2022-12-04 19:56:19
5 አመት የዘለቀውን የዘር ፍጅትና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እጥፍ ድርብ የሚያደርጉት " የህዝብ በዝምታ ተባባሪነትና መንግስታዊ ክህደት" ናቸው!
እንደአለመታደል ሆነና ፥ በአንድ መንግሥት አለሁ በሚልባት ሀገር ያለእረፍት ይህ ሁሉ እልቂትና ግፍ ሲፈፀም የመጀመሪያው እርምጃ ፥ እንደመንግስትም ሆነ እንደህዝብ የሚፈፀመውን እልቂት በስሙና በአፈፃፀሙ ልክ በትክክል ጠርቶ በአደባባይ በግልፅ ከማውገዝ ይጀምራል፡፡
ነገርግን ይህ ሁሉ ለሰሚው የሚከብድ በሀገራችን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እልቂትና ፍጅት ሲፈፀም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ሀላፊነት የነበረበት መንግሥት ተብዬው ሀይል አይደለም ወንጀሉን በትክክል ገልፆ በማውገዝ እልቂቱን የማስቆም መንግስታዊ ግዴታውን መወጣት ይቅርና እኚህን " እንደቅጠል የሚረግፉ ዜጎችን ጭምር ወክዬ" ተቀመጥኩ የሚለው ፓርላማ የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንኳ ነፍጓቸዋል፡፡ እልፍ ሲልም እልፍ ሲልም ከችግኝ ተከላ ጋር እያነፃፀሩ መሳቂያና መሳለቂያ አድርገውታል፡፡ ይህ ጭፍጨፋም ገና በጧቱ ያልተገታውና ተጠናክሮ የቀጠለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
መላው ለአንባገነን መሪዎች ሀዘን 40 ቀን ድንኳን ጥሎ ደረት እየደቃ ሲነፋረቅ የምናውቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ፥ በሚሊየኖች እልቂትና ስደት ላይ ሰብአዊነቱ ርቆታል ፥ የእንባ ከረጢቱ ደርቆበታል ብሎም ለማውገዝ የሚያስችለው አንደበቱ ተቆልፎበታል፡፡ ይህ ዝምታው ነገ ማንንም ወደማያስቀር የእልቂት ውቅያኖስ እየዘፈቀው መሆኑን እንኳ ለአፍታ እንዳያስብ አድርጎታል፡፡
ከዝምታው ባሻገር ሌላው ሰቆቃና በደሉን እጥፍ ድርብ የሚያደርገው ክህደት ነው፡፡፡ መንግስትም ሆነ በዙሪያው ያሉ ( ሸኔ ፥ አመራሮች ፥ አክቲቪስቶች ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ፣ …ወዘተ) ይህን በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈፀም እልቂት ፥ በስሙ ጠርቶ ከማውገዝና እንዲቆም ከመረባረብ ይልቅ ፥ ተራ ግጭት በማስመሠል እልፍ ሲልም በመካድ ብሎም "አማራ ተጨፈጨፈ" ለሚለው መራራ ሀቅ አቻ ማስተባበያ ጨፍጫፊና ተጨፍጫፊ ታሪክ በመፍጠር እልቂቱ እንዲባባስና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣቱ ቀርቶ ወደማንወጣውና ማንኛችንንም ተራፊና አሸናፊ ወደማያደርገን ዘላቂ የእርስበርስ እልቂት ውስጥ እንድንገባ ከፍተኛውን ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አንዳች ልበ-ስውርነት ሆኖ እንጂ ፥ ለኦሮሞም ሆነ ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያስብ ሀይል ፈፅሞ ይህ አይነቱን ነውር ከመፈፀም በተቆጠበ ነበር፡፡ ይህ የሚፈፀመው እልቂትም እነርሱ የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካትና በዙፋን ለመሰንበት ሲሉ በየአደባባዩና መድረኩ ሲረጩት የነበረው የጥላቻ ትርክትና ፖለቲካ ያፈራው መርዛማ ፍሬ ነው፡፡
ሀገራችን የተሸፋፈነውንና የተደበቀውን ገላልጦ የመመልከት ሀያልነት ያለው ፈጣሪ እንኳ የማይፈራባት የጭካኔ ምድር ሆናለች!
4.0K viewsedited 16:56