Get Mystery Box with random crypto!

Fuad Muna (Fuya)

የቴሌግራም ቻናል አርማ fuadmu — Fuad Muna (Fuya) F
የቴሌግራም ቻናል አርማ fuadmu — Fuad Muna (Fuya)
የሰርጥ አድራሻ: @fuadmu
ምድቦች: ስነ-ጽሁፍ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 16.20K
የሰርጥ መግለጫ

የኛ እዉነታ የሌሎችን ስጋ ለብሶ ሲቀርብ!
በፅሁፍ ያስነበብኳችሁን በድምፄ ስትሰሙት!
ለአስተያየትዎ
@fuadmubot
ዩቲዩብ ቻናል http://Www.YouTube.com/c/FuadMuna
የፌስቡክ አካውንቴን ለማግኘት www.facebook.com/fuadmuna14
ለፒዲኤፍ ብሎግ www.fuadmuna.wordpress.com

Ratings & Reviews

3.33

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

1

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 30

2022-09-12 17:23:22 ቀን 7 ሳላይሽ ....
(ፉአድ ሙና)
.
አልሀምዱሊላህ⁰
ተቃጠል ጠላት፣ ወዳጅ ተደሳ፣
የጆሮዬ ራ‘ብ
የድምጿ ማዕቀብ፣ ድንገት ተነሳ!!
አልሀምዱሊላህ!!!

ሰማሁት ድምጿን ....

ሰማሁኝ ድምጿን
ወረረኝ ደስታ፣ ቆመ ፀጉሬ፣
ፈገግታ እሺ አለኝ
ቦግ ፈካ አለ፣ ሁሉ ነገሬ።

አወይ ቅላፄ ....

አወይ ቅላፄ
ሲያለሰልሰው፣ ታምቡሬን ስሞ፣
አወይ አሳሳቅ
ነፍስ ሲሰጠኝ፣ ልቤን አክሞ።
ደስ ሲል ድምጿ!!!

ድምፅሽ ሲነካኝ ....

ለአንዴ ለአፍታ
ጀነት መሰለ፣ ቦታው ዙሪያዬ፣
ሻዩ ተደፍቶ
ከውሰር¹ ተሞላ፣ በብርጭቆዬ።
ሀያል ነው ድምፅሽ!!

መልዓክት ራሱ
ተክቢር² እያሉ፣ ዞሩኝ በደስታ፣
አስተናጋጇ
ለምጧ ጠፋላት፣ ድምፅሽን ሰምታ።

የክረምቱ አየር
ይሞቀኝ ጀመር፣ በድምፅሽ ርዶ፣
ደስታ ወረረኝ
አንቺን በማድመጥ፣ ሸሸሁ ከመርዶ።
ሲጣፍጥ ድምፅሽ!

እያሸተትኩኝ
በወሬሽ ለዛ፣ ሚስክ³ ተነፍቶ፣
ይሀ ምቀኛ
አዛን አወጣ፣ ከመስጂድ ገብቶ።

ስልኩ ተዘጋ ....

እንደዘጋሽው
ናፍቆትሽ ባሰ፣ በእጥፍ በእጥፉ፣
ምንድን ፍርጃ ነው
ተቀምሶ ‘ማይበርድ፣ የፍቅርሽ ግፉ።

ባሰብኝ ናፍቆት ....

አይኔ ከሰሰኝ፣
ይድረሰኝ አለ፣ የጆሮዬ እጣ፣
ለአንድ‘ዜ ይይሽ
ባይበርድለትም፣ ፍትህ አይጣ።

ሲራ⁴ ስትቀሪ፣ እንደተማርሽው፣
ትንሽም ቢሆን፣ በ‘ኔ እንዳየሽው፣
ራቁት ልቤን፣ ፍቅር አልብሽው፣
ጅብሪል⁵ አይመጣም፣ አንቺ ካልሆንሽው።

ናፍቆት ክፋቱ
በማግኘት አይበርድ፣ አይተው በማጣት፣
መብሰክሰክ ፍርጃ
የምኞት ብፌ፣ የሚጥም ቅጣት።
ያማል ግን!

ናፍቀሽኛል በእጥፍ!

20 ቀን እኮ ብዙ ነው!!

ያ ረብ ኢኒ ፈቂር!!
***
አገባባዊ ፍቺ
¹ አልሀምዱሊላህ:– ለአላህ ምስጋና ይገባው
² ከውሰር: – ለነብዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) በጀነት የተሰጠ ምንጭ
³ ተክቢር: – የአላህ ታላቅነት መግለጫ
⁴ ሚስክ: – የጀነት ሽቶ
⁵ ሲራ:– የነብዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) ታሪክ
⁶ ጅብሪል:– መልዓክ
.
@Fuadmu
@Fuadmu
@Fuadmubot
3.9K views14:23
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-11 15:50:27 ቀን 6 ሳላወራሽ ....
(ፉአድ ሙና)
.
አበባየሆሽ
ለምለም፣
አድርሰናል እንደመባል
‘ሚቀፍ የለም።

ሆ ብዬ መጣሁ
ሆ ብዬ ....
ፍቅሬ ካለሽ ብዬ፣
ሆ ብዬ መጣሁ
ሆ ብዬ!!

በእንቁጣጣሹ
ጭፈራው ሲደምቅ፣ ሰማይ ሳትጠራ፣
ሆ ብሎ መምጣት
አሰብኩኝና፣ ስስ ልቤ ፈራ።

ፈሪ ነኝ እኮ ....

ፈሪ ነኝ በጣም
ያንቺ ፍቅር ነው፣ ስሱ ብልቴ፣
ላግባሽ ለማለት
እንደምን ልድፈር፣ አልቆመም ቤቴ።

በእኩለ ለሊት
ገና ሳልጨርስ፣ እንጨት ሰበራ፣
አይመጥንሽም
ነይ ግቢ መባል፣ ቤት ሳይሰራ።

ፍቅርሽ ተራራው
እያሳነሰው፣ በእጄ ያለን ሁሉ፣
ብትገዝፊብኝ ....
ወላዋይ ብለሽ፣ አማሽኝ አሉ።

ቆራጥ ነበርኩኝ ....

ፍቅርሽ ነው እንጂ
ያስደፋኝ አንገት፣ ነበርኩኝ ዋና፣
እጄን የማልሰጥ
የማልሰፈር፣ በቆንጆ ቁና።

ግን ተበለጥኩኝ ....

አልገባሁሽም
ታየ እንደሽንፈት፣ ስስት ፍቅሬ፣
አነስኩሽና
ሌላ ሰው መርጠሽ፣ ቃል ሰጠሽ ማሬ።
ቀልዴን ነው በይኝ!!

አበባየሆሽ
ለምለም፣
አድርሰናል እንደመባል፣
‘ሚቀፍ የለም።

ቀልድሽን ነው
አውቅሻለሁ፣  አትጨክኚም በመውደዴ፣
ከቶ አልችልም
አንቺን ማጣት፣ ለአፍታ ለአንዴ።
ቀልድሽን ነው!!

አሁን አሁን
አይኔ ሲራብ፣ ፊትሽን ለምዶ፣
ፅልመት ሞላኝ
ድምፅሽ ሲጎ‘ል፣ ከጆሮዬ ተዋህዶ።

አዲስ አመት
ሳላወራሽ ሳንተያይ፣ አበሰሩ፣
ያላንቺ ሳቅ
መድመቅ ሽተው፣ ችቦ አበሩ።
ኪሳራ!!

እኔ ጋር ግን
የፅልመት ጎርፍ፣ ይታየኛል ተጥለቅልቆ፣
ያላንቺ ድምፅ
ያለሳቅሽ፣ ምሎልኛል ላይሄድ ለቅቆ።
ልሰምጥ ነው!!

ሲያዩኝ ብመስል፣ ያካበበኝ ድሎት ሞልቶ፣
ትንኝ ታክል፣ ልቤ አያውቅም ደስታ አይቶ፣
ራሪልኝ፣ ውስጤ አይንደድ አንቺን አጥቶ።

ናፍቀሽኛል ....
ደሙን ትቶ፣ ልቤ እንባ እስኪዘራ፣
አይኖቼ ላይ
በስምሽ ቅርፅ፣ የደም መስመር እስኪሰራ።
ንፍቅፍቅ ብለሽኛል።

አበባየሆሽ
ለምለም፣
አድርሰናል እንደመባል፣
‘ሚቀፍ የለም።

ናፍቀሽኛል!!!

20 ቀን እኮ ብዙ ነው!!!

ያ ረብ ኢኒ ፈቂር!!!
.
@Fuadmu
@Fuadmu
@Fuadmubot
676 viewsedited  12:50
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-10 16:16:48 ቀን 5 ሳላወራሽ ....
(ፉአድ ሙና)
.
ክረምቱ ሊሄድ
አንድ ቀን ቀረው፣ ፀደይ ልትፈካ፣
ከንቱ ልፋቷ
ላይወግግ ጠፍተሽ፣ አመት ቢተካ።
ልፊ ሲላት ነው!!

ለምንድን ጨከንሽ ....

ለምንድን ጨከንሽ
እንዴት አስቻለሽ፣ ስሰቃይ ውዴ፣
ቁርጡን ንገሪኝ
ምን ተፈጠረ፣ ማሊ ፊ በዴ¹?

አገባሽ እንዴ?

አገባሽ እንዴ
እንደፈራሁት፣ አምናም ካቻምና፣
ወሰዱብኝ ወይ
የልቤን አስኳል፣ ሊያደርጉኝ ወና?!

እሺ አልሻቸው?

እሺ አልሽ ወይ
ሰው እንደማልሆን፣ ስታውቂው ከቶ፣
ላይቻልልኝ
ህይወትን ማለም፣ ፍቅርሽን አጥቶ።
እሺ አልሽ እንዴ?

ፈራሁ አለሜ ....

ፈራሁኝ በጣም
ሞት ይመስለኛል፣ ገዝፎ ስጋቴ፣
ሌላ አግብተሽ
መኖር አልሻም፣ ያልቃል ህይወቴ።

ኧረ እንዲያ አይሆንም ....

እንዲያማ አይሆንም
እኔ ነኝ እንጂ፣ ክፉ ጠርጣሪ፣
አትፈርጂብኝም
እኔ እያለቀስኩ፣ ስቀሽ ልትኖሪ።

ሰው ደግሞ ከፋ ....

ሰዉ ጨከነ
ይዝናና ይዟል፣ ላንቺ ስደማ፣
ላፋልግ አይልም
ንቆ ያልፈኛል፣ ሰምቶ እንዳልሰማ።
ጨክኗል ሰዉ!

አመት ሊቀየር
ሲመታ ድቤ፣ ሲገረፍ ጅራፍ፣
አይኔ ይዋልላል
ቻው ካልኩሽ ቦታ፣ ከካፌው በራፍ።

ማሊ ፊ በዴ?

ማሊ ፊ በዴ
የአይኔ ምግብ፣ ደስታዬን ማያ፣
ሲፊን ጅራ ናንጄይ²
ደማብሽ ልቤ፣ ጃለሌ ቲያ³።

ጨረቃዬ ....

ሲርቀኝ ወዳጅ፣ ስምሽን አብዝቼ፣
ትቅርብህ ሲሉኝ፣ ስላቸው ሞቼ!!
ራበኝ መፍካት፣ ሳቅሽን አይቼ!!

ሰው ይርባል?

‘ርበሽኛል
ጠኔ እስኪሆን፣ ሚያንሰፈስፍ?
ካልቆረጥሽው
ሚስኪን ነብሴን፣ እስኪያሳልፍ!!
ናፍቀሽኛል!!!

ያ ጃለሌ ቲያ
ስሞትልሽ ነያ!

ናፍቀሽኛል ብዙዙዙዙ!!!!!

20 ቀን እኮ ብዙ ነው።

ያ ረብ ኢኒ ፈቂር!

***
አገባባዊ ፍቺ
¹ ማሊ ፊ በዴ: – ለምንድን ጠፋሽ?
² ሲፊን ጅራ ናንጄይ: – አለሁልህ በይኝ
³ ጃለሌ ቲያ:– የኔ ፍቅር
.
@Fuadmu
@Fuadmu
@Fuadmubot
2.0K views13:16
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-09 15:02:45 Fuad Muna (Fuya) pinned «ቀን 4 ሳላወራሽ .... (ፉአድ ሙና) . ጁሙዓ ሆነ .... ጁሙዓ ሆነ ሊሰበሰብ ነው፣ የወትሮ ቀሪ፣ ኢድ¹ ኢድ ሊሉ ነው ምስቅ መስሏቸው፣ አንቺ ሳትኖሪ። አንቺ ነሽ ኢዴ .... አንቺ ነሽ ኢዴ የፊትሽ ብርሀን፣ ‘ሚያበስረኝ ደስታ፣ ስትስቂ ነው ኢድ ሆነ ‘ሚባል፣ ‘ሚደምቀው ፌሽታ። የምንድን ኢድ ነው? የምንድን ኢድ ነው? አንቺን ሳላይሽ፣ ሳልሰማሽ ለአንዴ፣ አርካን² አይደል ወይ? ጁሙዓ…»
12:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-09 14:31:55 ቀን 4 ሳላወራሽ ....
(ፉአድ ሙና)
.
ጁሙዓ ሆነ ....

ጁሙዓ ሆነ
ሊሰበሰብ ነው፣ የወትሮ ቀሪ፣
ኢድ¹ ኢድ ሊሉ ነው
ምስቅ መስሏቸው፣ አንቺ ሳትኖሪ።

አንቺ ነሽ ኢዴ ....

አንቺ ነሽ ኢዴ
የፊትሽ ብርሀን፣ ‘ሚያበስረኝ ደስታ፣
ስትስቂ ነው
ኢድ ሆነ ‘ሚባል፣ ‘ሚደምቀው ፌሽታ።

የምንድን ኢድ ነው?

የምንድን ኢድ ነው?
አንቺን ሳላይሽ፣ ሳልሰማሽ ለአንዴ፣
አርካን² አይደል ወይ?
ጁሙዓ ሙባረክ³፣ ማለትሽ ውዴ??
ጎደለ አርካን!!!!

ማይኩ ተመታ ....

ማይኩን ነካኩት
አዛን⁴ ሊሉ ነው፣ ትንሽ ሳያፍሩ፣
ናፍቆትሽ አሞኝ
ኢድ ሆነ ብለው፣ ጀመዓ⁵ ጠሩ።

ምቀኛ ሁላ ....

ምቀኛ ሁላ
ደግሞ አውቀዋለሁ፣ ይኼን ሙዓዚን⁵፣
አንድ ላይ ስንሆን
ያለ ሰዓቱ፣ ገብቶ ሲዓዝን⁶፣
ምቀኛዬ ነው
ስቆ አያውቅም፣ ደስ ያለኝ ለታ፣
ሊበቀለኝ ነው
ህመሜን ሊያብስ፣ ጅል ማይኩን መታ።
አዛን ተባለ!!!

ደግሞ ትዝ አለኝ ....

ትዝ ትዝ አለኝ
ገላን መታጠብ፣ የጁሙዓው ሱና⁷፣
ሻወሩ አስቀናኝ
ስትታጠቢ ፈጦ እንዳያይሽ ፣ ገና ለገና።

አልፈረሰም ወይ? ....

አልተናደም ወይ?
መለመላሽን፣ ልትታጠቢ የቆምሽበቱ፣
ተዓምር አይደል ወይ
ይህንን ውበት፣ ችሎ መፅናቱ።
ታድሎ!!!

ሄድኩ ወደ መስጂድ ....

ሄድኩ ወደ መስጂድ
እንደሚገደል ፍርደኛ እስረኛ፣ እየተጎተትኩ፣
ኹጥባውን⁸ ሰማሁ
ስላንቺ ነበር፣ ክፉኛ አለቀስኩ።

ኢማሙ ያለቅሳል ....

ኢማሙ ያነባል
አልሰማም መሰል፣ እሱም ድምፅሽን፣
ከሚንበሩ ላይ
ሁረል ዓይን⁹ ብሎ፣ ደግሞ ደጋግሞ ይጠራል ስምሽን።

ናፍቆሻል እሱም!!

እኔ እና እኔ  ....

ሲያልቅ ኹጥባው፣ አለቀስንና ዱዓ አደረግን፣
ትምጣልን ብለን፣ በጀመዓው¹⁰ ፊት ተንሰቀሰቅን፣
ራርተህ ላካት፣ የኛም ኢድ ይሁን ብለን ጠየቅን።

ናፍቆትሽ ጨምሯል ....

ከሰላቱ ኋላ
ኢድ የማያውቅ ኢዳም፣ ሲሰለቅጥ ጥብሱን፣
እኔ ያንቺ ከርታታ
በትዝታ ትሪ፣ በላሁኝ ናፍቆትን።

እየናፈቅሽኝ ነው ....

አመመኝ አመመኝ
ናፍቆትሽ አመመኝ፣ በሰይፍ እንደደማ፣
አሽሪኝ አሽሪኝ
ጤነኛ እሆናለሁ፣ ተይ ድምፅሽን ልስማ?!
አሽሪኝ አለሜ!!

ናፍቀሽኛል በጣም!!!

20 ቀን እኮ ብዙ ነው!!

ያ ረብ ኢኒ ፈቂር!!

****
አገባባዊ ፍቺ
¹ ኢድ: – የጁሙዓን ሳምንታዊ በዓልነት ለመግለፅ የገባ፣ ደስታ፣ በዓል
² አርካን:– መሰረት፣ ካልተሟላ ስራን ውድቅ የሚያደርግ
³ ጁሙዓ ሙባረክ: – የተባረከ ጁሙዓ ይሁን የሚል የተለመደ የጁሙዓ መልካም ምኞት መግለጫ
⁴ አዛን: – ወደ መስጂድ የሚደረግ ጥሪ
⁵ ሙዓዚን: – አዛን የማውጣት የስራ ድርሻ ያለው ግለሰብ
⁶ ሲዓዝን: – አዛን ሲል
⁷ ሱና: – ተወዳጅ ልማድ
⁸ ኹጥባውን: – የጁሙዓ መልዕክት
⁹ ሁረል ዓይን: – የጀነት ቆነጃጅት
¹⁰ ጀመዓ:– ህዝብ
.
@Fuadmu
@Fuadmu
@Fuadmubot
2.4K views11:31
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-08 18:27:52 Fuad Muna (Fuya) pinned «ቀን 3 ሳላወራሽ .... (ፉአድ ሙና) . አንቺን የማያውቁ ጊዜው ተለወጠ፣ አሉኝ ዳግም ነጋ፣ ምንም ብርሀን የለ እንደጨለመ ነው፣ እስካሁን እኔ ጋ! አንቺ ነሽ ብርሀኔ ... አንቺ ነሽ ብርሀኔ በፊትሽ ፀዳል ነው፣ ወቅቴን የምቆጥረው፣ አይኔን ስትሞዪ ስትስቂ ስትስቂ፣ ይኸው ነጋ ‘ምለው። ልቤን ይወጋኛል .... ልቤን ይቀስፈኛል ደምኗል አየሩ፣ ጠቋቁሯል ሰማዩ፣ ውስጤ አይረጋጋም ከርታታ አይኖቼ፣…»
15:27
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-08 18:20:39 ቀን 3 ሳላወራሽ ....
(ፉአድ ሙና)
.
አንቺን የማያውቁ
ጊዜው ተለወጠ፣ አሉኝ ዳግም ነጋ፣
ምንም ብርሀን የለ
እንደጨለመ ነው፣ እስካሁን እኔ ጋ!

አንቺ ነሽ ብርሀኔ ...

አንቺ ነሽ ብርሀኔ
በፊትሽ ፀዳል ነው፣ ወቅቴን የምቆጥረው፣
አይኔን ስትሞዪ
ስትስቂ ስትስቂ፣ ይኸው ነጋ ‘ምለው።

ልቤን ይወጋኛል ....

ልቤን ይቀስፈኛል
ደምኗል አየሩ፣ ጠቋቁሯል ሰማዩ፣
ውስጤ አይረጋጋም
ከርታታ አይኖቼ፣ ፊትሽን ካላዩ።

አመመኝ በጠና ....

ከንፈርሽ ያውና
ዚክር¹ አለስልሶት፣ ተቀብቶ ሙራጃ²፣
አንድዜ ብገምጠው
እስከዘላለሙ፣ መራቤንም እንጃ።

ቅሪልኝ³ ህመሜ
ልስማሽ ስትሞጥዪ⁴፣ እንዳይጠፋሽ ሂፍዙ⁵፣
ብጮህም አልፈራም
ሀጢዓት አይባልም፣ ሰው ባንቺ መያዙ!!
ቅሪልኝ ግድየለም!!

ተራብኩሽ አለሜ ....

ተራብኩሽ በፀና፣
ጆሮዬ አኮረፈኝ፣ አለኝ ድምጿን አምጣ፣
አንደበቴ ከዳኝ፣
በወሬዬ መሀል፣ ስምሽን እያወጣ!!
አወይ የኔ ጣጣ!!

ናፍቀሽኛል እኮ ....

ናፍቀሽኛል በጣም
የሀፍረትሽ አስኳል፣ ተስሏል ከፊቴ፣
ያ ረብ እያልኩኝ ነው
ታፋሽ ላይ እንድሞት፣ ቤትሽ ሆኖ ቤቴ።

ተዪ ግን ራሪ ....

ሲሰቃይ ለኖረ ፣ ልቡን ‘ሚሞላ አጥቶ፣
ትናንት ለሌለው፣ የኔ አይነት ማቶ፣
ራሪ አለሜ፣ ጀግና አትባዪም፣ በፍቅርሽ ሰው ሞቶ።

ግን አንቺስ እንዴት ነሽ?

ናፍቄሻለሁኝ?
ትዝ ብዬሻለሁ፣ ትንሽ እንኳን ለአፍታ?
ወይስ ብቅ አላልኩም፣
በአዕምሮሽ መሀል፣ ከቶም ለብልጭታ?
ቲሽ! ምኔ ይናፈቃል?
እኔ አንቺን አይደለሁ!!

ናፍቆት ሲያም!!

አመመኝ መናፈቅ
የወትሮው ታታሪ፣ አቃተኝ መነሳት፣
አንቺን ብቻ ሳስብ፣
የዝሁርን አዛን⁶፣ ደረስኩ እስከመርሳት።
አልፎኛል ጀመዓ⁷
ጣትሽን አውሺኝ፣ ስቲግፋር⁸ ላ‘ርግበት፣
ባንቺ ያረፈደ፣
ባንቺ ጣት ብቻ ነው፣ መቅቡል⁹ ‘ሚሆንለት።
አስነኪኝ ግድየለም!!

ጨረቃዬ ....

ናፍቀሽኛል
ናፍቆት ራሱ፣ እስኪያየኝ ሀዘን ለብሶ፣
እስኪል ድረስ፣
አላየሁም ያንተን ህመም፣ ሌላው ቀምሶ።

ናፍቀሽኛል ውዴ!!!

20 ቀን እኮ ብዙ ነው!!

ያ ረብ ኢኒ ፈቂር!!!

***
አገባባዊ ፍቺ
¹ ዚክር: – አምላክን ማወደስ
² ሙራጃ: – ቁርዓንን በቃል ሽምድዶ መለማመድ
³ ቅሪልኝ: – ቁርዓን አንብቢልኝ
⁴ ስትሞጥዪ: — ቁርዓን በቃል ስትለማመጂ
⁵ ሂፍዙ: – የተሸመደደው ቁርዓን
⁶ የዝሁር አዛን : – በቀን አካፋይ ላይ የሚሰገደው ሰላት ጥሪ
⁷ ጀመዓ: – ለስግደት መሰብሰብ
⁸ ስቲግፋር: – ምህረትን መለመን
⁹ መቅቡል: – ተቀባይነት የሚያገኘው
.
@Fuadmu
@Fuadmu
@Fuadmubot
2.6K views15:20
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-07 14:48:29 Fuad Muna (Fuya) pinned «ቀን 2 ሳላወራሽ ... (ፉአድ ሙና) . ሲያፈቅሩ ስቄያለሁ፣ ባለማወቅ ወኔ፣ ይኸው ፍቅርሽ ቀጣኝ፣ አወይ መጥኔ ለኔ፣ ምናለ ባልሳቅኩኝ? ኧረ እንኳንም ሳቅኩኝ!!! ናፍቆትሽ ጀመረኝ ... ትዝ አሉኝ ጣቶችሽ ውብ ከንፈሮችሽን ‘ምትሸፍኝባቸው፣ እንደው ስለፍቅሬ ሀራም¹ ይሆናል ወይ አንዴ ብነካቸው? ትዝ አሉኝ ጉንጮችሽ ልክ እንደ መንደሪን፣ ግመጡኝ የሚሉ፣ ሳስቅሽ ሳስቅሽ ስትሽኮረመሚ፣ በደም የሚሞሉ፣…»
11:48
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-07 14:46:04 ቀን 2 ሳላወራሽ ...
(ፉአድ ሙና)
.
ሲያፈቅሩ ስቄያለሁ፣ ባለማወቅ ወኔ፣
ይኸው ፍቅርሽ ቀጣኝ፣ አወይ መጥኔ ለኔ፣
ምናለ ባልሳቅኩኝ?
ኧረ እንኳንም ሳቅኩኝ!!!

ናፍቆትሽ ጀመረኝ ...

ትዝ አሉኝ ጣቶችሽ
ውብ ከንፈሮችሽን ‘ምትሸፍኝባቸው፣
እንደው ስለፍቅሬ
ሀራም¹ ይሆናል ወይ አንዴ ብነካቸው?

ትዝ አሉኝ ጉንጮችሽ
ልክ እንደ መንደሪን፣ ግመጡኝ የሚሉ፣
ሳስቅሽ ሳስቅሽ
ስትሽኮረመሚ፣ በደም የሚሞሉ፣

ትዝ አሉኝ ጉንጮችሽ
ምናል ብገምጣቸው፣ ምናል ብነክሳቸው?
ሀራም ይሆናል ወይ?
በቡርቱካን ኒያ²፣ ለሚዳብሳቸው?

ናፈቅሽኝ አለሜ

ተመኘሁ ባቀፍኩሽ፣
ትንፋሽሽ ቢገርፈኝ፣ በተኛሽ በእቅፌ፣
እንጃልኝ እንጃልኝ፣
ያንተ ነኝ ካላልሽኝ አልተኛም አርፌ።

ትዝ አሉኝ አይኖችሽ
መሬት መሬቱ ላይ የሚንከራተቱት፣
በምን ከራማ³ ነው፣
አይኔን ገረፍ አ‘ርገው፣ ልቤን የሚያዩት??
ምንድነሽ አንቺዬ?

ጌታዬ በሰማይ
ለደጋግ ባሮቹ፣ አልቆ ያበጀው፣
እንዳትዋሺኝ ውዴ
ሁረል ዐይን⁴ ምንድነው?
ምድር ተልከሽ ነው?

አንቺን በዱንያ
ጀባ የተባለ እድለኛ ገዳም፣
ሁረል ዐይን ቢሉት
ቅንጣት ታክል ጉጉት ከልቡ አይገባም።
ምን ጉድነሽ በአላህ?

ናፍቀሽኛል በጣም

ከካፌው ተቀምጠን
የቆራረጥሽው ሶፍት ፣ አስቀናኝ በብዙ፣
እንዴት ቢታደል ነው፣
ባንቺ መነካቱ፣ በእጆችሽ መያዙ?
አጅነቢ⁵ ቢሆንስ???

ትዝ አለኝ ስትስቂ

ሲበራ አለሙ፣ ስትሆኚ ጨረቃ፣
ትፈካለች  ምድር፣ በውበትሽ ደምቃ፣
ራሷ ምድር እንኳን፣ ለራሷ አትበቃ።

እየናፈቅሽኝ ነው

ርቦኛል ድምፅሽ፣ የጆሮዬ ሩቃ⁶፣
አንቺን ሳደምጥ ነው
ከግራጫ አለሜ በርግጌ ‘ምነቃ።

ናፍቀሽኛል ውዴ!

ሀያ ቀን እኮ ብዙ ነው!!

ያረብ ኢኒ ፈቂር!!

***
አገባባዊ ፍቺ
¹ ሀራም: – በእስልምና አስተምህሮ የተከለከለ
² ኒያ: – ድርጊተ–አላማ፣ ሀሳብ
³ ከራማ – ከፈጣሪ የተሰጠ ልዩ ፈቃድ
⁴ ሁረል ዐይን – ለጀነት ሰዎች የተዘጋጁ ውብ እንስቶች
⁵ አጅነቢ – ለማግባት የማይከለከል፣ ባዳ
⁶ ሩቃ – መንፈሳዊ ህክምና

@Fuadmu
@Fuadmu
@Fuadmubot
1.1K views11:46
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-09-03 21:29:38 ገባ ገባ በሉ

https://t.me/fuadmu?livestream=5d4649d983c632cda8
904 viewsedited  18:29
ክፈት / አስተያየት ይስጡ