2023-04-11 01:06:49
የረመዷን ወርቃማ 10 ቀናቶች
T.me/ahmedin99
የወራቶች ሁሉ አለቃ የሆነው ረመዷን የመጨረሻ አስር ቀናቶቹ ደግሞ የወሩ ቀናቶች ቁንጮ ናቸው፡፡በነዚህ ቀናቶች ውስጥ የምትገኘዋ ለይለቱልቀድር ደግሞ የቁንጮዎች ቁንጮ ናት፡፡
አስሩን ቀኖች (ሌሊቶች) በሙሉ ለይለተል-ቀድርን በማሰብ በዒባዳ ያሳለፈ ያለምንም ጥርጥር ለይለተል-ቀድርን ያገኛል።
ቡኻሪይና ሙስሊም ከእናታችን ዓኢሻ
እንደዘገቡት ነቢዩ ﷺ"የረመዷን 10 ቀኖች ሲገቡ መቀነታቸውን ያጠብቁ ነበር፣ ለሊቱንም በሙሉ በዒባዳ (በሰላት) ያሳልፉ ነበር፣ ባለቤቶቻቸውንም (ለዒባዳ) ይቀሰቅሱ ነበር" ብለዋል፡፡
ጅምርና መነሻ ላይ ሁሉም እኩል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሮች የሚለኩት ግን በፍጻሜያቸው ነው፡፡ እስከመጨረሻው ታግሶ ስራውን አሳምሮ ያጠናቀቀ ይሸለማል፡፡ መጨረሻ ላይ የተሳነፈና ያበላሸ ግን ሽልማቱን በማጣት ወይም ከዛም በከፋ ነገር ሊቀጣ ይችላል፡፡
የረመዷን የመጨረሻ 10 ቀናት ላይ ይበልጥ ኸይር ስራ ላይ ልንተጋና መጨረሻችን ያማረ እንዲሆን ጥረት ልናደርግ እንጂ ልንዘናጋና ልንሰላች በጭራሽ አይገባንም፡፡
ኢብኑል-ጀውዚይ እንደሚሉት"ፈረስ እንኳ የእሽቅድድም ሜዳ ላይ የመጨረሻው ዙር ላይ ሲደርስ ኀይሉን አሟጦ ተጠቅሞ ሌሎች ፈረሶችን በመቅደም ከግቡ ላይ ቀድሞ ለመድረስ ይጥራል" ፣እነሆ ከፈረስ በላይ እንጂ በታች ልንሆን ፈፅሞ አይገባምና እኛም ወደ ጀነት በሮች በመልካም ስራ ልንሽቀዳደም ይገባናል፡፡
የረመዷን የመጀመሪያ አስርቶች ላይ ከነበረን የተሻለ ንቃትና ትጋት ሊኖረን ይገባል።
ሰራተኛ ስራውን ሲያጠናቅቅ የሚያገኘውን ደመወዝ በማሰብ የስራውን ድካም ተቋቁሞ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርገው ሁሉ እኛም የአላህን ውዴታና ጀነትን በማሰብ ነፍሲያችንን በማሸነፍ መልካም ስራ ላይ ልንበረታ ይገባናል፡፡ ሁኔታዎች ለመልካም ስራ የማያግዙበት ወቅትና ቦታዎች ላይ ሁሉንም ተቋቁሞ ከእኛ የሚጠበቀውን ማድረግና አላህ እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ደረጃው ለዲን ብሎ ወደ ነቢዩﷺ የመሰደድ ያክል ነው፡፡
ኢዕቲካፍ በመግባት ከዓለማዊ ጉዳዮች ርቆ፣ ከዱንያ ግርግርና ወሬዎቿ ተነጥሎ፣ ዒባዳ ታስቦ፣ የተለያዩ የአምልኮ ተግባራትን መፈፀም እዚያው ለመዋልና ለማደር ጠቅሎ መስጊድ መግባት ማለት ነው፡፡ የቻለ አሥርቱን ቀናት ኢዕቲካፍ ማድረግ ይችላል፤ ያልቻለ የተመቸዉን ቀን መርጦ ኢዕቲካፍ ማድረግ ይችላል፡፡ ኢዕቲካፍ ነፍስን ያጠራል፣ ዉስጥን ያፀዳል፡፡ አሥርቱን ቀናት ኢዕቲካፍ ማድረግ የፈለገ ሰው ረመዷን 20 ቀን (ምሽቱ 21) ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት መስጊድ ይገባና ነገ ዒድ ሲባል ከፀሐይ መጥለቅ በኋላ ይወጣል፡፡
"የሰው ልጅ ሆይ:- የተወለድከው ብቻህን ነው፣የምትሞተውም ብቻህን ነው፣ ቀብርም የምትገባው ለብቻህ ነው፣ ለምርመራ አላህ ፊት የምትቆመውም ለብቻህ ነው፣ጀነትም ይሁን ጀሀነም የምትገባው ለብቻህ ነው!" ታዲያ ነገ የምትድንበትን ኸይር ስራ ለብቻህ መስራት እንዴት ይከበድሃል?!?
ዛሬ ዱኒያ ላይ መስፈርቱን ያሟላ መልካም ስራ ከሰራን ነገ ኣኺራ ላይ በጀነት ስናርፍ ድካሙን በሙሉ እንረሳዋለን! ከዛም አልፎ የከፈልነውን ዋጋ እንንቃለን!
በወርቃማ አስርቱ ቀናት፣
1/ ኢዕቲካፍ በመግባት
2/ ቁርኣን
3/ ለራሳችንም ለሌሎችም የተለያዩ ዱዓዎችን በማድረግ በተለይም (አላህ ሆይ አንተ ይቅር ባይ ነህ ይቅር ማለትንም ትወዳለህ ይቅር በለኝ) የሚለውን ዱዓ ማብዛት
4/ ዚክር በማብዛት
5/ ሰደቃ
6/ ለሊቱን ሙሉውን -እስከ ሱሑር- በሰላት ብቻ ማሳለፍ የቻለ ይህን በማድረግ ይህን ያልቻለ ደግሞ ለሊቱን ከፋፍሎ በዚክር፣በዱዓእና በኢስቲግፋር እንዲሁም የቻልነውን ያክል ረዘም ያሉ 2/2 ረክዓ ሱንና ሰላቶችን በመስገድ ልናሳልፍ ይገባናል፡፡
አላህ ያግዘን ለይለቱል-ቀድርንም ይወፍቀን "ኣሚን"
ኡስታዝ አሕመድ አደም
123 viewsAm First, 22:06