2022-12-02 13:59:18
ፀረ ሙስና ዘመቻ
<<በመዲናዋ የአርሶ አደር ልጆች ወይም የልማት ተነሽ ሳይሆኑ የሆኑ በማስመሰል በሐሰት ሙስና የሰሩ ግለሰቦች ተለይተዋል>> የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ሥር ውለዋል
በቅርቡ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ሥራውን በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ የኮሚቴው አባላት በዛሬ ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል።
በአዲስ አበባም የአርሶ አደር ልጆች ወይም የልማት ተነሽ ሳይሆኑ የሆኑ በማስመሰል በሐሰት ሙስና የሰሩ ግለሰቦችም ተለይተዋል ብለዋል የብሔራዊ ኮሚቴው አባል ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ።
175 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታና የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝበራ የፈፀሙ እንዲሁም በፍትህ ዘርፉ ስልጣናቸውን በመጠቀም ከግለሰቦችና ከንግድ ተቋማት ጋር ለግል ጥቅማቸው ሲሰሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችም ተለይተዋል ተብሏል።
ኮሚቴው ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎችን ማለትም የህግ፣ የመረጃ እና የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴዎችን በማቋቋም እቅድ አውጥቶ ሥራ መጀመሩንም የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።
በመንግሥት አግልሎት አሰጣጥ፣ በፋይናንስና ግዥ፣ በፍትህ ስርዓቱ እና በመሬት አስተዳደር እንዲሁም በመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦት ዘርፎች ላይ ሙስና በከፍተኛ ኹኔታ እንደሚስተዋልም ገልጸዋል።
"የሌባ ትንሽ የለውም" ያሉት ተመስገን ጥሩነህ፤ ከመታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ ህብረተሰቡን የሚያማርሩት ላይ ጠንካራ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ተናግረዋል።
(ኢፕድ)
3.1K viewsAnt B, 10:59