2022-08-31 12:33:06
"የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዉ የጎላ ነዉ"
የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ነሐሴ 25 ቀን 2014
የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት በህይወት ክህሎት ስልጠና፣ በሥራ ክህሎት ዝግጁነት፣ በስነ ምግባርና በሥራ ፈጠራ ክህሎት ንቁና ብቁ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ገበያው በማስገባት ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንደሚያስገኝ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በስራ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን፤ በቂ የሥራ፣ የክህሎትና የህይወት ክህሎት ስልጠና አግኝተው ወደ ሥራው ዓለም የሚቀላቀሉ ወጣቶች ከባለሀብቶች ጋር ተግባብተው የመስራት ዕድላቸው ሰፊ ስለሚሆን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ቀጥተኛ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ብለዋል።
በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አማካኝነት በተደረገ ጥናት መሠረት በአዲስ አበባ ደረጃ ከ18 እስከ 20 ዕድሜ ክልል ባሉ ወጣቶች ሥራ አጥነቱ ይከፋል ያሉት አቶ ሰብሃዲን፤ በተለይ ከ10ኛ ክፍል በታች የሆኑ የስራ አጥ ወጣቶች 82 በመቶዎቹ እንዲሁም ከሴቶችም በዚህ የዕድሜ ክልል ካሉት 30 ነጥብ 4 በመቶ ያህሎቹ ስራአጥ ናቸው፡፡
በትምህርት ዝቅ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ገበያው ላይ ያላቸው ተፈላጊነት አናሳ መሆኑ ለስራ አጥ ቁጥሩ መጨመር ምክንያት መሆኑን አንስተው፤ ፕሮጀክቱ ለእነዚህ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ላይ የጎላ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው ያስችላል የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተመሳሳይ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ከሆኑ ወጣቶች 24 ነጥብ 6 በመቶ ያህሎች ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ሰብሃዲን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ እነዚህን ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ የሚያተኩር መሆኑንም አስገንዘበዋል፡፡
አክለውም፤ “በእነዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ወደሥራው ዓለም መግባት የሚችሉት ክህሎት ሲኖራቸው ነው፡፡ ክህሎቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያገኙት ደግሞ ወደቀጣሪዎች ተጠግተው ስልጠና ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት ተቀርጿል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ሳቢያ ወጣቶቹ በየፋብሪካው ውስጥ ገብተው ለ6 ወራት የሥራ ላይ ልምምድ ስልጠና ይወስዳሉ” ብለዋል።
ወጣቶቹ ለስድስት ወር በፋብሪካዎች ውስጥ ሲሰለጥኑ በወር 1 ሺህ 980 ብር እንደሚከፈላቸው የገለፁት አቶ ሰብሃዲን፣ ከስልጠናው በኋላም ልምምድ ያደረጉበት ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ቅጥር እንዲፈፀምላቸው ይደረጋል፡፡
ከስልጠና በኋላ የሥራ ማፈላለጊያ የሶስት ወር ደመወዝ ይሰጣቸዋል፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የሆኑት ሰልጣኞች ግን እዚያው የሥራ ልምምድ ባደረጉባቸው ተቋማት ውስጥ እንዲቀጠሩ ይደረጋል ሲሉ አሳውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ህፃን ላላቸው ሴቶች 600 ብር የህፃናት ማቆያ ክፍያ እንደሚፈፀምላቸው ታውቋል፡፡ ከስራ ልምምድ ስልጠናው በተጓዳኝ ገበያው ላይ ተፈላጊነታቸውን የሚያሳድጉላቸው ተያያዥ ስልጠናዎች እንደሚሰጧቸው የገለፁት አቶ ሰብሃዲን፤ ከእነዚህም ውስጥ የእርስ በእርስ መማማሪያ ዕድል፣ የህይወት ክህሎት ስልጠና እና መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ደረጃ 49 ሺህ ወጣቶች የሥልጠናውና የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ታቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተመዝግበው የህይወት ክህሎት ስልጠና ወስደዋል፣ ወደ 21 ሺህ የሚሆኑት አሁንም በህይወት ክህሎት ስልጠና ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
10 ሺህ 500 ወጣቶች በቀጥታ የሥራ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ከተመረጡ 1 ሺህ 500 እንደ የማፋክቸሪንግ፣ የኮንስትራክሽን፣ የአገልግሎት እና መሰል ዘርፎች ላይ በተሰማሩ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው የሥራ ልምምድ እንዲያካሄዱ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ደረጃ የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክትን በ36 ወረዳዎች ለመተግበር የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡ የሙያ ክህሎት የሌላቸውን ወጣቶች የክህሎት ባለቤት ለማድረግ ቢሮው በመረጣቸው ተቋማት ለ6 ወር የስራ ላይ ልምምድና ስልጠና የሚወስዱ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን በአለም ባንክ ድጋፍ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በ11 ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግና 70 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አበባ ከተማም በዚሁ ፕሮጀክት 49 ሺህ ወጣቶችን የክህሎት ባለቤት በማድረግ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አቶ ሰብሃዲን ገልፀዋል። በመጀመሪያው ምዕራፍ በተመረጡ 36 ወረዳዎች 10 ሺህ 500 ወጣቶችን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች ከነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ገብተው እየሰለጠኑ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በተካልኝ አማረ
4.9K views09:33