2023-05-26 15:19:02
እለት እለት ከሚያደቡብህ፣ ውድቀትህን አጥብቀው ከሚሹ፣ ኪሳራህን ከሚጠባበቁ፣ በወጣህ በገባህ ቁጥር ጥፋትህን ከሚቆጥሩ፣ እንዲሁ በባዶ ቀልባቸው ከማይወድህ፣ ያለምክንያት ሊርቁህ ከሚፈልጉ ሰዎች ምን ህብረት አለህ?
የምትፈልገውን እየሰጡህ ነውን? ወደምትፈልገው ስፍራ እየመሩህ ነውን? አንዳች ከእነርሱ ያተረፍከው፣ ለህልምህ እውንነት ያበረከቱት አስተዋፅዖ ምንድነው?
የምትበርበትን ከፍታ ለመጨመር ግዴታ የያዝከውን ሸክም መጣል ይኖርብሃል፤ ከሸክሞችህ ዋንኞቹ ደግሞ በሃሳብ፣ በምኞት፣ በተግባር የሚጠሉህ ሰዎች ናቸው። የሚጠየፉህን፣ ወደኋላ የሚጎትቱህን፣ ክፉ የሚመኙልህን ሰዎች ተሸክመህ ለስኬት መጓዝ የምትችል ይመስልሃል? ምንያክል ርቀት የምትሔድ ይመስልሃል? ከመጥፎ ልማዶችህ መለየት እንዳለብህ ሁሉ የሚጠሉህን ሰዎች የመለየት ግዴታ አለብህ።
አዎ! ሩቅ ለመሔድ ሸክምህን ቀንስ፤ የሚጠሉህን ችላ በል፤ ከህይወትህ ዞር አድርጋቸው፤ አስወግዳቸው። መልካም የማያስቡልህን አርቅ፤ በብርታት ቦታ እንቅፋት የሚሆኑብህን ሰዎች ከዙሪያህ አስወግድ።
'ጠላትህን ውደድ፣ የሚረግምህንም መርቅ' የሚለውን የአምላክ ቃል ለመፈፀም መልካም እያደረክላቸው፣ እያሰብክላቸው፣ በፍቅርህ እየማረካቸው መቆየት ትችላለህ፤ ነገር ግን በእነርሱ አሰናካይ ሃሳብ፣ በእነርሱ የምቀኝነት ደባ፣ በእነርሱ ቅስም ሰባሪ ንግግር የመጎዳትና የመሰበር ግዴታ የለብህም።
ክፋት አስበህ፣ ተናደህባቸው ወይም አዝነህባቸው አይደለም። እራስህን ለማዳን፣ ጠንካራ ጎንህን ለማጎልበት፣ በብርታት ወደፊት ለመጓዝ፣ ፍጥነትህን ለመጨመር፣ እራስህን ነፃ ለማውጣት ያለህ ብቸኛ አማራጭ እርሱ ስለሆነ ነው።
አዎ! እስከ መቼ ከህይወት ሸክምህ ቅንጣት ከማይቀንሱልህና ከማይካፈሉህ ሰዎች ጋር ትደክማለህ?
እስከ መቼ ውድቀትህን አጥብቀው ከሚመኙ ሰዎች ጋር ትቀጥላለህ?
እስከመቼ ከመንገድህ ከሚያስቀሩህ፣ ሃሳብህን ከሚቃረኑ፣ እቅድህን ከሚያምታቱ፣ ህልምህን ከሚያጨናግፉ ሰዎች ጋር ትጓዛለህ?
የሚደግፉህ ከሆነ ይደግፉሃል፤ የሚያግዙህ ከሆነ ያግዙሃል፤ የሚረዱህ ከሆነ ይረዱሃል ካልሆነ ግን ውድ ጊዜህን እያባከኑብህ፣ አቅምህን እያሳነሱብህ፣ ተነሳሽነትህን እየቀበሩት፣ መነቃቃትህን ውሃ እየደፉበት ልትመርጣቸውና አብረሃቸው ልትሰራ አትችልም።
እራስህን ለማዳን አትችልም ለሚሉህ መልስ መፈለግ አይጠበቅብህም፤ አሉታዊ ንግግርን የሚያቀርቡልህን መጥላት አይኖርብህም። እራስህ ላይ ማተኮር፣ ከእነርሱ ዞር ማለት፤ ፊትህን ማዞር፣ ቀስበቀስ ከህይወትህ ማስወጣት፤ በምትኩ የልብ ወዳጆችህንና ደጋፊዎችህን ማስገባት እጅግ በጣም በቂ ነው።
@ ምክረ-አዕምሮ/MentalCounsel
5.4K viewsLighthouse- Academy of Success, 12:19