2022-08-29 15:00:00
ጥያቄ፡-
ሰላም ነው ዶ/ር አዮብ ትምህርትህን በጣም ነው ምወደው እኔ ልጠይቅ ምፈልገው በህይወቴ አዲስ ነገር መልመድ በጣም እፈራለው አዳዲስ እድሎች ሲያመጡልኝ ስለምፈራ የት ይሄድብኛል ብዮ እራሴን አታልላለው ሲያመልጠኝ ደሞ መጀመሪያም ለኔ አልሆነም እላለው ይሄን ነገር እንዴት ልታገለው?
መልስ፡-
ሁላችንም ቢሆን አዲስ ነገርን እንፈራን፡፡ ለዚህ ነው ከምቹ ስፍራችን፣ ከለመድነው ባህላችንና ከመሳሰሉት ሁኔታዎች መውጣትና ለውጥን ብዙም የማንወደው፡፡ ነገር ግን ፍርሃቱ ከመጠን ሲያልፍ በአንድ ቦታ ተቆልፈህ እድሜህን እንድታስበላና ነገ እንድትጸጸት የሚደርግ ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ነገር የመጋፈጥ ፍርሃት ምንጩ ብዙ ሲሆን ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
የሚፈልጉትን ነገር ወይም ዓላማን በሚገባ አለማወቅ፡- ለመልመድ የፈለከው አዲስ ነገር ከህይወትህ ዓላማም ሆነ ለማከናወን ከምትፈልገው ነገር ጋር ግንኙነት ከሌለው ውስጥህ የመወሰን ጉልበት አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ያንን እርግጠኛ ሁን፡፡
በራስ የመተማመን ጉድለት፡- አዲስ ነገር ጀምረህ እስከጥጉ መውሰድ እንደማትችልና ሌሎቹ ጎበዞች አንተ ግን ብዙም ያልጎበዝክ አይነት ሰው እንደሆንክ ካሰብክ ምንም አዲስ ነገር የመጋፈጥ አቅም አይኖርህም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው አዲስ ነገር ውስጥ ሲገባ መጀመሪያ ግራ ገብቶት በኋላ ግር ራሱን በትጋት እያስለመደ ማደጉን አትርሳ፡፡
ጭፍን (ምክንያት-የለሽ) አዲስ ነገርን የመፍራት ዝንባሌ፡- በስነ-ልቦናው ቋንቋ “የማያታወቀውን መፍራት” (Fear of The Unknown) የሚባለው ሁኔታ ይኖርብህ እንደሆነ ራስህን ፈትሽ፡፡ ምንም ነገር ውስጥ ሁሉንም ነገር እርግጠኛ ሆነህ መግባት አትችልም፡፡ ማድረግ የምትችለው ሊደርስብህ ለሚችለው ነገር ራስህን በበቂ ሁኔታና የምትችለው ያህል በማዘጋጀት መራመድ ነው፡፡
የከዚህ በፊት የከሸፉ ሙከራዎች፡- ከዚህ በፊት አዳዲስ ነገሮችን ሞክረህ ደጋግሞ አልተሳካም ማለት ዛሬ አይሳካም ማለት አይደለም፡፡ የከዚህ በፊቱ ያልተሳካው ሁኔታ ምን ትምህርት እንደሰጠህ በማወቅህ የበለጠ መብሰል ነው ያለብህ፡፡
“የአርባ ቀን እድል” አመለካከት፡- አንዳንድ ሰዎች “ምንም ይሁን ምንም እድሌ ነው” የሚል ዝንባሌ አላቸው፡፡ ይህ ዝንባሌ ከአስተዳደግ ባህላዊ ውርስ ወይም ሁኔታዎችን ሁሉ በፈጣሪ ላይ ከመለጠፍ “ኃይማኖታዊ” ቅኝት ሊመጣ ይችላል፡፡ በሕይወተህ መለወጥ በምትችላቸውና በማትችላቸው ነገሮች መካከል በመለየት ተንቀሳቀስ፡፡
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
9.1K views12:00