2023-03-20 13:27:16
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት በዚህ አመት ሊሰጥ በታሰበው የመውጫ ፈተና ዙርያ በስሙ የተሰራጨው መረጃ ህብረቱን የማይወክል መሆኑንን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት በቅርቡ በስሙ በተሰራጨው መረጃ ዙርያ በትላንናው እለት መጋቢት 09/2015 ዓ.ም መግለጫ አውጥቷል።
የተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናን በተመለከተ በአስፈላጊነቱ ዙርያ ሁሉም ያመነበት ነው ሲል የገለፀው መግለጫው ፈተናው ስለሚሰጥበት ጊዜና ሁኔታ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ሲሰነዘሩ መቆየቱን አውስቶ ፈተናው ተማሪዎችን ባማከለ መልኩ በዚህ አመት እንዲስጥ የተወሰነ በመሆኑ ተማሪዎች በሚያነሷቸው ስጋቶች እና ቅሬታዎች ላይ ከትምህርት ሚኒስተር ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መጠነ ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን እንዲሁም ወደፊትም እንደሚደረጉ ተገልጿል።
በውይይቶቹ የተነሱ ሀሳቦች ገሚሶቹ ምላሽ ያገኙ ቢሆንም በቀጣይም በውይይት ዳብረው የሚስተካከሉ መረጃዎችን የሚያሳወቅ መሆኑንን የገለፀው ህብረቱ፤ ፈተናው የተማሪዎችን ብቃት የሚመዝን እና የተነሱ ጥያቄዎችን ያገናዘበ እንዲሆን ብሎም የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ሊያስጠብቅ በሚችልበት ሁኔታ ላይ አሁንም በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውሷል።
ተማሪዎች በፈተናው እና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሀሳብ በግቢያቸው ላለው የተማሪዎች ህብረት እያቀረቡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ት/ት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት በኩል ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑንም ተገልጿል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት ስም የተሰራጨው መረጃ ፈፅሞ ህብረቱን የማይወክልና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የተገለፀ ሲሆን በህብረቱ በኩል የተጠራ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ ባለመኖሩ፤ ተማሪዎች በተለይም የዚህ አመት ተመራቂዎች በተረጋጋ መንፈስ በቅርብ በተሰራጨው የፈተናው ንድፈ ማሳያ(Blueprint) እና የተመረጡ የትምህርት አይነቶች ያሉበት ቁልፍ የብቃት መለኪያ (Core Competencies) መሰረት በማድረግ፤ በተቋሞቻቸውና በህብረቶቻቸው በኩል የሚሰጡ የድጋፍ ትምህርቶችን በመከታተል፣ እርስ በእርስ በመተጋገዝ እንዲሁም በተናጥል በማንበብ ብሎም ከሀሰተኛ መረጃዎች በመጠበቅ በዩንቨርሲቲዎቻቸው ካሉ ህብረቶች፣ ከመምህራን እና ከበላይ አመራሮች ብቻ ትክክለኛውን መረጃ በመውሰድ ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ህብረቱ ጥሪ አቀርቧል።
በመጨረሻም ህብረቱ የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ተማሪዎችን የሚያዘናጉ እና አላስፈላጊ ለሆነ ነገር የሚያነሳሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳስቧል።
#መረጃው_የኢትዮጲያ_ከፍተኛ_ትምህርት_ተቋማት_ተማሪዎ_ህብረ_የመረጃና_አለም_አቀፍ_ግንኙነት_ዘርፍ_ነው
@Ethio_Students_only
@Ethio_Students_only
4.6K viewsAYY, edited 10:27