ሀገራት ሥጋ ለሥጋችሁ ስጋት ነው ያስረጃል ጤና ይነሳል እያሉ በሚዲያ እያስተማሩ ብሎም እያስጠነቀቁ ሕዝባቸውን አትክልት ተመጋቢ ሲያደርጉት እኛ በሃይማኖት የምንኖረው ጠንካራ ጿሚ መሆን አቃተን፡፡
አዳም እና ሔዋን በገነት ሲኖሩ ይመገቡት የነበረው ሥጋ ሳይሆን አትክልት እና ፍራፍሬ ነው፡፡ በየትኛውም መጽሐፍ በገነት ሥጋ በሉ የሚል ተጽፎ አናገኝም፡፡ ይልቁንም ከገነት ከተባረሩና ወደዚህ ምድር ከወደቁ በኃላ ነው ሥጋን የበሉት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሥጋ ከበደል በኃላ የመጣ የሰው ልጆች ምግብ ሆነ፡፡
አንዳንዶቻችን መምህራን ስናስተምር ‹‹የጾም ጥቅሙ፣ ሥጋን ለነፍስ ለማስገዛት እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ ሥጋህን ከገዛህ በጥቂቱ ጾመህ ብትበላ ችግር የለውም›› እያልን የራሳችንን የጾም ድክመት ለሰዎች እያሳየን በጾም ሕይወት እንዳይጠነክሩ እናደርጋለን፡፡
አባቶቻችንና እናቶቻችን በየገዳሙ ከሚገባቸውና ከመጠን በላይ የሚጾሙት ሥጋቸውን ለነፍሳቸው ማስገዛት አቅቷቸው ሳይሆን ጾም ወደ ብቃት ደረጃ ከሚያደርሳቸው መንገድ አንዱ መሆኑን ስለሚያውቁና ስለተጠቀሙበት ነው፡፡
አባቶቻችን ከጾም ትጋታቸው የተነሳ በመጨረሻ ከተፈጥሮ ሕግ በላይ በመሆን እህል እስከ አለመብላት ውኃ እስካለመጠጣት ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ በጾም ትጋታቸው ድካማቸው ተቆጥሮላቸው ከመልአክ እጅ ሰማያዊ ሕብስትና ጽዋ እየተቀበሉ እስከ መብላት ይደርሳሉ፡፡
እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሱት እንደ እኛ ‹‹አግዚአብሔር የማያውቀው የለም›› እያሉ በመብላት በመጠጣት ሳይሆን በጾም ተወስነው ነው፡፡
ጾም አንዱና ዋኛው የጸጋ መንገድ ነው፡፡ የትኛውንም ገድለ ቅዱሳን ብንመለከት አባቶቻቸን በልተው ሳይሆን ጾመው ነው የበቁት የተሰወሩት፡፡
ለዚህም ነው ጾሞ እንጂ በልቶ የበቃ ቅዱስ እስከ ዛሬ ያልተገኘው፡፡ ምናልባት ከበቁ በኃላ እንደ ፈለጉ ሊበሉ ይችላሉ፡፡ የአባቶቻችን የመንፈሳዊ ሕይወት አኗኗር የተመሠረተው በጾም ላይ ነው፡፡ ጾም ለእነሱ ቅጣት ሳይሆን ደስታ ነው፡፡ ጾም ለእነሱ ለሥጋቸውም ለነፍሳቸውም የተመቸ ነው፡፡
አባቶቻችን ወጥ የሆነ የጾም ሕይወት ነው ያላቸው፡፡ እኛ ደግሞ ስንጾም ለተወሰነ ሰዓት ከእህል ከውኃ እንከለከልና በኃላ ሰዓቱ ሲደርስ ጾሙን በምግብ ለማካካስ እንጥራለን፡፡ ጾም በመንፈሳዊ ጥቅሙ መንፈሳዊ ጥንካሬን እንድናገኝ በኃጢአታችን እንድንጸጸት ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብና ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ጭምር ነው፡፡ እውነተኛ ጾም አንድን መንፈሳዊ ሰው እራሱን እንዴት መቆጣጠር እንዳለበት ያሰለጥነዋል፡፡ ራስን መቆጣጠር ደግሞ ለቅድስና ሕይወት ዋና መሠረት ነው፡፡
ስለዚህ ጾምን የምናዘወትር ከሆነ ሥጋችንም ነፍሳችንም በጾም ቁጥጥር ስር ሆነች ማለት ነው፡፡ የሚጾም ሰው ሥጋውን እየጎዳ ነፍሱን የእግዚአብሔርን በረከት ያጠግባታል፡፡ የሚጾም ሰው ለጊዜው በሥጋ ቢከሳ ቢጎሳቆልም በነፍሱ ግን ምቾት ያለው ሰው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከምግብ እና ከመጠጥ ያልተቆጠበ ሰው ሕይወቱን ለጌታችን አሳልፎ ለመስጠት ሥጋውን ለመቆጣጣር እና ለመግዛት ይከብደዋል፡፡
የወለላይቱ እመቤት ልጆች ብዙዎቻችን እንደለመድነው እንደተማርነውም ‹‹ፅጌ ጾም የፍቅር ጾም እንጂ የአዋጅ ጾም አይደለም›› እንላለን፡፡ ልክም ነው፡፡ ግን ፅጌ ጾም የፍቅር ጾም ከሆነ ለምን በፍቅር አንጾምም? ‹‹አይደለም›› በምትለዋ አፍራሽ አማርኛ በፅጌ ፆም ስንቱ ሳይጠቀምበት ቀረ፡፡ ከሌሎቹ አጽዋማት እያሳነስነው ስንት የእመቤታችን በረከት ቀረብን፡፡ ዛሬ እንኳን በልተን ጾም ትተን ቀርቶ ጾመንም ጸልየንም ሰይጣን ከእኛ አልርቅ ፈተናችን አልላቀቅ ብሎናል፡፡
96 views05:17