2022-12-20 19:24:56
በምዕተ ዓመቱ ከተፈጠሩ 12 ስራ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ነው፤ በ2008 'Top 100 Global Thinkers' ከሚባሉት ውስጥ በደረጃ 2ኛው ነበር! በ2006 የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት አግኝቷል፤ በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት በዓመት አንድ ቀን በስሙ መታሰቢያ "January 14 Muhammad Yunus Day" ተሰይሟል፤ ለመሆኑ ይህ ኢኮኖሚስት ለዓለም ምን ሰርቶ ነው?
በዓለም ላይ ብዙ ኢኮኖሚስቶች ከድህነት እንዴት መውጣት እንደሚቻል ቢያስተምሩም ያወሩትን እራሳቸው አድርገውት አይገኙም ነገር ግን ሙሃመድ የኑስ በ100 ሀገራት የሚተገበር የአነስተኛ ብድር አቅርቦት ተቋም በማቋቋም ሚሊዮኖችን ከድህነት ለማውጣት በቅቷል፡፡
የኑስ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሃል 1940 በባንጊላዲሽ ቤተሰቦቹ ከወለዷቸው 9 ልጆች መካከል 3ኛው ሆኖ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ በ20 ዓመቱ የመጀመሪያ ድግሪ፤ በ21 ዓመቱ የማስተርስ ድግሪ እንዲሁም በ31 ዓመቱ የዶክትሬት ድግሪውን በኢኮኖሚክስ ጨርሷል፡፡
"ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ሃሳቦችን ባስተምርም በርሃብ ለሚጠቁ ዜጎች ወዲያው ምንም ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩ ያስቆጨኛል" የሚለው የኑስ፤ በ1976 አስተማሪ ሆኖ በሚያገለግልበት ዩኒቨርስቲ አካባቢ በሚገኝ ሰፈር ውስጥ ወክ በሚያደርግበት ወቅት በቀርከሃ ንግድ የተሰማሩ የሰፈሩ ድሃ ሴቶች ቀርከሃ ለመግዛት አራጣ እንደሚበደሩ እና ያገኙትን ገቢ በአብዛኛው ላበዳሪ እንደሚከፍሉ ይመለከታል እንዲሁም በተመሳሳይ ባንክ ቤቶች መያዣ ማቅረብ ለማይችሉ ሰዎች ብድር እንደማይሠጡም አወቀ፤ በዚያ ወቅት ለድሆች ገንዘብ ቢሰጣቸው በእምነት እንደሚመልሱ በማመን ያለውን 27ዶላር ለ42 ሴቶች በ2 ሳንቲም ወለድ ያበድራቸዋል፤ ያኔ አነስተኛ ብድር (Microcredit እና Microfinance) አገልግሎትን ሀ ብሎ ጀመረ፡፡
ከባንክ በመበደር ለድሆች ያለ ምንም ወለድ ማበደሩን ቀጥሎ በ6 ዓመት ውስጥ 28ሺ አባላትን ማፍራት የቻለው የኑስ ስራውን ወደ ድርጅት አሳድጎ የመንደር ውስጥ ባንክ ማለትም Grameen Bank አቋቁሟል፤ ማህበረሰቡ ሙስሊም በመሆኑ ብድር ያለመውሰድ እምነት ስለነበራቸው ፈተና ሆኖበት የነበር ቢሆንም በ2007 (ከተቋቋመ በ31ዓመት ውስጥ) 6.38 ቢሊዮን ዶላር ለ7.4 ሚሊዮን ሴት ድሆች ብድር አቅርቧል፡፡ ይሄ ሁሉ ብድር ያለምንም መያዣ እርስ በርስ በመተማመን "Solidarity Groups" ብቻ የተሰጠ ነው፡፡ የግራሚን ፕሮጀክቱ እያደገ በግብርና፤ በአሳ ማርባት፤ በመስኖ፤ በሶፍትዌር፤ በሞባይል እና በኔትዎርክ አገልግሎቶች በመሳተፍ በባንጊላዲሽ ትልቅ የግል ኩባንያ ሆኗል፡፡
የግራሚን ስኬት ዛሬ ላይ 100 ታዳጊ ሀገራት ሌላው ቀርቶ አሜሪካንን ጨምሮ በሌሎች ያደጉ ሀገራት ጭምር ተስፋፍቶ ከ94% በላይ ደንበኞቹን ሴቶቸ በማድረግ ሚሊዮኖችን ከድህነት አላቋል፡፡ በዚህም ተግባሩ ሙሃመድ የኑስ እና ያቋቋመው ግራሚን ባንክ በጋራ የ2006 የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የኑስ በኖቤል ሽልማት ያገኘውን 1.4 ሚሊዮን ዶላር ለድሆች ተመጣጣኝ ምግብ ለሚያቀርብ ድርጅት ማቋቋሚ እና በባንጊላዲሽ ለድሆች አገልግሎት የሚሰጥ የሃይን ሆስፒታል ለማቋቋሚያ አድርጓል::
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ከ2008 ጀምሮ በዓመት አንድ ቀን በስሙ መታሰቢያ ማለትም "January 14 Muhammad Yunus Day" በተጨማሪም የኑስ ከ20 ሃገራት 50 የክብር ዶክትሬት እና ከ26 ሀገራት 113 ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተበርክቶለታል፡፡ በ2010 ዓለማችን ካፈራቻቸው 50 ተጽኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል 40ኛው የኑስ ነው፡፡ ዛሬ ላይ የኑስ ጡረታ በመውጣት አለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት ትምህርቶችን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
የዓለም የተባበሩት መንግስታት አነስተኛ ብድር (Microcredit እና Microfinance) ድርጅትን በየሀገሪቱ በመመስረት በተለይ የሴቶች ድህነትን መቀነስ እንደሚቻል በማመኑ በ100 ድሃ ሀገራት (ኢትዮጲያን ጨምሮ) እንዲስፋፋ አድርጓል፤ ብዙዎቹም ተለውጠዋል የዚህ ሁሉ ባለውለታ ደግሞ የኑስ ነው።
YouTube፦
Facebook፦ https://www.facebook.com/EconomistWasyhun/?modal=admin_todo_tour
2.4K viewsWasyhun Belay, 16:24