2022-11-09 19:32:57
መሰረታዊ የሆኑ 5 የኢኮኖሚክስ ትምህርት መነሻ ሃሳቦች!
የኢኮኖሚክስ ትምህርት መሰረት ምርጫን የመወሰን ጉዳይ ነው! ስለዚህ ኢኮኖሚክስን በተረዳችሁ ቁጥር ለምታደርጉት ማንኛውም ውሳኔ ምክንያታዊነት እድትፈጥሩ ለማድረግ ነው ትምህርቱ የተቋቋመው፡፡
#እጥረት፡- አብዛኞቹ በዙሪያችን ያሉ ሃብቶች እና የሰዎች ፍላጎት መካከል ከፍተኛ አለመጣጣም አለ፡፡ ለምን? ምክንያቱም ሃብቶች (የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ) ውስን በመሆናቸው እና የሰዎች ፍላጎት በሂደት እያደገ በመሆኑ ያልተገደበውን የሰዎች ፍላጎት ማሟላት የሚችል ሃብት ሊኖር አለመቻሉ ይታወቃል፡፡
#ለምሳሌ፡- በአዲስ አበባ ተሰርተው በሚቀርቡ ቤቶች እና ሰዎች ለቤቶች ያላቸው ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ! ስለዚህ ኢኮኖሚክስ በተለያዩ ዘዴዎች ይህንን የሰዎች የቤት ፍላጎት እንዴት ማሟላት አንደሚቻል የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል (በግል ሴክተሩ መገንባት፤ መሬት ከሊዝ ነጻ ማቅረብ፤ የማህበራ የቤት ስርዓት ማዘጋጀት፤ ነባር አነስተኛ የመንግስት ቤቶችን በርካታ ሰው በሚይዙ ህንጻዎች መለወጥ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ትብብር ማሳደግ፤ በቤት ልማት የውጪ ባለሃብት መጋበዝ፤ በአነስተኛ ወጪ የቤት አሰራር ቴክኖሎጂ መፍጠር፤ የቤት አልሚዎችን መቆጣጠር፤ የመሬትን ባለቤትነት ፖሊሲ ማሻሻል፤ ወዘተ)፡፡
በሀገራችንም የሃይል፤ የመንገድ፤ የውጪ ምንዛሬ፤ የትራንስፖርት፤ የነዳጅ፤ የበጀት፤ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ፤ ቤተመጽሃፍት፤ የመስኖ፤ የአፈር ማዳበሪያ፤ የደህንነት ዋስትና፤ ወዘተ የእጥረት ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢኮኖሚክሰ ትምህርትን የፈጠረው የአቅርቦት እጥረትን ከአዳጊው ፍላጎት ጋር ስለማጣጣም ሲባል ነው፡፡
#አቅርቦት እና #ፍላጎት፡- እጥረት በባህሪው ሰዎች ተጨማሪ እንዲያመርቱ፤ እንዲሸጡ እና እንዲገዙ ወደሚፈልጉበት ስርዓት ይከታል፡፡ ስለዚህ የሰዎች ፍላጎት (የቁሳቁስ፤ የአገልግሎት እና የውጪ ምንዛሬ) በገበያው ካለው አቅርቦት (የቁሳቁስ፤ የአገልግሎት እና የውጪ ምንዛሬ) ከበለጠ እጥረት አለ ማለት ነው! ኢኮኖሚክስ ይህ ሁኔታ የሚስተካከልበትን ዘዴ ይፈልጋል፡፡ አቅርቦቶችን ከማሳደግ እስከ ፍላጎቶችን መገደብ ድረስ በአቅርቦት እና ፍላጎት መካከል የሚኖርን ክፍተት ለመሙላት የሚደረጉ የኢኮኖሚክስ መላዎች ናቸው፡፡
#ፉክክር፡- የእጥረት መከሰት በገበያ የሚኖርን ፉክክር ያሳድጋል፡፡ ለምሳሌ፡- የውጪ ምንዛሬ እጥረት ሰዎችን በጥቁር ገበያ ያላቸውን የመሸመት ፍላጎት በማሳደጉ ወደ ፉክክር ደረጃ ከቶታል፡፡ በገበያው የሚፈጠርን ጤነኛም ሆነ ጤነኛ ያልሆነ ፉክክር ስርዓት የማስያዝ ሃላፊነትን ኢኮኖሚክስ ይወጣል! እንዴት? የውጪ ምንዛሬ ፉክክሩ የመነጨው ከእጥረት ከሆነ የውጪ ምንዛሬ የሚገኝባቸው አማራጮች፤ የውጪ ምንዛሬ አጠቃቀም እና የውጪ ምንዛሬ የሚያስወጡ ምርቶች የመተካት አማራጭ ለገበያው ይሰጣል እንደማለት ነው፡፡
#ዋጋ_ንረት፡- በኢኮኖሚ ውስጥ በተከታታይ የቁሳቁስ እና የአገልግሎት ዋጋ እየጨመረ መምጣት የአንድ ኢኮኖሚ አደጋ ሲሆን ይህንን ሁኔታ ለማስተካካል ኢኮኖሚክስ የገንዘብ አቅርቦት እና ስርጭት ቁጥጥር፤ የማምረቻ ግብዓት አቅርቦት፤ የምርት እና የምርታማነት መጠን፤ የበጀት አጠቃቀም፤ የፕሮጀክቶች አይነት፤ የገበያ ቁጥጥር፤ የኮታ ስርጭት፤ የቀረጥ መጠን፤ የወለድ መጠን፤ የብድር አቅርቦት፤ ወዘተ እየተለዋወጡ እንዲተገበሩ የሚያደርገው ኢኮኖሚክስ ነው፡፡
#የንግድ_ጉድለት፡- አንድ ሃገር ከውጪ ለምታስገባቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች የምታወጣው ወጪ ወደ ውጪ ምርት እና አገልግሎት ልካ ከምታገኘው ገቢ የበለጠ ሲሆን ኢኮኖሚክሱ ለውጪ ንግድ የሚቀርቡ ምርቶች ምርታማነት እና አይነት መጨመር፤ የገበያ አማራጭ መለየት፤ የሃገር ውስጥ አምራቾችን የማሳደግ፤ መሰረታዊ የማይባሉ ምርቶች ማገድ፤ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ ማስፋት፤ ወዘተ ሊያደርግ ይችላል፡፡
አብዛኞቹ የኢኮኖሚክስ አስተምሮቶች ከላይ ከተጠቀሱ መሰረታዊ መነሻዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ስራ አጥነት የኢኮኖሚው ችግር ቢሆንም በምርት ስርዓት አቅርቦት ሲያድግ፤ የዋጋ ንረት ሲረጋጋ፤ የውጪ ንግድ ጤነኛ ሲሆን፤ ወዘተ መልስ እያገኘ የሚሄድ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱ ስርዓቶች በሙሉ ብቸኛ ምርጫ ስለሌላቸው ጠንካራ የሚባለውን አማራጭ ለመምረጥ እንዲረዳ የተለያዩ የኢኮኖሚክስ አስተምሮቶች/Theories ይቀረጻሉ፡፡
መቀሌ እያለን የመጀመሪያ ድግሪ ስንማር የኢኮኖሚክስ ትምህርት ብዙ በመሆኑ የዕለት ውሏችን በአብዛኛው ተመሳሳይ ነበር! መብላት፤ ማጥናት እና ከእኩለ ለሊት በኋላ መተኛት! ነገር ግን ከምንማራቸው እና ከምናነባቸው በላይ ብዙ ያልሰማናቸው የኢኮኖሚክስ አስተምሮቶች እንዳሉ ይሰማን ነበር፡፡ አሁንም በተቻለ መጠን የተወሰኑ የኢኮኖሚክስ አርቲክሎች ማንበብ መለማመድ እና አለመሰልቸት ተገቢ ነው፡፡
Subscribe
YouTube፦ https://youtube.com/channel/UCzc8ISpZJ6RskJmd_DEx7WQ
1.9K viewsWasyhun Belay, 16:32