2022-10-20 09:37:40
የሙፍቲ ሼህ አደም ቱላ ሕይወት እጅግ የሚያስደስት ነው።
የሙፍቲ ሼህ አደም ቱላ ሕይወት እጅግ የሚያስደስት ነው። እድሜያቸውን በሙሉ በዲን ኪድሚያ ነው ያሳለፉት።
ሙሉ ስማቸው ሼህ አደም ቱላ አህመድ ኢብራሂም ዑስማን(ሸንኮር) ይባላሉ።ወደ 110 ዓመት የሚጠጋ እድሜ በሕይወት ኖረዋል።ከዚህ ቀደም ከኑረል ሁዳ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እርሳቸውና የጎረቤት ልጅ በተመሳሳይ እለት የተወለዱ ሲሆን የጎረቤቱ ልጅ አባት ልጁ የተወለደበትን ቀን በማስታወሺያ የተጻፈውን መነሻ በማድረግ በጊዜው እድሜያቸው 104 ዓመት እንደሆነ ገልጸው ነበር። ከ2ኛው የጣሊያን ወረራ ቀደም ብሎ ነበር በ12 ዓመታቸው እያሉ በሱማሌው ሼህ ሙሀመድ ኢብራሂም ኩርኮሮ ላይ ቁርኣንን ጨርሰው ሰፊናንና ዑምደቱል አህካም ኪታብን ተማሩ።
ሼህ አሊይ ዐርሲ ዘንድ ለ10 ዓመታት የተለያዩ የፊቅህ ኪታቦችን እስከ ሚንሀጅ ድረስ ተማሩ።የዐረብኛ ቋንቋ ናህው፣ ሰርፍ፣በያንና መንጢቅ የጅማ ተወላጅና በአንይ ማዕከል በተማሩት በሸህ አብዱልመጂድ ዘንድ ጀምረው፣በሀረሩ የኮምቦልቻ ተወላጅ ሼህ ሰኢድ ዘንድ አጠናቀቁ።
የተፍሲር ትምህርት በኮምቦልቻው ሼህ ሰኢድ ዘንድ ጀምረው የለኦዳ የተሰኘ አከባቢ ሼህ ሙሳ ዘንድ አጠናቀዋል። የተውሂድና ሀዲስ ትምህርቶችን የተለያዩ ዓሊሞች ዘንድ ተምረው ማስተማር ጀመሩ።
በኢስላማዊ ዳዕዋና ተግባራት ላይ ለ80 ዓመታት ገደማ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓሊሞችን ያፈሩ ሲሆን በምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ፣በሀረሪ ክልልና ድሬደዋ አብዛኛዎቹ ዓሊሞች፣ የመስጂድ ኢማሞች የርሳቸው ተማሪዎች ወይንም የተማሪዎቻቸው ተማሪዎች የነበሩ ናቸው።
ሼህ አደም ቶላ በራሳቸው የኢልም ማዕከል(መጅሊስ) በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የነበራቸው ሲሆኑ እስከ አምና ድረስ በርካቶችን አስተምረው አስመርቀዋል።
ከመደበኛ በተማሪዎች ባሻገር አርሶ አደር ዓሊሞችንም አስተምረው ከ3 ዓመታት በፊት አንድ ሺህ ስምንት መቶ ስልሳ አንድ ሴቶችና ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ወንዶች በድምሩ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሠላሳ ሦስት የገበሬ ተማሪዎችን በሀረር በጨለንቆ አዳራሽ አስመርዋል። ተመራቂዎቹ በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ገበሬዎች የሆኑ ሥራቸውን እየሠሩ በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ ከጠዋቱ 2:30 እስከ 3:30 ብቻ ከ3 እስከ ስድስት ዓመታት በመቅራት ቂርዓታቸውን ጨርሰው በሸይክነት የተመረቁ ነበሩ።
ሼህ ዐደም ቱላ በ1960ዎቹ የሙስሊሞች መሪ ድርጅት ለማቋቋም በሀረርጌ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከነበሩት ዓሊሞች አንዱ የነበሩ ሲሆን 1966 ጀምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን(መጅሊስን) ለመመረሰት በተደረገው ጥረትና ከመሰረቱት ዑለሞች መካከል አንዱ ነበሩ።
በሙስሊሞች የመብት ጉዳይ በድፍረት ይናገሩ ዓሊም ሲሆኑ በ2004 ጀምሮ በተደረገው የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ በግልጽ መንግስትን ሲተቹ የነበሩና ለታሳሪዎች ዱዓ ያደርጉ ነበር።
በመጋቢት 2010 ከእስር ቤት ስንፈታ እድሜያቸው 100 አልፎ እንኳ ከሀረር አዲስ አበባ እኔ ቤት ድረስ በአካል በመምጣት «እንኳን አላህ አስፈታችሁ» ብለው መርቀው ዱዓም አድርገውልን ነበር።
በሀረርጌ በሞላ «የመሻይኮች ሼህ» በሚል ማዕረግ ይታወቁ የነበረ ሲሆን ከዓመት በፊት የኦሮሚያ መጅሊስ «ሙፍቲ» የሚል ማዕረግ ሰጥቷቸው ነበር።
እኚህን ታላቅ ዓሊምና ሙፍቲን ለመሸኘት ዛሬ በጠዋቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን፣የአዲስ አበባ መጅሊስ ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን ሀጅ አማን፣ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢ የመጡ ዓሊሞችና እንግዶች ድሬደዋ ገባን።የድሬደዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር አቀባበል አደረጉልን። ቁርስም ጋበዙን።
ቀጥሎም ከሀረርጌ ወረዳዎችና ድሬደዋ ለቀብር ተሚመጣው ህዝብ ብዛት መንገዱ ስለተጨናነቀ በፍጥነት እንድንደርስ በፖሊስ መኪኖች አጀብ ወደ ሀረር አብረን አቀናን።
ህዝቡ በኢማም አህመድ ስታዲየም ከሱብሂ በፊት መግባት የጀመረ ሲሆን በጠዋቱ ሞልቶ ተጨናንቆ አብዛኛው ሰው በከተማው መንገዶች ላይ ተጨናንቆ ደረስን።
ከህዝብ መጨናነቅ የተነሳ ገሚሱ ህዝብ ቀድሞ ሰግዶ እየወጣ ነበር። እኛና እንደ አዲስ ስታዲየሙን የሞላው ህዝብ በመጅሊስ ምክትል ፕሬዝዳንት መሪነት ሰላቱል ጀናዛ ሰገድን። ከተለያዩ አከባቢ የመጡና አውሮፕላን አምልጧቸው የዘገዩት እንደ ዶ/ር ጄይላን ከድር፣ዶ/ር ሼህ ሙሀመድ ሀሚዲን፣ ኡስታዝ ጋሊ አባቦር፣የኦሮሚያ መጅሊስ ፕሬዝዳንት ሼህ ጀማል ሙሳ፣ሼህ አሊ ጅማ፣ሼህ ሻፊ አብዱራህማን እና ሌሎች እንግዶች እንዲደርሱ ሲባል ቀብሩ በአስር ላይ እንዲሆን በተወሰነው መሰረት ቀብሩ በአስር ሰላት ላይ ተፈጸመ።
አላህ ጀነተል ፊርደውስን ይመንዳቸው። ከፊል እንግዶች ሀረር ሲያድሩ እኛም በአላህ ፈቃድ በሼህ አደም ቱላ ሽኝት ላይ ተሳትፈን በአላህ ፈቃድ አሁን ወደ አዲስ አበባ አሁን ተመለስን።
21.2K views06:37