Get Mystery Box with random crypto!

በድንገት ከሁሉም ለየት ያለ ሰው ወታደራዊ ልብሱን እንደለበሰ መትረየሱን ደግኖ ወደ ሰልፉ ጠጋ አለ | Ahmedin Jebel - አሕመዲን ጀበል

በድንገት ከሁሉም ለየት ያለ ሰው ወታደራዊ ልብሱን እንደለበሰ መትረየሱን ደግኖ ወደ ሰልፉ ጠጋ አለ። የአስተባባሪዎቹ ዓይን በቅጽበት በርሱ ላይ ዐረፈ።የባሕር ኃይል ምክትል ኃላፊ የነበረው ኮማንደር ዘካርያ ይባላል። ሙስሊም ነው። የእምነት ጭቆና አንገሽግሾታል። ብዙ በደሎች ደርሰውበታል። ሌላ ምንም ጥፋት አላጠፋም፤ወንጀሉ ሙስሊም መሆኑ ብቻ ነበር! ጠጋ ብሎ ወደ ሰልፉ ተቀላቀለ። መትረየሱን ደግኖ የመጣው ‹‹ከመንግሥት ኃይል ጥቃት ይፈጸምብናል›› በሚል ሥጋት ነበር። ዶ/ር አሕመድ ቀሎ ጠጋ ብሎ ‹‹ይህ ምንድን ነው?›› ሲል ጠየቀው። ‹‹ዛሬ ቀናችን ነው! ብናልቅም ጨርሰን ነው የምንሞተው!›› ሲል መለሰ። በርግጥ ሰልፉ የተጠራው ያለፈቃድ ነው። ሆኖም መንግሥት ሳይወድ በግድ ሰልፉ እየተካሄደ ነው። ዶ/ር አሕመድ ቀሎ አግባብተው ሰይፉን ብቻ ታጥቆ ከነወታደራዊ ልብሱ በሰልፉ እንዲሳተፍ አደረጉት።

ሙስሊሙ ለመብቱ ሲል እንዲያ ሲሆን ለጥቅም ብለው ከመንግሥት ጋር የወገኑ ሙስሊሞችም አልጠፉም። ከሙስሊሙ መብት መከበር ይልቅ ለነሱ የበለጠባቸው ዓለማዊ ጥቅም (ከመንግሥት የሚገኝ ጥቅም) ነበርና። የሙስሊሙ ስሜትና ብሶቱን የሚያሰማበት አኳኋን አስደንጋጭ ነበር። ማንም ‹‹እንደዚህ ያለ ሰልፍ ይደረጋል›› ብሎ አልጠበቀም ነበር። ‹‹ሙስሊሙ እንዲህ ይበዛል›› ብሎ የገመተም አልነበረም። ሰልፉን ለማክሸፍ ሲራወጡ የነበሩት የደህንነት አባላትም ጥረታቸው ከሽፎ ከፖሊስ ጋር ፀጥታ ለማስከበር ጥግ ጥጉን ይዘዋል።
ሰልፉ ተጀመረ። እየዘመረ፣ መፈክር እያሰማና ተክቢራም እያለ ከአንዋር መስጂድ ተንቀሳቀሰ። ሐብተ ጊዮርጊስ ድልድይን ተሻገረ። ፒያሳን አቋርጦ ራስ መኮንን ድልድይን አለፈ። አራት ኪሎ አካባቢ ሲደርስ ትንሽ ግርግር የሚጀመር መስሎ ነበር። ግና ወዲያው ተረጋጋ። ጉዞውንም በሰላም ቀጠለ። በየመንገድ ዳር የቆሙና በየፎቅ በረንዳ ላይ በመስኮት በኩል በሚመለከቱት ጭብጨባ ደመቀ።መፈክሮች ተስተጋቡ፡-

‹‹ሀገር የጋራ ነው! ሃይማኖት የግል ነው! እስላማዊ በዓላት ብሔራዊ በዓላት ይሁኑ! ‹ኢትዮጵያዉያን እስላሞች› ተብለን እንጠራ! የሃይማኖት ልዩነት በየትም ቦታና መሥሪያ ቤት ይቅር! የእስልምና ሃይማኖት የመንግስት ድጋፍ ይኑረው! ኢትዮጵያ በሃይማኖት መከፋፈል የለባትም! ኢትዮጵያዉያን እስላሞችና ክርስቲያኖች ወንድማማቾች ናቸው! በኢትዮጵያዉያን መካከል አንድነት ለዘለዓለም ይኑር! ኢትዮጵያ በልጆቿ አማካይነት ወደፊት ትራመድ! አንድነት ኃይል ነው! ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዉያን ደሴት ናት! ነቀፌታ የማይቀበል መንግሥት ዘለቄታ የለውም! (የኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ተቋም፣ ማኑስክሪፕት ክፍል፣ ማኅደር ቁጥር 2396/02/5)

ይቀጥላል....