Get Mystery Box with random crypto!

Muslim ሙስሊም

የቴሌግራም ቻናል አርማ ethiomuslim_1 — Muslim ሙስሊም M
የቴሌግራም ቻናል አርማ ethiomuslim_1 — Muslim ሙስሊም
የሰርጥ አድራሻ: @ethiomuslim_1
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 851

Ratings & Reviews

1.67

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

2


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 39

2022-07-27 17:04:51 #ሐያቱ_ሷሐባ

#ቢላል_ኢብኑ_ረባሕ
#ክፍል_1

የአቡበክር ስም ሲነሳ ዑመር ኢብኑል ኸጧብ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “አቡበክር ልዑላችን ነው። የኛን ልዑልም ነፃ አውጥቶልናል።”

ዑመር “ልዑላችን” ሲሉ ያሞካሹት ግለሰብ ታላቅ ሰው ነበር። እጅግ በጣም ዕድለኛ። ይህ ሰው እንዲህ ዓይነቱን የሙገሣ ቃል ሲሰማ ግንባሩን ደፋ፥ ዓይኑን ገርበብ በማድረግ “እኔ ትናንት ባሪያ የነበርኩ የሐበሻ ሰው ነኝ” ይል ነበር።

ለመሆኑ የትላንቱ የሐበሻ ባሪያ የዛሬው ልዑል ማን ይሆን?

ቢላል ኢብኑ ረባሕ ነው። የኢስላም “ሙአዚን”ና የጣዖታት አሳፋሪ ነው። የእምነትና የእውነተኛነት (ኢማንና ሲድቅ) ወርቃማ ፍሬ ነው።

በየትኛውም ጊዜና ቦታ ከሚገኙ ሙስሊሞች መካከል ቢያንስ ከአሥሩ፥ ሰባቱ ቢላልን ያውቁታል። ስሙን ዝናውንና ሚናውን በሚገባ ያወሱታል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አቡበክርንና ዑመርን እንደሚያውቁ ሁሉ የቢላልም ስም እንግዳ አይሆንባቸውም። ሕፃናትን ቢላል ማን ነው ብለህ ብትጠይቅ የአላህ መልዕክተኛ “ሙአዚን” ነው ይሉሃል። አሳዳሪው በጋለ ድንጋይ ላይ በማስተኛት ሲያሰቃየው ወደ ጥንት እምነቱ ከመመለስ ይልቅ “አሐድ አሐድ...” በማለት ጽናትን የገለጠ ሰው ነበር የሚል ምላሽ ታገኛለህ፡፡

ይህ ሁሉ ታላቅ ዝናና ዕውቅና ያተረፈው ቢላል ኢስላምን ከመቀበሉ በፊት በሕዝብ ዘንድ ከእንስሳ ተለይቶ የማይታይና የተናቀ ባሪያ መሆኑን ማስታወስ ያሻል።

ይህ ሰው ኢስላምን ባይቀበል ኖሮ የአሳዳሪውን ግመል ከመጠበቅ ሌላ የሕይወት ሚና የማይኖረው፥ ከሞተ በኋላ ቀርቶ በሕይወት ዘመኑም አስታዋሽ አካል የሌለው ተራ ፍጡር ሆኖ በቀረ ነበር። ነገር ግን በእውነተኛ ኢማን በመጠመቁ፥ ታታሪና ቀናኢ በመሆኑ የገባበት ሃይማኖትም እጅግ ታላቅ በመሆኑ ቢላል ኢስላም ከሚያወሳቸው ድንቅ ሰዎች መካከል በመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠቃሽ ለመሆን በቅቷል! እንዳውም ከፍተኛ የታሪክ ሰዎች የቢላልን ያህል ትውስታ አልተቸሩም።

የቆዳው መጥቆር፥ የሙያውና የዘሩ እውቅ ያለመሆን፥ በሰዎች ዘንድም ትናንት ነፃ የወጣ ባሪያ መሆኑ ቢታወቅም ኢስላምን ከመረጠ በኋላ ወደ ከፍተኛ ደረጃና ማዕረግ ለመሸጋገር አላገደውም። እንደ ቢላል ያለ ከዐረብ ጐሣ ያልሆነ ባሪያ ዘመድና ኃይል የሌለው ሰው ለታላቅ ዕጣ ይበቃል ብሎ የሚገምት አልነበረም። ከቁረይሽም ነገድ ውስጥ በታላቅነታቸው የሚታወቁና ኢስላምን የተቀበሉ ግለሰቦች ሲመኙት የነበረውን የነቢዩ ሙሐመድ “ሙአዚን” የመሆን ዕድልም ቢላል ማግኘቱ የሚደንቅ ነው።

የቢላል እናት ጥቁር ሐበሻ ናት፡፡ የአላህ ውሳኔ ሆነና የበኒ ጁመሕ ጐሣ አባል ለሆነ ሰው በባሪነት ተመዘገበ። እናቱም የዚሁ አባላት ባሪያ ነበረች፡፡ ዛሬ አንዳች መብት የሌለውና ለነገም አንዳችም ተስፋ የሌለው ተራ ባሪያ ነበር ቢላል።

የሙሐመድ ዜና ከቢላል ጆሮ መግባት ጀመረ። የመካ ሰዎች በትኩስ ወሬነት የሚያነጋግሩት ሙሐመድ ነቢይ ነኝ ብሎ የመነሳቱን ጉዳይ ነበር። አሳዳሪውና እንግዶቹም በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ይሰማል። በተለይ ኡመያ ኢብኑ ኸለፍ የተባለው አሳዳሪው ተንኮል የተሞላበት ውይይትና ምክክር ከጥቂት ሰዎችና ከበርካታ እንግዶች ጋር ሲነጋገር አድምጦታል።

የቢላል ጆሮ ተሰብሳቢዎቹ ከሚናገሩት የጥላቻ ንግግር ውስጥ ሙሐመድ ስለተነሱበት ዓላማና ምን እያሉም እንደሚያስተምሩ ሊቀነጭብ ቻለ። አዲስ የመጣው ሃይማኖት ለአካባቢው እንግዳና ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ፥ ሙሐመድም ምንም እንኳ ነቢይ ነኝ ብለው በመናገራቸው ተቃውሞ የገጠማቸው ቢሆንም ታማኝ፥ እውነተኛና በሥነ ምግባር የታነጹ መሆናቸውን ከጠላቶቻቸው ቁንጮዎች አንደበት አድምጧል። “ሙሐመድ አንድም ቀን ዋሽቶ አያውቅም። የአዕምሮ ዘገምተኛም ሆነ እብድ አልነበሩም። ዛሬ ግን እኛ እርሱን በእነኝህ ነገሮች መጥራት ይኖርብናል። ወደርሱ የሚጐርፉትን ሰዎች መግታት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው” በማለት ሲዶልቱ ታዝቧቸዋል። ሙሐመድን የሚቃወሙት በቅድሚያ የአባቶቻቸውን ዲን በቀጣይነት ለማረጋገጥ ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የቁረይሽን የበላይነት የሚያከስም መሆኑ ስለተሰማቸው ነው። ቁረይሽ በመላው ዐረብ ለጣዖታዊው እምነት ማዕከል በሆነችው በመካ የሚገኝ ነገድ በመሆኑ ተፈሪነቱና ከበሬታው የላቀ ነበር። በሦስተኛ ደረጃ ሃሺም ተብሎ በሚታወቀው የነቢዩ ሙሐመድ የዘር ሐረግ ቤተሰብ ላይ ያሳደሩት ቅናትና ምቀኝነት ነበር። ከበኒ ሃሺም ቤተሰብ ነቢይና መልዕክተኛ መምጣቱን እንደ ሽንፈት ቆጥረውታል። ሁሉም ቤተሰብና ጐሣ ነቢይ ከራሱ ወገን እንዲመጣ ይሻ ነበር...!

ከዕለታት አንድ ቀን ቢላል ኢብኑ ረባሕ የኢማን ብርሃን ፈነጠቀበት፡፡ ምርጫውን ይፋ ማድረግ እንዳለበት ወሰነ። ወደ ነቢዩ ሙሐመድ በመሄድም ለኢስላም እጁን መስጠቱን ይፋ አደረገ። የቢላል መስለም በመካ ምድር ተሰማ። የበኒ ጁመህ መሪዎች በቁጣ ተወጠሩ። በተለይ አሳዳሪው የኢስላም ጠላት ኡመያ ኢብን ኸለፍ ሐበሻዊ ባሪያው መስለሙን እንደ ታላቅ ነውርና ንቀት ቆጥሮታል። ለዚህም እንዲህ አለ፦ “ይህ ኮብላይ ባሪያ በመስለሙ ፀሐይ ተመልሳ የምትጠልቅ አይመስለኝም...” ሲል ቁጭቱን ገለጹ።

ቢላል ግን ለኢስላም ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የሚያኮራ አቋም ከመውሰድ ወደ ኋላ አላለም። አላህ የአንድ ሰው የቆዳ ቀለሙ መጥቆር ከፍተኛውን የኢማን ደረጃ ከማግኘት የሚያግደው እንደማይሆን በቢላል ተምሳሌት አስተምሯል። ቢላል ለዘመኑ ሰዎችና ከርሱ በኋላ ለመጣው ትውልድ እንዲሁም እምነት ለሚያጋሩትም ሆነ ለማያጋሩት ወገኖች ያስተማረው ትምህርት ቢኖር የሕሊና ነፃነትና ሉዓላዊነት ምድርን የሞላ ንዋይም ሆነ አሰቃቅ ቅጣት ሊበግረው እንደማይችል ነው። ቢላል እርቃኑን በትኩስና አሸዋማ መሬት ላይ እንዲንከባለልና ቋጥኝ ድንጋይም ደረቱ ላይ እንዲጫን ተደርጓል። ግን እምነቱን ሊቀይር አልፈቀደም። በተከታታይና በተደጋጋሚ ኢ_ሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል። የቁረይሽ ሹማምንት አንድን ባሪያ ሊያሳምኑትና ወደ ቀድሞው እምነቱ ሊመልሱት ባለመቻላቸው ቁጭትና ሀፍረት ስለተሰማቸው ክብራቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ቢላል ቢያንስ ቢያንስ ስለ አማልክቶቹ ጥቂት በጎ ነገር እንዲናገር ጠይቀውት አሻፈረኝ አለ። ሕይወቱን ከስቃይ ምናልባትም ከሞት ለማዳን አማልክታቸውን ከልቡ እንኳ ባይሆን ማመስገን በቂ ነበር። ታላቁ ቢላል ግን ከሥጋዊ ህመም መንፈሳዊ የበላይነትን በመምረጡ ለጠላቶቹ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ይልቁን በተደጋጋሚ “አሐድ.. አሐድ...” በማለት የመለኮትን አንድነት ያውጅ ነበር። “ላት” እና “ዑዝዛ” የተሰኙ ጣዖታትን እንዲያወሳ ያለ መታከት ይጠይቁታል። መልሱ ግን “አሐድ... አሐድ...” ነበር። እኛ የምንለውን ደግመህ በል በማለት ይገርፉታል። በምጸታዊ ቃልም፦ “እናንተ የምትሉትን ለመናገር ምላሴ አይችልም...” ይላቸዋል። “ላት እና ዑዝዛ ጌታዎች ናቸው አንተንም እምነትህንም እንተዋችኋለን፤ በርግጥ እኛ ራሳችን ስቃይ ተቀባዮች የሆን ይመስል አንተን በማሰቃየት ደክመናል።” ይሉታል። ጭንቅላቱን በመነቅነቅ ፦ “አሐድ... አሐድ...” የሚል ምላሽ ከመስጠት ባሸገር እጅ አልሰጠም ቢላል። ቁረይሾች ተስፋ አልቆረጡም። “አናሰቃየው፥ እርሱ የኛ ወገን ነው። እናቱም የኛ ደንገጡር ነች፡፡ በመስለሙ እኛን የቁረይሽ መዘባበቻ አያደርገንም።” አሉ። ቢላል ግን ለተንኮላቸው አልተንበረከከም፦ “አሐድ... አሐድ...” በማለት የአላህን አሃዳዊነት ገለጸላቸው።
ቴሌግራም
https://t.me/ethiom
168 viewsAm First, 14:04
ክፈት / አስተያየት ይስጡ