2023-03-15 07:05:58
#_መከራን_በራስ_ሰው_መቀበል!
#_በመተት_ወዘተ_የምትሰቃዩ_በጥሞና_አንብቡት!
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በመንፈሳዊ ሕይወት እና በሥጋዊ/በዓለማዊ/ ሕይወት ስኬቶቻችን ከሰይጣን ባልተናነሰ ሁኔታ የራሳችን ሰዎች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ብዙዎቻችን ፈተናና መከራን የምንቀበለው ክብርም የምናገኘው በሰይጣን ብቻ ተፈትነን ይመስለናል። ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ ወዳጄ ከሰይጣን ባልተናነሰ ምናልባትም በባሰ መልኩ በራሳችን ሰዎች/የሰው የራስ ባይኖረውም/ መከራን ልንቀበል እንችላለን፡፡
በራሳችን ሰው መከራን መቀበል ክብር የሚያሰጥ ስለማይመስለን ፈታኞቻችንን እንደ ሰይጣን ከመታገስ ይልቅ ባደረሱብን መከራ ልክ ከፈጣሪ ፍርድ እንጠብቅባቸዋለን፡፡ ለዚህም ነው የበዳዮቻችንን ጉዳይ ፈጣሪ ፊት ይዘን በጸሎት ቆመን ‹‹እንደህ ሲያደርገኝ እንዴት ዝም ትላለህ፣ ፍረድልኝ፣ ፍረድበት፣ የእሱን/የእሷን መጨረሻ ካላሳየኸኝ የለህም…›› እያልን የምናማርረው በራሳችን ሰዎች መከራ ተቀብለን ክብር ማግኘታችንን ስለማናውቅ ነው፡፡
ወዳጄ ጌታ እራሱ ለልዩ አገልግሎት በመረጠው የእኔ ባለው በይሁዳ አይደል እንደ ዕቃ የተሸጠው? ለመከራ ተላልፎ የተሰጠው? እስኪ አንዱ ለአንዱ ክብርና መከራ እንደሆነ ወደ ገድሉ ይዤህ ጎራ ልበል፡፡ ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሐዋርያት የሰማዕትነትን መከራ ይቀበሉ ዘንድ ጌታችንንና እመቤታችንን ለምነው ነበር፡፡
ታዲያ አንድ እሁድ ቀን እኚህ አባት ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ እመቤታችን በብርሃን ሠረገላ ተጭና መላእክትን አስከትላ መጥታ ‹‹የጳውሎስ አበባ፣ የጴጥሮስ ፍሬ የልጄ ተክል ወዳጄ ተክለ ሐዋርያት ሰላምታ ላንተ ይገባኃል፡፡ እነሆ የተመኘኸውን ታገኘዋለህ ጊዜው ቀርቧልና በርታ ጽና›› ብላው ተሰወረችው።
አባታችን አቡነ ተክለ ሐዋርያትም ምኞታቸው ስለ ፈጣሪያቸው ብለው በሥጋ መከራ መቀበል ነበር፡፡ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ባለቤት የገላውድዮስ እናት ከለላ የምትባል አባታችንን ‹‹ስለ ክርስቶስ አስተምረኝ ስለ ኃጢአቴም ምከረኝ›› ብላ መልዕክት ላከችባቸው፡፡ እሳቸውም መጥተው የሚገባትን ነገር ሁሉ አስተምረው ንስሐም ሰጥተው አረጋጓት፡፡ ልጇን ገላውድዮስንም የመጻሕፍትንም ምስጢር አስተማሩት፡፡
በመጨረሻም ወደ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቤት ገቡ፡፡ ንጉሡም ሥራቸውን ሁሉ ጠይቆ ማረፊያ ሰጣቸው፡፡ በዚያም ሦስት ወር ተቀመጡ፡፡ የመስቀል ክብረ በዓል ቀን የንጉሡ ወታደሮች በፈረስ ግልቢያ ሲጫወቱ፣ በድንጋይና በእንጨት፣ በአጥንት እየተመታቱ፣ ብዙዎቹም ሲሞቱ አቡነ ተክለ ሐዋርያት ተመለከቱ፡፡ ሁኔታውንም የአረመኔ ሥራ ነው ብለው ተቃወሙ፡፡
አቡነ ተክለ ሐዋርያትም አንድ ብርቱ ጉይ አለኝ ብለው ወደ ንጉሡ ገቡ፡፡ ንጉሡንም ሳይፈሩ ስለተደረገው ግፍ፣ በከንቱ ስለሚጠፋው ሕይወትም ተናገሯቸው፡፡ ንጉሡም እንዴት ደፍረው ተናገሩኝ፣አሻፈረኝ ብሎ ያለጥፋታቸው አቡነ ተክለ ሐዋርያትን ደማቸው በአፍና በአፍንጫቸው እስኪፈስ አስደበደባቸው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በብርቱ ወታደሮች ዳግም አስደብድቦ አስገረፋቸው፤በእስር ቤትም አኖሯቸው፡፡ በእስር ቤትም ስምንት ወር በመከራ ተቀመጡ፡፡
አባታችን አቡነ ተክለ ሐዋርያትም በዚህ ጽኑ መከራ እስር ቤት ውስጥ እያሉ እመቤታችን ተገልጻላቸው ‹‹እነሆ የልጄን ትዕዛዝ ፈጸምህ የተመኘኸውን አገኘህ ሌላ የትዕግስት በር ይቀርኃል›› ብላ ተሰወረቻቸው፡፡ አባታችንም በመማረር "እመቤቴ ሰማዕትነትን ስጭኝ ያልኩሽ በክርስቲያናዊ እጅ ነውን" እንዳሉ ገድላቸው ይናገራል፡፡ /ገድለ አቡነ ተክለ ሐዋርያት ገጽ 74-76 ይመልከቱ/
ወዳጄ ፈተናና መከራን በራስህ ሰው፣ በቤተሰብህ፣ የቅርቤ በምትላቸው ሰዎች ሊመጣብህ ይችላል፡፡ ምናልባትም በእነዛ ሰዎች ግፍን መቀበልህ ደም አልባ ሰማዕት ሊያሰኝህ ይችላል፡፡ አየህ አቡነ ተክለ ሐዋርያት ስመ ጥር ጻድቅ ናቸው፡፡ አፄ ዘርዓ ያዕቆብም የእመቤታችን ልዩ ወዳጅ ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ስትመለከት አንዱ ለአንዱ መከራ አንዱ ለአንዱ ክብር ነበሩ፡፡
አቡነ ተክለ ሐዋርያት ሰማዕትነትን የሥጋ መከራን ከአረመኔዎች ከአሕዛቦች እቀበላለው ብለው ቢያስቡም ክርስቲያን ከሆነ፣ለዛውም የእግዚአብሔር ወዳጅ ከሆነ ሰው ከአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ተቀብለዋል፡፡
መከራና ፈተና ከማንምና በየትም ይምጣ ዋናው ታግሶ ማለፍና ክብሩን መቀበል ነው፡፡ ስለዚህ እንዴት በቤተሰቤ? በዙሪያዬ ባሉ የኔ ባልኳቸው ሰዎች ግፍ ይደርስብኛል? እንዴት መከራ እቀበላለሁ? እንዴት መተት ይመተትብኛል? እንዴት ይመትቱብኛል? አትበል፡፡
በተለይ መርሳት የሌለብህ ሰይጣንም አንተን ለመፈተን ከአንተ ሰው የበለጠ የሚቀለው የለም፡፡ ሰይጣን አንተ ላይ የመከራ ድንጋይ ለመጫን ተሸካሚ ከሌላ ቦታ የማታውቀውን ሰው አያመጣም፡፡ የሰይጣን ፈተና እሾህን በእሾህ ነው፡፡ ይልቁንም ሰይጣን አንተን በፈተና ለማንገላታት፣ በመከራ አፈር ከድሜ ለማብላት ያንተ ሰው ይቀለዋል፡፡
በአቡነ ተክለ ሐዋርያትም የሆነው ይኸው ነው፡፡ አንተም ቤተሰብህ ሊበድልህ፣ ጓደኛህ መከራ ሊያደርስብህ፣ ያመንከው ሊከዳህ ይችላል፡፡ በራስህ ሰው ገንዘብህን፣ ትዳርህን፣ሥራህን፣ ዕድልህን፣ መልካም አጋጣሚህን ልታጣ ትችላለህ፡፡ አንዳንዴም እነሱ አንተ ላይ አሲረው ካንተ በወሰዱት ነገር ሲለወጡ፣ አንተ ከድጡ ወደ ማጡ ልትሆን ትችላለህ፡፡
ባል ለሚስት ሚስት ለባል የሕይወት አጋር ብቻ ሳትሆኑ መፈተኛም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በቀናተኛ ባል እና ሚስት ፍቅር ይፈተናል፡፡ በተናጋሪ ሚስት ትዕግስትህ ይፈተናል፡፡ በቁጡ ባል ትህትናሽ ሊፈተን ይችላል፡፡ በአኩራፊ ሚስት ተለማማጭነትህ ሊፈተን ይችላል፡፡ በነጭናጫ ባል ከሚስትነትህ ባለፈ እንደ እናት ልትፈተኚ ትችያለሽ ወዘተ… በዚህ ሂደት ነገሮችን ሁሉ በማስተዋል በትዕግስት ማለፍ ትዳርን ከመታደግ፣ዕድሜውን ከማርዘምም ባሻገር መከራን በመቀበላችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ታገኛላችሁ፡፡
ወዳጄ በሕይወትህ የመከራ እንጀራ እንድትበላ፣ በሕይወትህ እንድትጉላላ ያደረጉህን ሰዎች እዘንላቸው፡፡ ሰይጣን አንተን ለመጉዳት እነሱን መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙ፤ የራስህን ሰው ሥጋ ለብሶ፣ እነሱን መስሎ ፊት ለፊት ስለተዋጋህ ጸልይላቸው፡፡
አንዳንዴ መከራውን መሸከም እስኪከብድህ ድረስ ልትሰቃይ ትችላለህ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከአቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር›› በማለት በሰይጣንና በሰው የመጣው መከራ ሐዋርያውን እንዴት እንደከበደው ጽፎልናል፡፡ 2ኛ ቆሮ 1፥8
አንተ መከራ ባደረሱብህ ሰዎች መከራ ተጭኖህ በስቃይ ስትኖር፣ መከራ የሚያደርሱብህ ሰዎች በሥጋ ምቾት ሲኖሩ ስታይ፤ እግዚአብሔር ያለ ፍርድ በዝምታ የተባበረብህ አድርገህ እንዳታስብ፡፡ ለጊዜው አንተ እየተጎዳህ እነርሱ የተሻለውን ሲሆኑ ብታይ በጊዜው ጊዜ የዘሩትን ያጭዳሉ፡፡ ‹‹መከራን የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ›› ተብሏልና፡፡ ኢዮ 4፥1
በአሁን ጊዜ ሰይጣን ለሰው ፈተና ከሆነው ባልተናነሰ መልኩ ሰው ለሰው ፈተና እየሆነ ነው፡፡ ክርስቲያን ነኝ የሚሉት ክርስትናህን እንዳትኖር ሊያደርጉህ ይችላሉ፡፡ ቆራቢ ነኝ የሚሉት በእነሱ የመጣ ፈተና እንዳትቆርብ ሊያደርጉህ ይችላሉ፡፡ ጻድቅ ነኝ የሚሉት ሰዎች በእነሱ የመጣ ፈተና ትንሿ ጽድቅህን ሊያሳጡህ ይችላሉ፡፡
313 views04:05