2023-07-01 15:57:34
ምርምር / Research / ምንድን ነው?
ፔጃችንን #Like ያድርጉ! አንድ ቀን ይጠቅማችኋል #ሼር አርጉት
ከጽሑፍ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ምርመር /Research/ ለሚለው ቃል አንድ ወጥና የማይለዋወጥ ትርጉም አልተገኘለትም፡፡ ምክንያቱም መስኩ ሰፊና በተለያዩ ምሁራን የተለያየ ማብራሪያ ሲሰጥበት የቆየ በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንዳንድ ምሁራን እጅግ በጣም ቀለለ ያለ ትርጉም ሲሰጠው በሌላ ጊዜና በሌሎች ምሁራን ደግሞ ላቅ ያለና ውስብስብ የሆነ ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ምርምር አዲስ ዕውቀትን ለማግኘትና የተገኘውንም እውቀት እውነተኛነት ለማረጋገጥ ወይም በእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያጋጥመንን ችግር መፍትሄ ለማበጀት ሲባል ሥርዓት ባለው ሁኔታ የተቀነባበረና ሆን ተብሎ የሚከወን የሰው ልጅ የተግባር
እንቅስቃሴ ነው፡፡
በዚህም መሠረት በምርምሩ ሂደት ውስጥ የችግሩ ምንነት ይለያል፣ ስልት ይቀየሣል፣ይቀነባበራል፣ መረጃ ይሰበሰባል፣ ይገመገማል፣ ይተነተናል፣ ብሎም የተገኘው
ውጤት በተቀነባበረ መልክ ይገለፃል፡፡ ከዚህም ሂደት በመነሳት ምርምር ሳይንሳዊ ይዘት አለው ማለት ይቻላል፡፡
የምርምር /Research/ ዓይነቶች
ልዩ ልዩ የምርምር ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ለዚህ ጽሑፍ አስፈላጊ ናቸው የተባሉትንና ዋና ዋናዎቹን በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
. ታሪክ ነክ ምርምር / Historical Study/
በዚህ የምርምር ዓይነት ተማራማሪው ያለፈን ታሪክ በማጥናትና በመመዝገብ ዕውቀቱን ያዳብራል፡፡ ይህ ዓይነት ምርምር ሲያዩት ቀላል ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን ተማራማሪው የተነሳበትን መላምት ለማረጋገጥ የተለያዩ መረጃዎችን አሰባስቦ ማስረዳት መቻል ይኖርበታል፡፡
ለምሳሌ አንድ ተመራማሪ ስለ ኢትዮጵያ ትምህርት ታሪክ ሲያጠና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ከንግሥት ዘውዲቱ ይልቅ አጼ ምኒሊክ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርገዋል የሚለውን ሃሳብ ይዞ ቢነሳ ሐሳቡ እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን በተለያዩ ዘዴዎች መረጃዎችን ሰብስቦ በማገናዘብ አሳማኝ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡
. ገላጭ ምርምር
ይህ የምርምር ዓይነት የአንድን ሁኔታ ትክክለኛ ገጽታ ለማወቅ ወይም በትክክል ለመግለጽ ሲባል መረጃዎችን ከመጽሐፍትና ከሌሎችም ጥናታዊ የጽሑፍ ምንጮች
በማሰባሰብና የምልከታ መረጃዎችን በማጠናቀር ትንተና በማድረግ የሚያጠና ሲሆን ውጤቱን በስድስት ንዑስ ክፍሎች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
እነሱም፡-
ሀ/ ውሱን ጥናት /Case study/
ለ/ አወዳዳሪ ጥናት /Comparative Study Study/Studies/
ሐ/ ዕድገት ተኮር ጥናት/developmental
መ/ ተከታታየነት ያለው ጥናት/follow up studies/
ሠ/ ተዛምዶን የሚያሳይ ጥናት /correlational/
ረ/ አሣሽ ጥናት/Survey Study/
2.1. ውሱን ጥናት /case Study/
ይህ ዓይነቱ ምርምር የአንድን የተወሰነ ሁኔታ የአለፈ ታሪክ ጨምቆ በማጥናት አሁን ላለው ይዘትና ጠባይ በማብራሪያነት መጠቀምን ይመለከታል፡፡
ለምሳሌ ተማራማሪው ስለ አንድ ተማሪ ጠባይ ማጥናት ይፈልጋል እንበል፡፡ ተማሪው በት/ቤቱ አስቸጋሪ
ፀበይ/ባህሪ ቢኖረው የጥናቱ ትኩረት በዚሁ በተማሪው ጠባይ ላይ ይሆናል፡፡ በጥናቱ ሂደት ሊነሳ የሚችለው ዋናው ጥያቄ ይህ ተማሪ ለምን እንዲህ ሆነ የሚለው ነው፡፡
በዚህ መሠረት ሊሰጡ ከሚችሉ መልሶች አጥኚው መላ መምታት ይችላል፡፡ ከመላ ምቶቹ ውስጥ፡-
ከመምህራንና ተማሪዎች፣ የተቀባይነትና ጥሩ አመለካከት በማጣት፣ በትምህርቱ ውጤት ተስፋ በማጣት፣ ከቤተሰቦቹ አያያዝና አስተዳደግ የተነሳና ሌላም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እንግዲህ የተማራማሪው ተግባር በልዩ ልዩ የምርምር ዘዴዎች ተጠቅሞ በየትኛው ምክንያት ተማሪው ለረብሻ እንደተገፋፋ ማወቅና መንስኤውን ካወቀ በኋላም ልጁ መልካም ጠባይ እንዲኖረው የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች የጥናቱና ምርምሩ ውጤት ያደርጋቸዋል፡፡
2.2. አሣሽ ጥናት / Survey study/
እንደዚህ ዓይነቱ ምርምር ስለአንዳንድ ማህበራዊ ክስተቶች መረጃዎችን አሰባስቦ በመተንተን ስለተጠናው ጉዳይ እውነተኛ ገጽታ መናገር የሚያስችል ነው፡፡
ለምሳሌ ከአንደኛ ደረጃ ትም/ቤቶች ተማሪዎች በየጊዜው እየወጡ የሚቀሩት በምን ምክንያት ነው
በሚል ጥያቄ መነሻ ምርምር ማካሄድ ይቻላል፡፡
ውሱን ጥናት በተወሠነ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ማካሄድ ሲሆን አሣሽ ጥናት ደግሞ ሠፋ ባለ ርዕስ ጉዳይ ላይ በማተኮር አጠቃላይ መፍትሔ ለመሻት ነው፡፡
2.3. አወዳዳሪ ጥናት /Comparative study/
ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ሁኔታዎችን ወስዶ ስለእያንዳንዱ ጉዳይ በጥልቀት በማወቅ አንዱ ከሌላው የሚለይበትንና አንድ የሚሆንበትን ሁኔታ በግልጽ ማሳየት የሚቻልበት የምርምር ዓይነት ነው፡፡
ለምሳሌ ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራን ሥልጠና የተሻለው ፕርግራም የቱ ነው በዲግሪ ወይም በዲፕሎማ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሁለቱን
ፕሮግራሞች ደካማና ጠንካራ ጎን ለመለየት ከዚህ በፊት በሁለቱም ፕሮግራሞች የሰለጠኑና በሥራ ላይ ያሉትን መምህራን የሥራ ውጤት በጥንቃቄ በመገምገም፣ የተሻለውን ፕሮግራም ማወቅ ያስችላል ማለት ነው፡፡
2.4. ዕድገት ተኮር ጥናት / Developmental Studies/
ይህ ጥናት በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ሕፃናት፣ ወላጆች፣ ተማሪዎች በየእርከኑ የሚያሳዩት የባሕሪይ ለውጥ ወይም የአስተሳሰብና የአእምሮ ዕድገት ለውጥን የማጥናት ሥልት ነው፡፡
ተማሪው በየክፍል ደረጃው በአንድ ወይም ከአንድ በላይ ባሉ የትምህርት ዓይነቶች የሚያስመዘግባቸውን ውጤቶች ተከታትሎ ማጥናትን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡
2.5. ተከታታይነት ያለው ጥናት / Follow-up studies/
ይህ ሥልት አንድ የትምህርት መርሃ ግብር ውጤታማ ስለመሆኑ ለአንድ ሙያ የሰለጠኑ ሰዎች በመስክ የሚያሳዩትን ለውጥ ወዘተ የምንገመግምበት ዘዴ ነው፡፡ በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ወቅት በሙከራ ት/ቤቶች በ1ኛ እና 5ኛ፣ በ2ኛ እና 6ኛ፣ በ3ኛ እና 7ኛ
በ4ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ሲካሄዱ የነበሩ ሂደታዊ ግምገማዎች እንደምሳሌ ሊጠቀሱ
ይችላሉ፡፡
2.6. የተዛምዶ ጥናቶች /correlational studies/
የዚህ ዓይነቱ ሥልት
1. ዕድሜ ከአእምሮ ጋር ያለውን ግንኙነት
2. የአጠናን ሥልት ከትምህርት ውጤት ጋር ያለውን ዝምድና
3. የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤት ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት የሚኖረውን ዝምድናና
የመሳሰሉትን የምንዳስስበት ዘዴ ነው፡፡
. የሙከራ ምርምር /Experimental Study/
ይህ እይነቱ ምርምር አንድን ሁኔታ በሙከራ አረጋግጦ ማየትን የሚመለከት ምርምር ነው፡፡
ለምሳሌ በአፀደ ሕፃናት ፕሮግራም ውስጥ ካለፉና በቀጥታ ከቤታቸው ወደ አንደኛ ክፍል ከገቡ ሕፃናት ሒሣብን፣ አማርኛን፣ ሣይንስን፣ ወይም ሌላ ትምህርት የትኞቹ በይበልጥ እንደሚከታተሉ ሕፃናቱን ለይቶ በጥንቃቄ በመከታተል ማወቅ ይቻላል፡፡
ጥናቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ መረጃዎችን በጥንቃቄ መያዙ ለውጤቱ ትክክለኛነት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
ለምሳሌ ከትምህርት ቤት ውጪ ተጨማሪ እገዛ ማግኘት አለማግኘታቸውን፣ የቤተሰብ ልዩነት አለመኖሩንና የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ ልዩነት ሁሉ መጤን ያለባቸው ነገሮች ናቸው፡፡
1.7K viewsBahiru Abas, 12:57