Get Mystery Box with random crypto!

ማዲንጎ ዘፋኝ እንደሆነ እያወቀ እንጦጦ ማርያም የመጣው ቤተ ክርስቲያን ፍርድ ቤት ሳትሆን ሐኪም ቤ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ማዲንጎ ዘፋኝ እንደሆነ እያወቀ እንጦጦ ማርያም የመጣው ቤተ ክርስቲያን ፍርድ ቤት ሳትሆን ሐኪም ቤት እንደሆነች ስላወቀ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ የምትፈርድ ሳትሆን ምህረት የምትለምን ናት፡፡ አንድ መርሳት የሌለብን ነገር ማዲንጎ ኦርቶዶክስ ነው፡፡ በእግዚአብሔር የሚያምን፣ በእመቤታችን ምልጃ የሚታመን፣ ስመ ክርስትና ያለው ሰው ነው፡፡

ወዳጆቼ ዘፋኝ በሞተ ቁጥር እኛው ዘፈናቸውን የምናዳምጥ አንድ ጥቅስ አንጠልጥለን፣ ጥቅሷን እየጠቀስን የሞተውን ሰው በጥቅስ ባንዘልፍ መልካም ነው፡፡ መጨረሻችንን ስለማናውቅ የሰውን ሞት አይተን፣ የሰማዩን ፍርድ ሳንመለከት አንፍረድ፡፡

በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ለመዳን፣ ገነት ለመግባት ሦስት ሰዓት አልፈጀበትም፡፡ ሌባም ይሁን፣ ቀማኛ፣ ዘማዊ፣ ዘፋኝ ይሁን ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት ስለማናውቅ በማናውቀው ጥልቅ ባንል መልካም ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን ማንም ሰው ቢሞት እግዚአብሔር እንዲምረው መጸለይ እንጂ መፍረድ እና ሲዖል እንዲማገድ ሟሟረት የለብንም።

ወዳጆቼ እኔ ማዲንጎን በዘፋኝነቱ እየደገፍኩት አይደለም፡፡ ነገር ግን ዘፈኑን የሰማው ነው የሚኮንነው፡፡ ሁሉም በተለያየ ቦታ እና ሁኔታ እንዲሁም ቤቱ ቁጭ ብሎ ዘፈን በማዳመጥ ዘፋኙን እየተባበረ ዘፋኝ ገነት አይገባም ይላል፡፡ ዘፋኝ ገነት አይገባም ማለት እኮ የማይዘፍን ገነት ይገባል ማለት አይደለም፡፡

ሁሉም በሥራው ነው ገነት የሚገባው፡፡ አንድ ዘፋኝ ዘፈኑን በዩትዩብ ሲለቅ ቀድመንና ተሽቀዳድመን ዘፈኑን የምናዳምጥ እኛው ክርስቲያኖች ነን። ከሚሊዮን ተመልካቾቻው ውስጥ ከግማሽ በላዩ እኛው ክርስቲያኖች ነን። ፈዘናቸውን የምናዳምጠው፣ እነሱንም የምናደንቀው፣ ስናገኛቸው አብሬ ፎቶ ከልተነሳው የምንለው እኛው ሲሞቱ ኮናኞች እኛው።

አንድ የማውቃቸው ጳጳስ ‹‹ስለ ዘፈን እና ስለ ዘፋኝ ምን ይላሉ?›› ስላቸው፡፡ ‹‹አይ ልጄ ሰው በአፉ ባይዘፍንም በልቡ ይዘፍናል›› አሉኝ፡፡ በአፋችን ሳይሆን በልባችን የምንዘፍን ብዙ ነን፡፡

ወደ ማጠቃለያው ስመጣ ማዲንጎ ሌሊት ሲዘፍን አድሮ ጠዋት አመም ሲያደርገው በቅርቡ ወዳለ ክሊኒት መኪናውን እያሽከረከ ሄዶ ለሕመሙ ማስታገሻ እንተወጋ እዛው አርፏል፡፡ እንዲህ አይነት ሞት ምናልባት ሕክምናው በምርመራ እና በአሟሟቱ ሂደት የራሱን ውጤት እና መላ ምት ይናገራል፡፡ በመናፍስቱ ውጊያ ግን እንደዚህ አይነት ማለትም ሰው ሳያመው እየሠራ ቆይቶ በድንገት አመመኝ ብሎ ከሞተ ከመተት እና ከጥላ ወጊ ጋር ይያያዛል፡፡

በተለይ በዚህ በጥበቡ፣ በሩጫው፣ በኳሱ በእውቅናው ዓለም ወዘተ ከፍተኛ የሆነ በመተት እና በጥላ ወጊ የመገፋፋት፣ እድል የመቀማማት፣ አንዱ አንዱን የማጥፋት ክፉ አባዜ አለ፡፡ ማዲንጎ ብቻ ሳይሆን በእሱ ሞያ ያሉ አርቲስቶች ቀድመው የማዲንጎን አይነት የሞት ጽዋእ ጠጥተው አልፈዋል፡፡ እንደውም አንዱ ዘፋኝ ችግሩን ስላወቀ "እባካችሁ ጸበል ውሰዱኝ" እያለ ጸበል ሳይወስዱት እንደሞተ አውቃለሁ።

በመተት እና በጥላ ወጊ የሚሞት ሰው አሟሟቱ ይናገራል፡፡ ጤነኛ ሆኖ በድንገት አመመኝ ብሎ የሕክምና ተቋም ሳይደርስ በድንገት ይሞታል፣ አመመኝ ብሎ ሐኪም ቤት ቢሄድም እርዳታ ቢደረግለትም ይሞታል፡፡ ልቤን፣ ልቤን ወጋኝ፣ ራሴን ወጋኝ፣ ደረቴን ወጋኝ፣ ጎኔን ወጋኝ፣ መተንፈስ አቃተኝ፣ ደከመኝ ወዘተ እያለ በድንገት ይሞታል፡፡ ጠዋት ታይቶ ከሰዓት ይሞታል፣ ከሰዓት ታይቶ ማምሻ ይሞታል፣ ማታ በሰላም ተኝቶ ጠዋት ሞቶ ይገኛል፡፡ ቤት ወይም ቢሮ አልያም የሥራ ቦታ ቁጭ ብሎ፣ እየሠራ በድንገት ይሞታል፡፡

ወዳጆቼ ስንት መላከ ሞት የሆኑ ክፉ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ በጥበቡ፣ ሩጫው፣ በኳሱ ወዘተ ዓለም ያላችሁ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ካልቀረባችሁ፣ በጸሎት ካልበረታችሁ ሕይወታችሁን፣ ዕድላችሁን በምቀኞቻችሁ፣ በወዳጅ መሳይ ጠላቶቻችሁ ትነጠቃላችሁ፡፡ አንድ መረሳት የሌለበት አንድ ሰው በአንድ ሥራው ሲታወቅ የሚወዱትን ያህል አንዳንድ የሚጠሉት አለ። ከፍታውን ሲያዩ ዝቅታውን ለማየት ከላይ ወደ ታች የመጎተት ክፉ ሥራ የሚሠሩ አሉ። ታላቅ ስኬቱን ሲያዩ ለሞቱ ጉድጓድ የሚቆፍሩ አሉ።

ስለዚህ ኃላፊ በሆነ ዓለም ላይ እየኖርን የማያልፈውንና ችግራችንን የሚያሳልፈውን እግዚአብሔርን መዘንጋት የለብንም፡፡ ለጠላቶቹ፣ ለምቀኞቹ ልብ ይስጣቸው፡፡ የድምጻዊ የማዲንጎን ነፍስ የሚወዳት፣ የሚያከብራት የበላዔ ሰብእ እመቤት እመቤታችን በምልጇዋ፣ በቃል-ኪዳኗ በገነት ታኑረው፡፡ ለመላ ቤተሰቦቹ ልዑል እግዚአብሔር መጽናናትን ያድልልን፡፡

መስከረም 24-1-2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ