2022-10-21 12:25:54
የ2014 ዓም. 12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር አቀፍ ፈተና ተጠናቀቀ
--------------------------------------------------------------------------
ጥቅምት 11/2015ዓም (ትምህርት ሚኒስቴር) በሁለት ዙር ሲሰጥ የነበረው የ2014 ዓም 12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ተጠናቋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሁለት ዙር ሲሰጥ በነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ 900ሺህ በላይ ተማሪዎች በ130 የፈተና ጣቢያዎች ተፈትነዋል።
ፈተናው በመጀመሪያዉ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ሂደት ካጋጠሙና በመጀመሪያዉ ዙር ማጠቃለያ ከተገለጹ ችግሮች ዉጪ በታቀደው መሰረት በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን የሁለተኛ ዙር ተፈታኞችም ከዛሬ ጀምሮ ወደ የአካባቢያቸው መመለስ ጀምረዋል።
ዩኒቨርስቲዎች ለፈተናው ውጤታማነት ያደረጉት ዝግጅት እና በፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ የነበራቸው አስተዎፆ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ተፈታኞችም የፈተና ስርዓቱን ባከበረ መልኩ ፈተናቸውን ሲወስዱ ቆይተዋል።
ለዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ለወላጆች፣ ተፈታኝ ተማሪዎች እና ፈታኝ መምህራን ፣ጣቢያ አስተባባሪዎች ፣ሱፐርቨይዘሮች ፣ የጸጥታ አካላት እና በየደረጃው ለፈተናው ስኬታማነት የበኩላቸውን ለተወጡ አካላትም ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
የዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ ሂደት የፈተና ስርቆት እና ኩረጃን በማስቀረት ሂደት የነበረው አስተዎፆ ውጤታማ መሆኑ የታየበት እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።
በቀጣይም የፈተና አሰጣጥ ስርዓቱን በማሻሻል የተሻለ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድን ለመፍጠር በትኩረት የሚሰራ ይሆናል።
የፈተናዉን አጠቃላይ ሂደት በሚመለከት ዝርዝር መረጃዎችን በቀጣይ የምናሳዉቅ ይሆናል፡፡
10.2K viewsedited 09:25