2021-11-16 12:26:04
ሩሲያ የማይሰሩ ሳተላይቶችን በሚሳኤል ማውደም ጀመረች
የሩስያ ፀረ-ሳተላይት ሚሳኤል ሙከራ ከየአቅጣጫው ውግዘት እያስተናገደ ነው ሩሲያ "አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው" የሚሳኤል ሙከራ በማድረግ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (አይኤስኤስ) የሚገኙ ሠራተኞችን አደጋ ላይ ጥላለች ስትል አሜሪካ አውግዛለች።
ሙከራው ከሩሲያውያን ሳተላይቶች አንዱን ያፈነዳ ሲሆን በተፈጠረው ስብርባሪ ምክንያትም የጣቢያው ሠራተኞችን መጠለያ እንዲፈልጉ ያስገደዳቸው ነበር።
ጣቢያው በአሁኑ ጊዜ ሰባት አባላት አሉት። አራቱ አሜሪካውያን ሲሆኑ ሁለት ሩሲያውያን እና አንድ ጀርመናዊ ናቸው።
የጠፈር ጣቢያው በ420 ኪሜ ከፍታ ላይ ይዞራል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ዛሬ ባደረጉት ንግግር "የሩሲያ ፌዴሬሽን በግዴለሽነት በቀጥታ ወደ ላይ በሚወጣ ፀረ-ሳተላይት ሚሳኤል በራሱ ሳተላይት አጥፊ የሳተላይት ሙከራ አድርጓል" ብለዋል።
"ሙከራው እስካሁን ድረስ ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ ክትትል የሚደረግባቸው የምሕዋር ስብርባሪዎችን ፈጥሯል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ የምሕዋር ስብርባሪዎች የፈጠረም ሲሆን እነዚህም የሁሉንም ሀገራት ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው።" ብለዋል
የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን በድርጊቱ መናደዳቸው ገልጸዋል።
"በሰው ልጅ የጠፈር በረራ ውስጥ ካላት ረዥም ታሪክ አንጻር ሩሲያ በጣቢያው ላይ የአሜሪካ እና ዓለም አቀፍ አጋር ጠፈርተኞችን ብቻ ሳይሆን የራሳቸው እና የቻይናን የጠፈር ጣቢያ አደጋ ላይ ይጥላሉ ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው" ብለዋል በመግለጫቸው።
የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ሮስኮስሞስ ድርጊቱን አቅልሎታል።
ኤጀንሲው በትዊተር ገፁ ላይ "ዛሬ ሠራተኞቹ በመደበኛ አሠራር መሰረት ወደ ጠፈር መንኮራኩር እንዲገቡ ያስገደዳቸው ቁስ ከጣቢያው ምህዋር ርቋል። ጣቢያው በአረንጓዴ ዞን ውስጥ ነው" ሲል አስፍሯል።
የጠፈር ፍርስራሾችን የሚከታተለው እና ሊዮላብስ የተሰኘው ኩባንያ በኒውዚላንድ ያለው የራዳር ማዕከሉ ጊዜ ያለፈበት የጠፈር መንኮራኩር መኖር በነበረበት ቦታ በርካታ ዕቃዎችን እንዳገኘ ተናግሯል.
ፕራይስ የሩስያን ድርጊት "አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
"አሜሪካ እና ከአጋሮቿ ጋር በመተባበር ለሚያደርጉት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ምላሽ ለመስጠት እንሠራለን" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ በበኩላቸው ሙከራው "የጠፈር ደህንነትን እና ዘላቂነትን ሙሉ በሙሉ ችላ መባሉን ያሳያል" ብለዋል።
"በዚህ ሙከራ ምክንያት የሚፈጠረው ስብርባሪ የሳተላይቶችን እና የሰዎችን የጠፈር ጉዞ አደጋ ላይ በሚጥል ምህዋር ውስጥ ለብዙ ዓመታት ይቆያል" ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ሳተላይቶችን ከመሬት ላይ የማምጠቅ አቅም አላቸው።
እንደዚህ አይነት ሚሳኤሎችን መሞከር ብዙም አልተለመደም። ለሁሉም ሃገራት ከባቢውን ስለሚበክል በተሞከረ ቁጥርም ሰፊ ውግዘትን ያስከትላል።
ቻይና በአውሮፓውያኑ 2007 ጡረታ ከወጣች የአየር ሁኔታ መከታተያ ሳተላይቶች መካከል አንዷን ከጥቅም ውጭ ስታደርግ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ ስብርባሪዎች ተፈጥረዋል። ይህ ስብርባሪ ለቻይና ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ጭምር የህዋ ተልዕኮዎች ላይ ቀጣይነት ያለው አደጋ አስከትሏል።
ምንጭ - Bbc Amharic
የዩቲውብ ቻናላችንን subscribe ለማድረግ ወይም የለቀቅናቸውን ቪዲዮዎች ማየት ለምትፈልጉ በዚህ ሊንክ ታገኙታላቹ
https://youtube.com/channel/UCgmzpzIOElQB2v1JZtkjKQg?sub_confirmation=1
919 viewsedited 09:26