Get Mystery Box with random crypto!

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረ | AMN-Addis Media Network

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) ነሐሴ 25/2014

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ  ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ በዋናነት ስራ ፈጣሪ ዜጎችን መደገፍ የሚያስችል ሲሆን፤ በሥልጠና፣ሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንቨስትመንት ስፍራዎች ላይ ምቹ የስራ ሁኔታን መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነትን በማሻሻል ረገድ ተቋማቱ በጋራ እንዲሰሩ ያስችላል፡፡

ስምምነቱንም የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ተፈራርመዋል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች የፋይናንስና ስልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

የስራ እድል ፈጣራ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚወጡ ዜጎችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው፦ ባንኩ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ፣ ክህሎትን ማስፋት፣ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣን እንዲሆን ማድረግ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ  መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በገበያ ሥርዓት ሊፈጸሙ የማይችሉ ሥራዎችን በፖሊሲ ጣልቃገብነት ተግዳሮቶችን በመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን  ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን  ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የስራ ፈጠራ ሃሳብ ይዘው የፋይናንስ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በማገዝ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሥምምነቱ በሀገር ደረጃ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እንዲሁም በወጪ ንግድ ዘርፎች ላይ የተሻለ የስራ ፈጠራ እድል ለማምጣት እንደሚያግዝ   ገልጸዋል።