2023-04-22 15:30:51
የሰው ልጅ ሕይወቱን በእንዴት ያለ መላ እንደሚመራ ሁሉንም የሚያግባባ ወጥ የሆነ የተቀመጠ የኑሮ-ዘዴ የለም፡፡ ሰው ፍላጎቱ፣ ማንነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ዝንባሌው፣ ፍልስፍናው ለየቅል በመሆኑ የአኗኗር ዘይቤውም አልተገናኝቶም እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሰውን በዚህ መንገድ ሕይወትህን ብትመራው ወይም ኑሮህን ብትገፋው ደስተኛና ስኬታማ ትሆናለህ ተብሎ መላ አይታዘዝለትም ወይም prescription አይጻፍለትም፡፡ እሱ የወደደውን፣ ያመነበትን፣ የተቀበለውን፣ የተመቸውንና የቀናውን መንገድ ይይዛል ወይም Subscribe ያደርጋል እንጂ፡፡
ብዙ ሰው የራሱን የሕይወት ፍልስፍና ሌላው ላይ ለመጫን ሲጣደፍ ይታያል፡፡ ሌላው በራሱ የሕይወት መንገድ ተመላልሶ የደረሰበት የአኗኗር ልምድ ሌላ ሰው ላይ ላይገጥም ይችላል፡፡ ሃሳብ ጫሪ ወይም እንደማንቂያ ደውል፤ እንደማበረታቻ ወይም እንደመቀስቀሻ መነሻ ሃሳብ ሆኖ ሊያገለግል ይችል ይሆን እንጂ የመጨረሻው ለሰው ልጅ ሁሉ የሚያዋጣ ምርጡ የሕይወት መንገድ ነው ተብሎ ግን አይወሰድም፡፡ “ምርጥ!” በራሱ አንጻራዊ ነውና!
ይሄንን ሃሳብ በሚመለከት የተለያዩ ምሁራንና ፈላስፋዎች የራሳቸውን ሃሳብ አጋርተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል ፈላስፋ፣ የስነልቦና ሊቅ፣ ፀሐፊና የጥበብ ሰው የነበረው ካርል ጁንግ ይገኝበታል፡፡ ይህ ሰው እንዴት መኖር እንዳለብን ለተከታዮቹ በፃፋቸው የግል ደብዳቤዎች የራሱን ምክረ-ሃሳብ አስቀምጧል፡፡ ይህ ታላቅ ሰው ‹‹How to live and the origin of “Do the next right thing”›› በሚባለው አስተሳሰቡ ይታወቃል፡፡ ካርል ጁንግ አድናቂዎቹና ተከታዮቹ ከሆኑ የተለያዩ ሰዎች ስለህይወትና ‹‹እንዴት ስለመኖር›› ለሚነሱለት ጥያቄዎች በደብዳቤ አማካኝነት ምክረ ሃሳቡን ለጠያቂዎቹ ይሰድላቸው ነበር፡፡ እነዚህም ደብዳቤዎቹ ተመርጠውና ተሰብስበው (Selected Letters of C.G. Jung, 1909-1961) በሚል ርእስ በመፅሐፍ ታትመውለታል፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አንዲት የካርል ጁንግ ተከታይ የሆነች ሴት አንድ የሕይወት ጥያቄ አንስታለት ነበር፡፡ ጥያቄዋም ‹‹እንዴት ልኑር?›› የሚል ነበር፡፡
ካርል ጁንግ ሲመልስ፡-
‹‹ጥያቄሽ ሊመለስ የማይችል ነው፡፡ ምክንያቱም አንቺ ማወቅ የፈለግሽው አንድ ሰው እንዴት መኖር አለበት የሚለውን ነው፡፡ ይሄን ደግሞ የሚያውቀው ራሱ ጠያቂው ነው፡፡ ማንም የሚኖረው እንደሚችለው ነውና (One lives as one can)፡፡ አንድ ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት ምንም ዓይነት የተቀመጠ ወይም የተጻፈ መንገድ የለም (There is no single, definite way for the individual which is prescribed for him or would be the proper one)፡፡ አማኝ ከሆንሽ ወደ ቤተ-እምነትሽ መሄድ ትችያለሽ፡፡ ምናልባት እነሱ እንዴት መኖር እንዳለብሽ ሊሰብኩሽ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የራስሽን የአኗኗር ዘይቤ መፍጠር ከፈልግሽ ቀድመሽ ያላወቅሽው ወይም ከማንም ያልተሰጠሸ የራስሽን የሕይወት መንገድ መስራት ይጠበቅብሻል፡፡ ይሄ በእያንዳንዱ የሕይወት እርምጃሽ የሚጀመር ነው፡፡
ሁሌም የሚቀጥለው የሕይወት ተግባርሽ ትክክለኛ ነገርን መከወን ከሆነ የራስሽን የህይወት መንገድ ወይም እንዴት የመኖር ጥበብን በውስጠ-ሕሊናሽ የመፃፍ ብቃትን ታዳብሪያለሽ፡፡ በሌሎች ተደጋፊ ሳይሆን ራሷን በራሷ ሃሳብ ችላ የምትንቀሳቀስ የራሷ አዋቂ ትሆኛለሽ፡፡ ወደፊት እንዴት መኖር እንዳለብሽ ባታውቂም በአሁኑና በሚቀጥለው ሕይወትሽ አስፈላጊውን በማስቀደምና ትክክለኛውን በመከወን ኑሮሽን በደስታና በስኬት ልትሞይው ትችያለሽ፡፡›› ... ሲል መክሯታል፡፡
ጉዳዩን ወደባለቤቱ የሚመልስ ታላቅ ምክር ነው! የሕይወት ቁልፉም፣ የጥያቄው መልሱም ያለው እያንዳንዳችን ጋር ነው፡፡ የሌሎች ሰዎች የሕይወት ቁልፍ የአንተን ወይም የአንቺን የሕይወት በር አይከፍትምና፡፡ በሌላ ሰው መንገድ የሚመላለስ ከግቡ አይደርስም፡፡ ራሱን መምራት የሚችል ሕሊና መፍጠር ያልቻለ በመጣው ወጀብ ይወሰዳል፡፡ ማንም ሲገፋው ይወድቃል፡፡ ስኬት እውን የሚሆነው በራስ መንገድ ነው፡፡ ደስታ የሚገኘው ከራስ ነው፡፡ ያለፈውን ውድቀት መድገም ሳይሆን የሚቀጥለውን አዲስ ሕይወት በማሳመር ነው ሕይወትን በደስታ ማዝለቅ የሚቻለው፡፡ በድግግሞሽ ከመደንዘዝ አካሄድን መለወጥ ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ ከድንግዝግዙ አስተሳሰብ በመውጣት ራስን ማብራት የሚቻለው የሚቀጥለውን ተግባራችንን በማስተካከል ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ.... ከቆረጥክ የማትወጣው ፈተና የለም፡፡ ፀፀትህንና ጭንቀትህን የምታራግፈው፣ ያለፈው ውድቀትህን ድል የምትነሳው ቀጣይ ስራህን አስፈላጊና ልክ ስታደርገው ነው፡፡ ልክነትህን በራስህ መንገድ ስራው፡፡ በሌሎች መንገድ አትወዛገብ! የራስህን የጠራ መንገድ ፍጠር! በራስህ እጅ የሕይወት ቁልፍህን ቅረፅ! ለምን ወደቅኩ አትበል፤ ለምን ተሳሳትኩ ብለህ ወደኋላ አትመለስ፡፡ ባትወደውም፣ ባላሰብከው አጋጣሚ ወይም ጥሩ መስሎህ የማይፈለግ ቦታ ብትገኝም እውነቱን ተቀበለው! ‹‹ሰው ራሱን በራሱ ካላፀደቀ ምቾት አይኖረውም! (A man cannot be comfortable without his own approval)›› እንዲል ማርክ ትዌይን አንተነትህን እስከነምናምንህ ካልተቀበልክ መረጋጋትና የአዕምሮ ሰላም አይኖርህም፡፡ ጥፋትህን ተማርበት! ውድቀትህን ተለወጥበት! የስኬትህ መወጣጫ አድርገው! የሆነው አንዴ ሆኗልና ሕይወትህን በአዲስ መንገድ ቀጥል፡፡ ዋናው የህይወት ጉዳይ ያለው የሚቀጥለው ላይ ነው፡፡ የሆነውን ነገር መመለስ አይቻልም፤ ቀጣይ የሚሆነውን ነገር ግን መቀየር ትችላለህ፡፡ ወደፊት ምን እንደሚገጥምህ ባታውቅም ስራህ ግን ሁሌ ልክና አስፈላጊ ይሁን፡፡ ልክነትህ ያድንሃልና!
ቀጣይ ተግባርህን በመልካም ጀምር! ሕይወት ይቀጥላልና!
በልክነት ወደፊት!
ፀሃፊው:- እሸቱ ብሩ ይትባረክ
1.7K viewsLighthouse- Academy of Success, 12:30