2023-03-19 06:55:50
እንግዲህ ምጽአት የምንለው ጌታችን ዳግም ወደዚህ ዓለም ለፍርድ የሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡ ምጽአት በሁለት ያከፈላል፡፡ አንደኛ የጌታ ምጽአት እና ሁለተኛ የጌታ ምጽአት ይባላል፡፡
የመጀመርያው የጌታ ምጽአት የምንለው ፦ ነብያት በተነበዩት፤አባቶች በሱባኤ ተስፋ ባደረጉት መሰርት ጌታችን ከድንግል ማርያም ተወልዶ ወደዚህ ምድር መምጣቱን ነው፡፡ ይህ ምጽአት ጌታ ለመአት ሳይሆን ለምህረት፣ ለአሳር ሳይሆን ለፍቅር፤ ለጸብ ሳይሆን ለእርቅ የመጣበት ነው፡፡ ይህ ምጻት የጌታን ምህረትና ለሰው ያለውን ፍቅርና ቸርነት ያየንበት ነው፡፡
ይህ ምጽአት የጌታን ፍርድ ሳይሆን የፍቅር መንገድ አሳይቶናል፡፡ ይህ ምጽአት እኛ የሰው ልጆች የዳንበት ነው፡፡ ይህ ምጽአት በሰይጣን ያጣነውን የልጅነት ክብር ያስመለሰልን ነው፡፡ ይህ ምጽአት ስለ እኛ ፍቅር ከግርፋት እስከ ሞት ዋጋ የከፈለበት ነው፡፡ ይህ ምጽአት ስጋውን የቆረሰበት ደሙን ያፈሰሰበት ነው፡፡
በዚህ ምጽአት ከክርስቶስ ጋር በእናቱ በእመቤታችን በድንግል ማርያም በኩል በስጋ የተዛመድንበት ነው፡፡ በዚህ ምጽአት በረከተ ስጋ በረከተ ነፍስ አግኝተንበታል፡፡ በዚህኛው ምጽአት ብዙዎች የንስሐ እድል አግኝተዋል ከቅድስናው በረከትም ተካፍለዋል፤ የሰማይ ቤታቸውንም አሳምረዋል፡፡
በመጀመሪያው ምጽአት ጌታ ከፈሪሳውያን ከሰዱቃውያን ጀምሮ ያሉትን ተከታዮቹንም አስተምሯል፤ መክሯል፤ የታመሙትንም ፈውሳል፤ ድንቅ ድንቅ ተአምራት አድርጓል፡፡ ይህ ምጽአት ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡
በሁለተኛውና በሚጠበቀው ምጽአት ፦ ጌታችን እንደ ቀድሞው በትህትና በፍቅር ሳይሆን ሊነገር በማይችል በታላቅ ክብር ነው የሚመጣው፡፡ በዚህ ምጽአት አይታገስም፤ ፊቱንም ለማየት አይቻልም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስፈራ ግርማ መለኮት፤ በታላቅ መፈራት ይመጣል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ማቴዎስ 24÷ 30 ላይ ‹‹የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ይመጣል›› ብሏል፡፡
ይህንንም ጌታ በሐዋርያት ፊት በደመና በሚያርግበት ጊዜ ሁለት ሰዎች ተብለው የተገለጡት የጌታ መላእክት ‹‹ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል›› ብለው ጌታ ለፍርድ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡ /የሐዋ 1÷11/
ታድያ ጌታችን በመጨረሻ የሚመጣው ለምህረት ለይቅርታ ለቸርነት ሳይሆን ለእያንዳንዱ ሰው በዚህ ዓለም እንደ መልካምና ክፉ ሥራው ዋጋውን ለመስጠት ነው፡፡ ይህንንም ጌታችን በዮሐንስ ራዕይ በምዕራፍ 22÷12 ላይ ‹‹እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ›› ብሎናል፡፡
ሲመጣ እንደ ቀድሞ ሰው ሆኖ በትህትና፤ በታላቅ ሰብእና ሆኖ ሳይሆን በፈራጅነቱ በዳኝነቱ በአምላክነቱ በግርማ መለኮቱ ነው፡፡ ዳኝነት ስንል በሰጠን ህግ ያለ ርህራሄ እንዳኛለን፡፡ እውነተኛ ዳኛ ዘመድ ባዳ ሳይል በህጉ ይዳኛል፡፡ ጌታም ኃጥእ ጻድቅ ሳይል በሥራችን ይዳኘናል፡፡
በዚህኛው ምጽአት የንስሐ እድል የለም፤ የንስሃን ዋጋ በቀበል እንጂ፡፡ ጽድቅ የመሥራት እድል የለም፤ የጽድቅን ዋጋ መቀበል እንጂ፡፡ በዚህኛው ምጻት ሥጋ በበደለበት ነፍስ የሚቀጣበት ነው፡፡ ሥጋ በጎ ነገር በሠራበት ነፍስ ዋጋ ተቀብላ፤ ጸጋን ታድላ፤ ለዘላለም ከጌታዋ ጋር የምትኖርበት ነው፡፡ ይችህ ቀን ምንኛ ታስፋራ ይሆን!
ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ በቅዳሴው ከሚያስፈሩት ነገሮች ውስጥ አንደኛው በአምላክ ፊት ለፍርድ መቆም መሆኑን ተናግሯል፡፡ ወገኖቼ እግዚአብሔር ፊት እንኳን ለፍርድ ለሽልማት መቆም እጅጉን ያሥፈራል፡፡ በፍርድ ቀን ባለጸጋው ስለ ባለ ጻግነቱ አይፈራም፤ ድሃም ስለ ድህነቱ አይታዘንለትም፡፡ ሁለም የሥራውን ያገኛል፣ በክርስቶስ ፊት የዘራውን ያጭዳል፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች ጌታ ሲመጣ ምን ይዘን እንጠብቀው ይሆን? ከጌታ ምጽአት በፊት ሞት ሲቀድመን፤ በነፍሳችን ምን ይዘን እንሄድ ይሆን?
ይቺ ቀን ጌታችን ህጉን ትእዛዙን አክብረው በተሰጣቸው እድሜ በጎ ነገር ሰርተው ላለፉት፤ ለተገኙት የማታልፍ መንግስተ ሰማያትን የሚያወርስበት ቀን ነው፡፡ ለኃጥአን ማለትም ንስሐ ሳይገቡ፤ ነፍሳቸውን ኃጢአት ሲቀልቡ፤ ለኖሩት ፍዳና ገሃነመ እሳትን የሥራቸው ዋጋ አድርጎ ይከፍላቸዋል፡፡ ግን ጌታችን ለጻድቃን ይፈርድላቸዋል በኃጥአና ላይ ይፈርድባቸዋል ስንል ጌታችን ና አንተ ጻድቅ ነህ የሚገባህ ይህ ነው፡፡ ና አንተ ኃጥእ ነህ ዋጋህ ይህ ነው ብሎ በተናጠል አይፈርድም፡፡ ለእኛ የሚፈርድልንና በእኛ ላይ የሚፈርድብን ሥራችን ነው፡፡ እርሱ ዋጋችንን ነው የሚሰጠን፡፡
የሠራነው ጽድቅና መልካም ሥራ ከሆነ በጻድቃን ጎን ያቆመናል፡፡ ሥራችን ኃጢአት እና ክፉት ከሆነ በኃጥአን ጎራ ያሰልፈናል፡፡ ጌታችን በማቴ 25÷31-33 ‹‹የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱ ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለየው እርስ በእርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል›› ቢልም የሚለየን ወገኖቼ ሥራችን ነው፡፡
ያኔ በሥራችን እርስ በእርስ እንለያያለን፡፡ ጌታ ለምንድነው ጻድቃንን በበጎች ኃጥአንን በፍየሎች የመሰለው? ብንል፡፡
በግ ፦ ትሁት ነው ወደ ምድር እያየ ይሄዳል፡፡ ጻድቃንም እለተ ሞታቸውን እያሰቡ በትህትና ይኖራሉና፡፡
በግ አፍረቷን በላቷ ትሰውራለች፡፡ ጻድቃንም የራሳቸውን ኃጢአት በንስሐ፤ የወንድማቸውን ኃጢአት በትእግስት ይሰውራሉና፡፡ እኛ ግን ለራሳችን እንደ ሸክም የከበደንን ኃጢአት ሰውረን፤ የሰውን ገልጠን እንኖራለን፡፡ የራሳችን ኃጢአት እንደ ምሰሶ በውስጣችን ተተክሎ፣ የሰውን ጉድፍ ነቅሎ ለመኖር እንጥራለን፡፡
በግ ከበረረ የሰው ልጅ ካመረረ እንደሚባለው በግ ከመካከላቸው አንዱን አውሬ ከነጠለው ይሸሻል አይመለስም፡፡ ጻድቃንም ከመካከላቸው አንዱ ከሞተ ሞታቸውን በማሰብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፡፡ የቆረጡትም ይመንናሉ ከመነኑም አይመለሱም፡፡ እኛ ግን ባየነው የወዳጅ የዘመድ ሞት፤ ለንስሐ ሕይወት መብቃት አቃተን፡፡
በግ ኑሮው በደጋ ነው፡፡ ጻድቃንም በደጋ በተመሰለው በመንግስተ ሰማያት ነው ኑሮአቸው፡፡ ስለዚህ በበግ ተመለሱ፡፡
ፍየል ፦ ትእቢተኛ ናት፡፡ ሽቅብ ሽቅብ ትመለከታለች፡፡ ፍየል ኃፍረቷን በላትዋ አትሰውርም፡፡ ኃጥአንም የራሳቸውን ኃጢአት በንስሐ፤ የወንድማቸውን ኃጢአት በትእግስት አይሰውሩም፡፡ እኛም ኃጢአታችንን በንስሐ አንሰውርም፡፡
ፍየል በዋለበት ቦታ፤ እህል፣ ከተክል እየገባ እየበላ ሰው ሲያሳዝን ይውላል፡፡ ኃጥአንም ሰውንም ፈጣሪንም ሲያሳዝኑ ይውላሉና፡፡
ፍየል ከመሃላቸው አንዱን አውሬ የበላው እንደሆነ ለጊዜው ይሸሻል፤ ኃላ ግን ይመለሳል፡፡ ኃጥአንም ከወገናቸው አንዱ የሞተ እንደሆነ ለጊዜው ይደነግጣሉ፤ ኃላ ወደ ቀደመ ግብራቸው ይመለሳሉ፡፡ ብዙዎቻችን የሰው ሞት ስናይ ለጊዜው እንደነግጣለን፤ ስለነፍሳችንም እንጨነቃለን ግን ብዙም ሳንቆይ እንረሳዋለን፡፡
ፍየል ኑሮው በቆላ ነው፡፡ ኃጥአንም የነፍስ ኑሮአቸው በቆላ በተመሰለው በገሃነም ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታ ጻድቃንን በበግ ኃጥአንን በፍየል የመሰለው፡፡ የአባቶቻችን አምላክ በቆላ ከተመሰለው ከሲኦል ይሰውረን፡፡
332 views03:55