Get Mystery Box with random crypto!

ስለዚህ ይህ የጌታችን የምጻት ቀን ለኃጥአን እለተ ፍዳ ናት፡፡ ለጻድቃን ደግሞ የደስታቸው ቀን ናት | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ስለዚህ ይህ የጌታችን የምጻት ቀን ለኃጥአን እለተ ፍዳ ናት፡፡ ለጻድቃን ደግሞ የደስታቸው ቀን ናት፡፡ ጌታችንን ተዘጋጅተን ከጠበቅነው በእውነት ይህቺ ቀን በትንሽ የጽድቅ ሥራችን ብዙ ዋጋ የምንቀበልበት፣ በብዙ የጽድቅ ሥራችን ደግሞ እጥፍ ደርብ የሚንቀበልበት ቀን ናት፡፡
ይችህ ቀን ዳግም ምጻት የትንሳኤ ሙታን መቅድም ነው፡፡ ወይም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ ሲመጣ ነው የሞቱት የሚነሱት፡፡

እኛ የሰው ልጅች ከሞትን በኃላ ፈርሰን በስብሰብ የምንቀር አይደለንም፡፡ ይልቁንም አፈር ትብያ ከሆን በኃላ በመጨረሻ እለት ህይወትን አግኝተን እንነሳለን፡፡ ትንሳኤያችንም በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ የክብር ትንሳኤ እና የሐሳር ትንሳኤ ነው፡፡ የክብር ትንሳኤ የምንለው በሠራነው ስራ ከብረን የምንነሳበት፤ ዋጋ የምንቀበልበት ነው፡፡ የሐሳር ትንሳኤ የምንለው ፍዳና መከራ ለመቀበል የምንነሳው ነው፡፡

ግን ዋጋችንን ተቀብለን ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት በመጨረሻ እንደ ይለፍ የሚጠይቀን ነገር አለ፡፡ እሱም በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 25÷34 ጀምሮ ‹‹እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ ዓለም ከተረጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችኑን መንግስቴን ውረሱ›› ለመባል ምግባርን፣ ሰብአዊነትን፣ ርህራሄን፣ የተመለከቱ ጥያቄ እንጠየቀቃለን፡፡
እነሱም ተርቤ አብልታችሁኛልን፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልን እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልን፤ታርዤ አልብሳችሁኛልን፤ታምሜ ጠይቃችሁኛልን፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኃልን›› በማለት ይጠይቀናል፡፡

እኛም ጌታን መቼና የት አግኝንተንህ በማለት ለማምለጥ ብንሞክር በማቴዎስ 25÷45 ባለው ቃል ‹‹ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁም›› በማለት ያሳፍረናል፡፡
ብዙዎች እንደሚመስላቸው የምንጠየቀው በእሱ ማመናችንን ብቻ ሳይሆን በእሱ ስም ምንም ባለማድረጋችን እንጠየቃለን፡፡ ጥያቄውም በእምነት የሆነ ምግባር ነው፡፡

ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በ 2÷26 ላይ ‹‹ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ፤እንዲሁ ደግሞ ከሥራ/ከምግባር/ የተለየ እምነት የሞተ ነው›› ያለው፡፡ ስለዚህ ጌታችን መቼ እንደሚመጣ፤ ዛሬ ይሁን ነገ፤ ቀን ይሁን ሌሊት አናውቅምና በንስሐ ተዘጋጅተን በስጋ ወደሙ ታትመን ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል በ 24÷42 ላይ ‹‹ጌታችሁ በምን ሰዓት እደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› ብሎናል፡፡

ስለዚህ ከተኛንበት ኃጢአት በንስሐ ልንነቃ ይገባል፡፡ ከክፋት መንገድ ርቀን በጽድቅ ጎዳና ለመጓዝ መዘጋጀት አለብን፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቻችን የክርስቶስ መምጫው ገና ነው በማለት በንስሐ መዘጋጀት አልቻልንም፡፡ ግን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሞት ለብዙዎች ክፉ ምጻት በመሆን ህይወትን እየቀጠፈ ነው፡፡ ላወቀበት ሞት ምጻት ነው፡፡ በድንገት ባልታሰበ ሰዓት ሞት የስንቱን ቤት እያንኳኳ ነው፡፡

ሰው ንስሐ ገብቶ ተዘጋጅቶ ለመኖር የግድ የክርሰቶስን እለተ ምጻት በማሰብ ብቻ ሳይሆን ድንገተኛው፣ ቀጠሮ አልባው፣ የንስሐ እድል የማይሰጠውን፣ ሞት እንደ እለተ ምጻት፣ በማሰብ መዘጋጀት አለብን፡፡
ምክንያቱም ስለዛች አስጨናቂ ሰዓት ማለትም ኃጥአን ጨለማን የሚጎናጸፉባት፤ጻድቃን ብርሃን ስለሚለብሱባት ቀን ከእግዚአብሔር በቀር በሰማይ ያሉ መላእክቶች፤ በምድር ያሉ የሰው ልጆች አያውቁም፡፡

ስለ ቀኒቱም ቅዱስ ጴጥሮስ በ2ኛ ምልእክቱ በምዕ 3÷10 ላይ ‹‹የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፡፡ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፣ የሰማይ ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፣ምድርም በእርሷዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል›› በማለት ተናግሯል፡፡

ወገኖቼ የጌታ ቀኑ መድረሱን የተፈጸሙት ምልክቶች ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ዓለም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታዋ እየተለዋወጠ ለመጥፋት እጠሮጠች ነው፡፡ እኛም የሰው ልጆች መንገዳችን ከእግዚአብሔር ስለራቀ ፈተናችን መከራችን በዝቷል፡፡
በርዕሳችን እንዳነሳነው ጌታችን ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሎናል ስለዚህ እንዴት ነው የምዘጋጀው?

በመንፈሳዊ ህይወት ዝግጅት የምንለው፤ ለነፍስ ማሰብ ነው፡፡ ዝግጅታችንም ስለ እውነት ቀላል ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት የሰራነውን ኃጢአት በአንዲት እለት በንሰሐ ማራገፍ ነው፡፡ የትኛውንም በደል እና ኃጢአት ብንሰራ ኃጢአታችን እግዚአብሔር ከሰጠን ከንስሐ በላይ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔርም በንስሐ ይቅር የማይለን አንዳችም ኃጢአት የለም፡፡ እስኪ እኛ ለንስሐ እንዘጋጅ፤ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን የቸርነቱን፣ የፍቅሩን ሥራ እናያለን፡፡

መዘጋጀት ማለት፦ ንስሐ መግባት የበደሉትን መካስ፣ የቀሙትን መመለስ፣ የተጣሉትን መታረቅ፤ቂም የቋጠሩበትን ልብ በይቅርታ መፍታት፤ በጾም በጸሎት ተግተን በመጨረሻም ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ነው፡፡ ይህን ካደረግን የክርስቶስን ሰማያዊ መንግስት ለመውረስ ዝግጁ ነን ማለት ነው፡፡

የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባህሪይ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለሁሉም ነገር እርሱ ይርዳን፡፡ ፍጻሜያችንን ያሳምርልን፡፡ ጌታችን ሊፈርድብን ሳይሆን ሊፈርድልን፤ ሊኮንናን ሳይሆን ሊያጸድቀን፤ ሰማያዊ የክብር ዋጋችንን ሊሰጠን ከፈለግን፤ በንስሐ ተዘጋጅተን እንጠብቀው፡፡

‹‹እንግዲህ እንዴት እንደተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ ጠብቀውም ንስሐ ግባ፡፡ እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸው ሰዓት እንደምመጣ አታውቅም›› በማለት አመጣጡ ስውርና ድንገት መሆኑን በራዕ 16 ÷15 ላይ ነግሮናል፡፡

‹‹ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰአት ይመጣልና››

‹‹አዎ በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና፡፡
ራዕ 22÷20

መጋቢት 10-7-15 ዓ.ም

ካሊፎርኒያ አሜሪካ