2023-03-02 14:22:56
አንቶኒ ሞክለር ስለ ዐድዋ ጦርነት የመጨረሻ ምዕራፍ ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤
“ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ቅዳሴውን በሚመሩበት ግዜ ኹለት ጥይት ከውጭ ተተኮሰ:: .. ራስ መኰንንም የኢጣልያኖችን መምጣት ተናገሩ:: .. አቡኑም መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው፣ “ልጆቼ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚገለጽበት ቀን ነው:: ሒዱ:: ለሃይማኖታችሁና ለንጉሣችሁ ተከላከሉ:: ኹላችሁንም ከኃጢአት እግዚአብሔር ይፍታችሁ፤ አሉ:: መኳንንቱም መስቀል ተሳልሞ ወደ ውጊያ ገባ ይላል፤“ ጳውሎስ ኞኞ፡፡ (ዐጤ ምኒልክ፣ ገጽ 203)
የኢትዮጵያ ዋና ዋና የጦር መሪዎች ቅዳሴ ላይ ነበሩ:: ጣልያን የመጀመርያውን ጥይት እንደተኮሰ -ቅዳሴውን አጠናቀው የጦር መሪዎቹን ባርከው “ሒዱና ተዋጉ” ብለው መንፈሳዊ ቡራኬና የማበረታቻ ቃል ሰጥተው ኢትዮጵያውያንን ያሰናበቱት ጦርነቱን ያስጀመሩት – እዚያው በቦታው የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው::
የጦር አዝማቾቹ ወደ ውጊያ ሲገቡም ሊቀ ጳጳሱና ሌሎቹ ካህናት እጃቸውን ዘርግተው ይጸልዩ ነበር:: ይህን ጉዳይ ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ በ“ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ዐጤ ምኒሊክ” ገጽ 268 እንዲህ አስፍረውታል፡-
“አቡነ ማቴዎስም ታቦተ ማርያምን ይዘው ካህናቱም መነኮሳቱም ኾነው ምሕላ ይዘው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁር ሳይጨርሱ ድል ለኢትዮጵያ ኾነ:: እኛም ለጊዜው የፊተኛ ሰልፍ ድል ቢሆን የተኩሱ መጨረሻ መስሎን ደስ አለን፡፡“
የዐድዋ ጦርነት ላይ በአካል ተገኝተው ታሪክ ሲዘግቡ የዋሉት ጸሓፌ ትእዛዝ፣ በዚሁ ዘገባቸው ገጽ 264 ላይ እንዲህ ሲሉ ይቀጥላሉ፤
“የዘመቱትም የኢትዮጵያ መነኰሳት እጅግ ብዙ ነበሩ:: ወይባ፣ ኣጥፍ፣ የዳባ ቀሚስ የለበሱ፣ የሰሌን ቆብ ያደረጉ ብዙ ነበሩ:: የጦርነቱም ለት እኩሉ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር፣ እኩሉ ደግሞ ከንግሥቲቱ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር፣ እኩሉ ደግሞ ከሰልፈኛው ጋር ኾነው ወደ ጦሩ የሚሔደውን እየናዘዙ፣ የደከመውን እያወገዙ ሲያዋጉ ዋሉ::”
በዐድዋ ዘመቻ ድል አድርገው ነጻነታችንን የሰጡን አርበኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን ብቻ አይደሉም:: ሰማዕት ኾነው ነጻነታችንን የሰጡን፣ አበው ካህናት እና መነኰሳት አባቶቻችንም ጭምር ናቸው:: ለሀገራችን ነጻነት ካህናትና መነኰሳት ከወታደሩ እኩል እንደ ወታደር ተጉዘዋል:: እንደ ጦረኛ ተዋግተዋል:: አዋግተዋል:: ካህናቱ ብቻ ሳይኾኑ ታቦታቱም ዘምተዋል።
ድሮ የዐድዋ በዓል ሲዘከር፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት በምልዓት ይነገር እንደነበር ድርሳናት ይገልጻሉ:: በዐድዋ ክብረ በዓል የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕልም ይታተም ነበር:: ይህ ሥርዓት ከቀድሞው መንግሥት የኮሚኒዝም አስተሳሰብ ወደ ሥልጣን መምጣት ጋራ ተያይዞ እንደቀረ ከዚያም በኋላ እስከ አኹን የቤተ ክርስቲያኗ ድርሻ እንዲወሳ አይፈለግም::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የዐድዋ ድል ዋነኛ ባለውለታ ናት:: ዐድዋ ሲወሳ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዋፅኦ ይነሣ! ሌላው ባያደርገው ለእኛ ለኦርቶክሳውያን ግን ታሪካችን ነው:: በዓሉ በሚከበርበት ጊዜ ኹሉ የቤተ ክርስትያንዋ አስተዋፅኦ ይወሳ፤ ይነሳ።
በvideo ለማግኘት
https://www.youtube.com/channel/UCfWtKqb7qsxjXey4kN_tykg?sub_confirmation=1
ዘወትር ምክረ አበውለማግኘት ሰማያዊውን ነክታችሁ ተቀላቀሉ ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ
@mekra_abaw
@mekra_abaw
@mekra_abaw
✧━━━━━━━━━━━━━━━━━✧
❍ㅤ ⎙ㅤ ⌲ ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ ˢᵃᵛᵉ ˢʰᵃʳᵉ
699 views▂▃▄▅▆░ Hab mis ░▆▅▄▃▂, 11:22